Fact: ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የመከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ በዛሬው ዕለት ተገናኝተው በመደመር እይታ በኢህአዴግ

#Fact

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የመከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ በዛሬው ዕለት ተገናኝተው በመደመር እይታ በኢህአዴግ ዉህደትና በብልጽግና ፓርቲ መደራጀት ጉዳይ በኦሮሞ ባህልና ወግ መሰረት ከተወያዩ በህዋላ ባሃሳቦች ተግባብተዋል የሚል ዜና ከኦዴፓ (ODP Official) ካድሬዎች ዘንድ ተሰምቶአል። የዚያው ተለጣፊ ፕሮፓጋንዲስቶችም እንደተለመደው የማራገብ ስራቸውን በስፋት ቀጥለዋል።
የተባለው ሙሉ በሙሉ ዉሸት አይደለም። ለለውጥ ያህልም ትሁን የካድሬዎቹና የግብረ አበሮቻቸው ምናብ መሰረተ ቢስ አይደልም ። ነገሩ እንዲህ ነው።

አቶ ለማ መገርሳ “መደመር አልገባኝም፣ ዉህደቱ ለኦሮሞ ሕዝብ አይጠቅምም። ይጠቅማል ቢባል እንኳ ጊዜው አሁን አይደለም። ያልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎች አሉ። ቅድሚያ ለነሱ መስጠት ይገባናል” ብለው በVOA ራዲዮ ጣቢያ ላይ ከተናገሩ ጊዜ ጀምሮ ጠ/ሚ አብይ ወደ አቶ ለማ ዘንድ ለሽምግልና ያልላኩት የህብረተስብ ክፍል የለም። ሽማግሌዎች፣ ባለሀብቶች፣ አባገዳዎች፣ ካህናት፣ ሼኮችና የቅርብ ጓደኞች ወደ አቶ ለማ ዘንድ ሲተምሙ ነበር።

ለነዚህ ሁሉ የአቶ ለማ መልስ አንድና አንድ ነበር። “እኔ ድምፄን አጥፍቼ በነበር ጊዜ የት ጠፋህ አላላችሁም። አሁን አንድ ጊዜ ብተነፍስና ሃሳቤን ለሕዝብ ብገልፅ መቆምያ መቀመጫ አሳጣችሁኝ። እኔና አብይ ጥል የለንም። የፖለቲካ አስተሳሰብና አመለካክት ልዩነት ግን ተፈጥሮአል። ይህ ደግሞ በሽምግልና የሚያልቅ ጉዳይ አይደለም። ስለጥረታችሁ አመሰግናለሁ። ከዚህ ወዲያ ግን አትቸገሩ” ብለው መልሰዋቸው ነበር። ጠ/ሚ አብይ ተስፋ ሳይቆርጡ ሽማግሌዎችን ከቦረናና ጉጂ አስመጥተው ባለፈው ሰሞን ወደ አቶ ለማ ላኩ። ሽማግሌዎቹም ሁለታችሁን በአንድነት ሳናነጋግር ፈፅሞ አንመለስም ብለው ግድ ስላሉ አቶ ለማ ሽማግሎችን አይሆንም ማለት የኦሮሞን ባህል መዘርጠጥ ይሆንብኛል ብለው ጠ/ሚ አብይን ለመገናኘት ተስማሙ። የዛሬው ስብሰባ አላማ ይህ ነበር።

ስብሰባው እንደተጀመረ ጠ/ሚንስትሩ “አብረን እንስራ” የሚል ሃሳብ አቀረቡ። አቶ ለማም “ትናንትም አብሬ ሰርቻለሁ። አሁንም እየሰራሁ ነው። ይህ እንደ ችግር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ይሁን እንጂ የሃሳብ ልዩነት በመካከላችን እንዳለ የአደባባይ ምስጢር ነው። የኔን ሃሳብ በተለያዩ የኦዴፓ መድረኮች በይፋ ገልጫለሁ። በኔ እምነት 1) የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች እስካሁን አልተመለሱም። እንዲያሙ አልተነኩም። ለእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማስገኝት የተሰጠንን አደራ እንደመወጣት አዲስ ፍልስፍና እና የፓርቲ ዉህደት እያልን ጊዜ እያባከንን ነው። 2) ኦዴፓ እነዚህን በአደራ የተቀበልናቸውን የህዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችለን መሳሪያ ነው። ይህ ድርጅት ይብዛም ይነስ ለኦሮሞ ህዝብ የታገለና የሚታግል ድርጅት ነው። ማፍረስ አይገባንም።” ብለው ተናገሩ።

በነዚህ ጉዳዮች ላይ ከመከሩ በሁዋላ ጠ/ሚ አብይ የአቶ ለማ ሀሳብ ጋር እንደሚስማሙ ተናገሩ። አብረዉ ለመስራት እንደሚፈልጉ ገልፀው ነገሩን ቁዋጩት።በመጨረሻም በመካከላቸው ያሉትን የፖለቲካ ልዩነቶች አስመልክቶም አቶ ለማ ያላቸውን አቁዋሞች ይዘው መቀጠል እንደሚችሉ ተስማምተው እንደተለያዩ ከውስጥ አዋቂ ምንጮች የደረሱን መረጃዎች አረጋግጠዋል።

Via: Tsegaye Ararssa