ESAT Eletawi Wed 06 June 2018

ESAT Eletawi Wed 06 June 2018

ሁለቱ የዛሬ ውሳኔዎች የራሳቸው ጥቅምና ጉዳት እንዳላቸው አያጠራጥርም። በየትኛውም መለኪያ ግን የህወሀት አጥር እየፈራረሰ መሆኑን ያመላከቱ ውሳኔዎች ናቸው ማለት ይቻላል። አብዮታዊ ዲሞክራሲን በመቃብሬ ላይ ካልሆነ ብሎ የተቸነከረው ኢህአዴግ የርዕዮተ ዓለም ለውጥ ማደረጉን ሳይነግረን በህይወት እያለ የሊብራል ኢኮኖሚን መቀበሉ አስገራሚ ክስተት ነው። ኒዮ ሊበራሊዝም ሸሸ ወይስ አፈገፈገ የሚለው የውይይት ርዕስ አሁን መልስ አግኝቷል። አፈግፍጎ ነበር – በጓሮ በር ድንገት ከች ብሏል።

በእርግጥ ውሳኔው በግርድፉ የሚደገፍ ነው። ሆኖም ከህወሀት ባህሪ አንጻር ፡ ኢፍትሀዊ የሆነ የኢኮኖሚ ስርዓት ከመስፈኑ ጋር ተያይዞ፡ የህግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ይህን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረጉ ከሚያመጣው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ እንዳያመዝን ነው ስጋቱ። በተለይ አየር መንገድ እንዲሁ በቀላሉ ለውጭ ባለሀብቶች ተላልፎ መሰጠቱ ላይ ብርቱ ስጋት አለኝ። ቻይና አየር መንገዱን ለመቆጣጠር ማሰፍሰፏን ላጤነ ሞገስና ክብራችን የሆነው አንድዬ ተቋም ከእጃችን እንዳያመልጥ ምን ያህል ጥናት ተደርጎበት ይሆን? አየር መንገዱ የኢኮኖሚ አውታር ብቻ አይደለም። መለያችን፡ ሰንድቃችንም ጭምር በመሆኑ በስስት የሚታይ ነው። ቻይና ይህን ተቋም ጠቀለለችው ማለት ክብራችንን በዶላር ሸጥነው እንደማለት ነው።

ውሳኔው የህወሀት ኩባንያዎችና ባለሀብቶች እነዚህን ተቋማት በእጅ አዙር ተቆጣጥረው የኢኮኖሚ የበላይነታችን በአዲስ አቅጣጫ ለማስቀጠል የተቀመረ ስልት ነው የሚለው ስጋትም ባዶ ስጋት አይደለም። ከመሬትም የሚጣል ስጋት አይሆንም። ነገር ግን በዋናነት የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በሚል የተወሰደ እርምጃ ከመሆኑ አንጻር ለውጭ ባለሀብቶች የተሰጠ እድል ይመስለኛል። እነኢፈርትማ የውጭ ምንዛሪ ቀርጥፈው የሚበሉ እንጂ የሚያስገኙ አይደሉም። ታፔላ ቀይረው በውጭ ኩባንያ ስም ሊመጡ ከቻሉም የዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርበት ይሰማኛል። ህወሀቶች ለኦጋዴኑ ነዳጅ በካናዳ ኩባንያ ስም ከጀርባ ሆነው የመጡበትን ታሪክ እናስታውሳለን። በአፋር ክልልም የፖታሺየም ማዕድን ላይ የተሰማራው በውጭ ኩባንያ ስም የተመዘገበ ቢሆንም ባለቤቶቹ የህወሀት ሰዎች ለመሆናቸው መረጃዎች ይፈነጥቃሉ።

ሆነም ቀረም ግን የዛሬው ውሳኔ የሚደገፍ ነው። ቴሌንና መብራት ሃይልን በግሉ ዘርፍ እንዲያዙ በከፊልም ይሁን በሙሉ መደረጉ ህወሀት ወደ መቃብሩ ከመውረዱ በፊት ይሆናል ተብሎ የሚታሰብ አልነበረም። ግን ሊሆን የተቃረበ ይመስላል።

የአልጀርሱ ስምምነት ህወሀትን ዋጋ ማስከፈሉ እንደማይቀር ሲነገር ነበር። በኢትዮጵያ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ባይተዋር ሆነው የህወሀት ሰዎች ብቻቸውን ጠረጴዛ ከበው የወሰኑትና ተሸናፊ የሚያደርጉ ማስረጃዎች እንዲቀርቡ የተደረገበት ክርክር ኢትዮጵያን የሚጎዳ መሆኑ በወቅቱ ምሁራን ሲጮሁበት የነበረ ጉዳይ ነው። የሆነው ያልተጠበቀ አልነበረም። ባድመ ለኤርትራ የተፈረደው ያን ጊዜ ነው። በህግ ያውም ዓለም በታዘበው ሂደት ባደመ የኤርትራ መሆኗ ተገልጾ ፍርድ ተሰጥቶበታል። ከ70 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ልጆች ህይወት ለተቀጠፈበት ጦርነት እነመለስ ዜናዊ ተሸናፊ የሚያደርግ ማስረጃና መከራከሪያ ይዘው የቀረቡ ዕለት ባድመ ሄዳለች።

ከዚያ በኋላ ያለው ቡራ ከረዩ አይነት አቋም አያዋጣም ነበር። የምዕራብ መንግስታት ወዳጅነትን በጸረ ሽብር አጋርነት መስመር በማግኘቱ የህወሀት አገዛዝ ከማዕቀብና ከውግዘት ተረፈ እንጂ አሳሪ የነበርውን ውሳኔ መቀበልና ተግባራዊ ማድረግ ነበረበት። ይህን ስል ከህግ አንጻር ያለውን የማይቀለበስ እውነት መነሻ አድርጌ ነው። እናም አልሰጥም፡ ኖርማላይዜሽን ገለመሌ የሚለው የእነ መለስ የድርቅና አካሄድ በህግ ተቀባይነት አልነበረውም።

ከ15 ዓመታት ግትርነት በኋላ የአልጀርሱን ስምምነት ያለቅድመ ሁኔታ የመቀበሉ ውሳኔ የህወሀትን ሞት በቅርበት እንድናይ ያደረገ ነው ማለት ይቻላል። ህወሀትን እዚህ ቅርቃር ውስጥ ምን ከተተው? ባድመ የትግራይ ህዝብ ጉዳይ ብቻ ነው ሲሉ በቅርቡ የሰማናቸው አንድ ባለሀብት የዛሬውን ውሳኔ ሲሰሙ ምን አሉ ይሆን?

የኢህአዴግ የአልጀርሱን ስምምነት የመቀበሉ የዛሬ ውሳኔ በሁለቱ ሀገራት መሀል የተወጠረውን ያረግባል የሚል እምነት የለኝም። ቀድሞውኑ ባድመ ምክንያት እንጂ መንስዔ አልነበረችም። ችግሩ ከባድመ በላይ ነው። ይህን ስል ጨለምተኝነት አሸንፎኝ አይደለም። የጦርነቱን አጀማመር፡ በሁለቱ ወገኖች ማለትም በሻዕቢያና በወያኔ መሀል የነበረውን ግንኙነት፡ በኋላም አይንና ናጫ የሆኑበትን ጉዳይ በሚገባ ለመረመረ ሰው ባድመ የጦርነቱ መነሻም እንዳልነበረች፡ የሰላሙም መዳረሻ እንደማትሆን በቅጡ ይገነዘባል። ከሁለቱ አንደኛው ወይም ሁለቱም አንድ ላይ ከስልጣን እስካልተወገዱ ድረስ ሰላም ይወርዳል ለማለት የሚቻል አይደለም። አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በአንድ ቃለመጠይቅ ላይ ”ድንበር ጉም ነው” ያሉበት ንግግር የሚፈነጥቀው ችግሩ ከባድመ በላይ ከፍ ያለ መሆኑን ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር ከኤርትራ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት እነመለስ ዜናዊና ሃይለማርያም ደሳለኝ በመጡበት መንገድ የሚሞክሩ ከሆነ ትርፍ የለውም።ችግሩንም የአልጀርሱን ስምምነት በመቀበል የሚፈታ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ከሆነ ተሳስተዋል። ወይም ችግሩን ለመፍታት ከልብ ቆርጠው አልተነሱም። አልያም ኤርትራን ዲፕሎማሲያዊ ቅርቃር ውስጥ ለመክተትና ጊዜያዊ ድል ለመጨበጥ በሚል ብቻ የተወሰደ እርምጃ ሊሆን ይችላል።
Mesay Mekonnen


DW (Amharic)