Abiy Ahmed: Kun Naqamtee, Mana Hidhaa Jaatoo jedhamutti!!

Abiy Ahmed: Kun Naqamtee, Mana Hidhaa Jaatoo jedhamutti!!

Mootummaan hidhamtoota siyaasaa kumoota bifa kanaan mana hidhaa tokkichatti udume hamilee maaliitiin waa’ee ittisa dhibee koronoo dubbata? Jarri kunoo, lammii Itoophiyaa mitii laata? Yoo lammii Itoophiyaa tahuullee baatan mootummaan yeroo kanatti dhala namaa akkasitti dhibee kanaaf saaxilu dhala maalii jedhama?

Yaya Beshir


ድንቁርናቸው ጠርዝ ድረስ ነው፣ ግና ስለ ስልጣኔ ልሰብኩን ይፈልጋሉ!
Yoseph Mulugeta Baba
የምዕራባዊያን የለየለት ዘረኝነት ለአፍሪካ ፍልስፍና አዲስ ነገር አይደለም፤ በዛ ምርምር ዓለም ውስጥ ያለነው እኛ በስፋት ጽፈንበታል፤ ድንቁርናቸው ጠርዝ ድረስ ነው፣ ግና ስለ ስልጣኔ ልሰብኩን ይፈልጋሉ! ከዚህ በፊት ከሳነበብኳቸው የምርምር ሥራዎቼ በጥቂቱ እነሆ!

የወጣለት ዘረኝነት በማቀንቀን ከሚታወቁ አብይ የምዕራቡ ዓለም ፈላስፎች መካካል ጊዮርግ ቪልሄልም ፍሪድሪሽ ሄጌል—Georg Wilhelm Friedrich Hegel (1770-1831)፣ ዣን ዠክ ሩሶ—Jean-Jacques Rousseau (1712-1778)፣ አማኑኤል ካንት—Immanuel Kant (1724-1804)፣ ዴቪድ ሂዩም—David Hume (1711-1776)፣ ሻርል ደ ሞንተስኪየ—Charles de Montesquieu (1689-1883) እና ካርል ማርክስ—Karl Marx(1818-1883) ይጠቀሳሉ። ለምሳሌ፡- የሄጌል ዘረኝነት በአውሮፓዊያን ፈላስፎች ዘንድ እንኳ ሳይቀር ለውይይት እንደማይቀርብና እንዲያውም የማይታወቅ ወይም በሚገባ የተደበቀ ሐቅ መሆኑን አፍሪካዊ-አሜሪካዊው ፈላስፋ ክርስቲያን ኤም ኖይገቧዎር—Christian M. Neugebauer በአጽንኦት ያሰምርበታል። የፈረንሣይ እና የጀርመን ማርክሲስቶች፣ የሄጌልን ዘረኛ አስተሳሰብ በተመለከተ አሳፋሪ ዝምታ የማሳየታቸው ጉዳይ እና ጨርሶ ዕውቅና ያለመስጠታቸው አካሄድ ደግሞ ነገሩን የባሰ (the worst) አሳሳቢ ያደርገዋል።

እዚህ ላይ በአፅንኦት ሊሰመርበት የሚገባ ነጥብ ቢኖር፣ በእያንዳንዱ ፈላስፋ ሥራ ውስጥ የተንፀባረቀው ይህ የለየለት ዘረኝነት፣ በጊዜው ከነበረው ስልተ-ምርት ጋራ በጥብቅ የተቆራኘ ነበር። በአውሮፓ እና አፍሪካ መካከል የነበረው ግንኙነት፣ እስከ 15ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ ድረስ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ እንደነበር እንግሊዛዊው የታሪክ ሊቅ ባስል ዴቪድሰን Africa: History of the Continent እና The African Genius በተሰኙ ሥራዎቹ ውስጥ በትክክል ይሞግታል። አውሮፓውያን የቢኒ—Bini፣ የዳዎም—Dahomey፣ የአሻንት—Ashanti ወ.ዘ.ተ ንቁ መንግሥታትን፣ ከሮማው ጳጳስ አሠራር፣ ሥልጣን፣ እና ተጽዕኖ ጋር በአድናቆት ያነጻጽሩ እንደነበር የምዕራቡ ዓለም የታሪክ ዘገባዎች በግልጽ ያመለክታሉ። (Basil Davidson, 1966: Passim፤ 1969፡ Passim) ይሁን እንጂ፣ በአሜሪካ የነበረው ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች ማደግ ሲጀምሩና የአፍሮ-አውሮፓውያን የንግድ ፍላጎት ከጥሬ-ዕቃ ወደ ሰው-ጉልበት ሲቀየር፣ አውሮፓውያን በሥነ-ጹሑፍ፣ በኪነ-ጥበብ እና በፍልስፍና ሥራዎቻቸው ውስጥ አፍሪካና አፍሪካዊያንን በተመለከተ ዓይነተኛና መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ማድረግ ጀመሩ። (Emmanuel C. Eze, 1997፡ 6፤ Hugh Honour, 1989፣ Passim፤ Henry Louis Gates: 1978) በተለይ የእንግሊዝ፣ የፈረንሣይ እና የጀርመን አብርሆት ፈላስፎች (French, British and German Enlightenment thinkers)፣ አፍሪካዊያን በተፈጥሮ “ከሰው ዘር በታች” ወይም “ያልሰለጠኑ ሕዝቦች” መሆናቸውን በአደባባይ ጽፎ አስተምረዋል።

በአፍሪካዊያን ሕልውና ላይ አውሮፓዊነትን በመጫን፣ ከአፍሪካዊያን ጋር ፈጽሞ የማይገናኘውን ማንነት (the Otherness of the Other) ፈጠሩ። እኛ-እነሱ በሚል ፈልስፍናዊ ተረታ-ተረት “ዲበ-አካላዊ” ልዩነት (ontological difference) ፈጥረው ኢምፔሪያሊዝምን ሕጋዊ አደረጉ። ይህንን የአስተሳሰብ ሽርሙጥና በማቀንቀን ከሚታወቁ ምዕራባዊያን ፈላስፎች መካከል ለአብነት ሦስቱን ብቻ እንጥቀስ፡-
(ሀ) በአንድ ወቅት በእንግሊዝ ቅኝ-ግዛት ቢሮ (British Colonial Office) ውስጥ ያገለገለው ዴቪድ ሂዩም—David Hume፤ አውሮፓውያን (ነጮች) በዓይነት (qualitatively) ከአፍሪካዊያን (ጥቁሮች) የተሻሉ መሆናቸውን “On national character” በተሰኘ ሥራው ውስጥ በግልጽ አስፍሯል። ሂዩም እንደሚተርተው፣ ይህ “ዲበ-አካላዊ” ልዩነት (ontological difference) አቋም ሲሆን፣ በተፈጥሮ ላይ የተመሠረተ ነው።

(ለ) ታላቁ ፈላስፋ እየተባለ የሚሞካሸው አማኑኤል ካንት—Immanuel Kant በበኩሉ፣ ይህንን “ዲበ-አካላዊ” ልዩነት ይበልጥ በማጉላት፣ ነጭ የቆዳ ቀለም ያላቸው አውሮፓዊያን፣ ከሌሎች የሰው ዘሮች (ማለትም ቢጫ፣ ጥቁር እና ቀይ የቆዳ ቀለም ካላቸው ሕዝቦች) በአይነት የተሻሉ መሆናቸውን “Observations On the Feelings of the Beautiful and Sublime” በተሰኘ ድርሰቱ ውስጥ ፍጹም ሕፃናዊ ማብራሪያ አቅርበዋል። ይህ ፈላስፋ፣ የቆዳ ቀለምን ብቻ እንደ መስፈርት ተጠቅሞ የሰው ልጅ ዘርን በአራት ደረጃ ከፋፍሏቸዋል፡- ነጭ የቆዳ ቀለም ያላቸው አውሮፓዊያን 1ኛ ደረጃ፣ ቀይ የቆዳ ቀለም ያላቸው አሜሪካዊንያን 2ኛ ደረጃ፣ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው አፍሪካዊያን 3ኛ ደረጃ፣ ቢጫ የቆዳ ቀለም ያላቸው ህንዳዊያን ደግሞ 4ኛ ደረጃ በማለት በሰው ልጅ ህልውና ላይ አላግጧል።(Emmanuel C. Eze, 1994፡ 201-141)

እንደ ካንት የተረቶች ሁሉ ተረት ከሆነ፣ አንድ ሰው ከራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ ጥቁር የሆነ እንደሆነ፣ ደደብ እንጂ ምክንያዊ ፍጡር ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዳ ደግሞ፣ እላይ የተጠቀሰውን የዴቪድ ሂዩም ሥራን እንደ ማስረጃ ያቀርባል። እርግጥ ነው፣ በወቅቱ ሥነ-ዕውቀትን በሚመለከት በምክንያታዊነትና (rationalism) እና በዳሳሽነት (empiricism) መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለማስታረቅ ካንት ሌላ የዕውቀት ንድፈ ሐሳብ አመንጭቷል። ይህንን አለመግባባት ለመፍታትም Critique of Pure Reason የተሰኘውን ፍልስፍናዊ ሥራውን ለዓለም አበረክተዋል፤ ዝናንም አትርፎበታል። ይሁን እንጂ፣ ካንት የሰው ልጅ “ሕልውና”ን በተመለከተ ከድንጋይ ዘመን የተሻለ አስተሳሰብ አልነበረውም።

(ሐ) የቅኝ-አገዛዝ ጽንሰ ሐሳብን በማስፋፋትና የጀርመን ቅኝ-ገዠዎችን በማነሳሳት በኩል ካየነው፣ ጊዮርግ ቪልሄልም ፍሪድሪሽ ሄጌልን—Georg Wilhelm Friedrich Hegel የሚስተካከል ፈላስፋ አልነበረም። በርከት ያሉ የብሉይ ፍልስፍናዊ ሥራዎች በጀርመንኛ ቋንቋ የተጻፉ ነበሩ። አሻሚ ትርጉም ተጠቅሞ በጥቅሶቹ ላይ ያለ-ምክንያት ትችት ከመሰንዘር፣ አስቀድሞ በጀርመንኛ ቋንቋ ችሎታ እርግጠኛ መሆን ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ይህንን እውነታ በትክክል የተገነዘበው ክርስቲያን ኤም ኖይገቧዎር (Christian M. Neugebauer, 1991፡ 248-249)፣ የሄጌልን ፍልስፍናዊ ሥራዎች ለማብራራትና ለመተቸት ዋናውን ምንጭ (original source) ተጠቅመዋል። ኖይገቧዎር እንደሚሞግተው፣ አፍሪካ ውስጥ የፍልስፍና እና የባሕልን ጥያቄ በተመለከተ፣ የሄገልን ፍልስፍናዊ ክርክሮችን በሰባት አንኳር አንኳር ነጥቦች ማጠቃለል ይቻላል፡- የአፍሪካ ቆሞ-ቀርነት (staticity of Africa)፣ የአፍሪካ ኃላ-ቀርነት (prmitivity of Africa)፣ አፍሪካ የዓለም አካል አይደለችም (Africa is without history)፣ የአፍሪካ ስድነት (profligacy of Africa)፣ የአፍሪካ ጨካኝነት (savageness of Africa)፣ አፍሪካ የተሟላ ፈልስፍና የላትም (Africa has no proper philosophy) እና አፍሪካን አንድ-ወጥ የሆነ ባህል ያላት አህጉር አድርጎ መመልከት (Africa is regarded as a cultural homogenous continent) የሚሉ ናቸው።

ሰሜን ተባለ ደቡብ፣ ሄጌልም ሆነ ለሎች ምዕራባዊያን ጠበብት፤ የአፍሪካን ማንነት አተያይ መረዳት ቀርቶ፣ የአፍሪካን ስልጣኔን በተመለከተ ምንም መረጃ እንዳልነበራቸው የፍልስፍና ሥራዎቻቸው ይመሰክራሉ። ለምሳሌ፣ ክርስቲያን ኤም ኖይገቧዎር እንደሚሞግተው፣ የመጀመሪያ ጥያቄ መሆን ያለበት፤ “የሄጌል ዋና ዋና የመረጃ ምንጮች ምን ምን ናቸው?” የሚል ነው። ይህንን ጥያቄ ኖይገቧዎር ራሱ በትክክል መልሶታል፤ መልሱም አንድና አንድ ብቻ ነው—እርሱም ድንቁርና ነው።
ስለዚህ፣ ሄጌል በፍልስፍና ስም ስለ አፍሪካና አፍሪካዊያን የደረሰው በትክክል ተረት እንጂ፣ በእውነተኛ መረጃ ምንጮች ላይ የተመሠረተ አይደለም።

ስለዚህ፣ ከላይ ለአብነት የጠቀስናቸው ፍልስፍናዊ ሥራዎች፣ ከአፍሪካ ሥነ-ሰባዊም ሆነ ታሪካዊ እውነቶች ጋራ ፈጽሞ የሚጣጣሙ አይደሉም። ምዕራባዊያን ፈላስፎች፣ የአፍሪካዊያንን የሥነ-ልቡና አቀራረጽ፣ የራስ-አረዳድ/አተያይ ቅንጣት ታእል እውቀት ሳይኖራቸው የለየለት ድንቁርናቸውን በፍልስፍና ስም በአደባባይ ማንጸባረቅ፣ ምሑራዊ ውስልትና ያሰኛል። እዚህ ላይ አንድ ነገር በአጽንኦት ሊሰመርበት ይገባል፤ የእነዚህ ጠበብት ፍልስፍና ድርሳናት ማዕከል ያደረጉት ፍልስፍናን ሳይሆን በአፍሪካዊነት ማንነት በኩል ያላለፈ አውሮፓዊነትን ነው።