Abdi Iley demands the resignation of not only Lamma Magarsa, Oromia

via Addisu Arega Kitessa – #OromiaCommunicationBureau

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል ከኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄራዊ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸዉ የቦረና፣ ጉጂ፣ ባሌ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች የኢትዮጵያ ሶማሌ ልዩ ፖሊስ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በሚያደርሰዉ ጥቃት የተነሳ ከአምና ጀምሮ ሰላም እንዳልነበር ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በ2009 የበጀት ከአምስቱ ዞኖች የግጭት አካባቢዎች 416,807 የሚሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች ከልዩ ፖሊስ ጥቃት በመሸሽ ህይወታቸዉን ለማትረፍ ሲሉ ቀየያቸዉን ጥለዉ ተፈናቅለዋል፡፡ ሠሞኑን በተከሰተ ችግርም ከ55,000 በላይ የሚሆኑ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ተፈናቅለዉ በሀረር፣ ጭናክሰን፣ ሚኤሶ እና ባቢሌ ከተሞች በድንኳን ተጠልለዉ ይገኛሉ፡፡

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሞኑን የተፈጠረዉ አሳዛኝ ሁኔታ እንዲረጋጋ፣ በዚህ ፈታኝ ወቅት የሀገራችን አንድነት እንዳይናጋ፣ ከምንም በላይ የህዝቦች በወንድማማችነት እና በፍቅር ላይ የተመሰረተ መስተጋብር እንዳይበላሽ ሃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከምንም በላይ በክልላችን የሚኖሩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ላይ ምንም ችግር እንዳደርስባቸዉ ለማድረግ ዉጤታማ ስራ ተሰርቷል፡፡ የኦሮሞ ተወላጆች ከኢትዮጵያ ሶማሌ ተፈናቀሉ በሚል ሂሳብ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የሶማሌ ተወላጆችን እንዲፈናቀሉ ማሰብ ተሸናፊነትና ጸረ ህዝብነት ነዉ፡፡ በመሆኑም በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች እንዳይፈናቀሉ ለማድረግ ከተሰራዉ ዉጤታማ ስራ ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ሊያጠናክሩ የሚችሉ የሰላም እና የወንድማማችነት ኮንፈረንሶች በሁሉም የኦሮሚያ ከተሞች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኦሮሚያ ክልል የሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቤት ናት፡፡ ሰሞኑን በተፈጠረ ችግር ሆነ በሌላ ሰበብ በክልላችን አንድም ኢትዮጵያዊ መፈናቀል ሊታሰብ አይችልም፡፡ ይልቁንም በዚህ አጋጣሚ በምንፈጥራቸዉ መድረኮች የህዝቦቻንን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር እንሰራለን፡፡ ስለሆነም በክልላችን ነዋሪ የሆናችሁ የሀገራችን ህዝቦች በተለመደዉ ፍቅር እና አንድነት ህብረታችሁን አጠንክራችሁ እንድትኖሩ፣ በዚህ አጋጣሚ በህዝቦች መካከል በመግባት ቁርሾ በመፍጠር የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ አካላትን እንድታጋልጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በሌላ በኩል ተፈናቃይ ወንድሞቻችንን መደገፍ ጊዜ የማይሰጠዉ እና የሁላችንም ጉዳይ በመሆኑ የኦሮሞ ህዝብ ወዳጆች የሆናችሁ በሙሉ በሚከተሉት ባንኮች ድጋፍ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡
የኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ የሂሳብ ቁጥር (1000025884888)
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር (1000219234256)
ከሀገር ዉጪ ነዋሪ ለሆናችሁ
Cooperative Bank Of Oromia S.C, Swift Code CBORETAA account name, Oromia Risk mgt Commission Displaced people rehabilitation Fund ( Account Number 1000025884888), Finfinne Branch በኩል ድጋፍ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡

ሠላም ለሀገራችን ኢትዮጵያ !
የህዝቦች ወንድማማችነት ለዘለዓለም ይኑር!