Gambela’s freedom forefront has no law to keep Gambela in power after September 25

Gambela’s freedom forefront has no law to keep Gambela in power after September 25

የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ከመስከረም 25 በኋላ የጋምቤላ ብልጽግና ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችል የህግ ማእቀፍ የለውም አለ

የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ከመስከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም በኋላ የጋምቤላ ብልጽግና ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችል የህግ ማእቀፍ እንደሌለው አሳወቀ። ግንባሩ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጋምቤላ ክልል ውስጥ የተደረገዉ ምርጫ የተጭበረበረ እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምንም አይነት ከፍተኛ ድምጽ እንዳያገኙ ለማስቻል በብልጽግና ቅንብር የታጀበ የይስሙላ ምርጫ እንደነበር ገልጿል፡፡

ከዚህም በላይ የጋምቤላ ነጻነት ግንባር የብልጽግና አገዛዝ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም መንግስት እንደሚመሰርት ፓርላማው ያሳወቀ መሆኑን ገልጾ በአሁኑ ሰዓት አሸናፊ ነኝ ብሎ ራሱን የሰየመው የጋምቤላ ብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ህዝብ ባልመከረበት እና ባልመረጣቸው ሰዎች በድጋሚ የጋምቤላ ክልልን ለማስተዳደር በመሯሯጥ ላይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ አክሎም “ይሁን እንጂ በ2007 ዓ.ም የተመረጠው የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት የስልጣን ጊዜው በ2013 ዓ.ም ያበቃ የነበረ ቢሆንም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በህገ-ወጥ መንገድ በተደረገው የህገ-መንግስት ማሻሻያ ስልጣኑ እስከ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ለአንድ ዓመት መራዘሙ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ከመስከርም 25 ቀን 2014 ዓ.ም በኃላ የክልሉ ገዢ ፓርቲ በህዝብ ሳይመርጥ ክልሉን ማስተዳደርም ሆነ ድጋሜ የህገ-መንግስት ማሻሸያ ማድረግና የስልጣን ጊዜ ማራዘም አይችልም” ብሏል።

እንዲሁም የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ያለ ምርጫ ስልጣን ላይ መውጣት እንደማይቻል ሁሉ ስልጣን ላይ መቆየትም አይቻልም። ክልሉ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ በመሆኑ፣ ከተለያዩ ክልሎችና አገራት ጋር ሰፊ ደንበር የሚጋራ ቀጠና በመሆኑ እና ለአራት ዓመታት የቆየው የፀጥታ ችግር እና አለመረጋጋት ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የአመራር ክፍተት እንዳይፈጠር ለማድረግ ያስችላል ያላቸውን አራት የመፍትሄ አማራጮች አስቀምጧል። እነዚህም የሰላም ድርድር፣ የሽግግር መንግስት ማቋቋም፣ ጊዜያዊ አስተዳደር መመስረት ወይም ባላደራ መንግስት ማቋቋም የሚሉት ናቸው።