12 የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላት ጉጂ ውስጥ በታጣቂዎች ተገደሉ

12 የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላት ጉጂ ውስጥ በታጣቂዎች ተገደሉ

የክልሉ መንግሥት የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላትን ባስመረቀበት ወቅት OROMIA COMMUNICATION BUREAU

(bbcamharic)–በጉጂ ዞን አስራ ሁለት የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት በታጣቂዎች መገደላቸውን አንድ የዞኑ ባለስጣታን ለቢቢሲ ገለጹ።

የጉጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ማሊቻ ዲቃ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በግጭቱ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በታጣቂዎቹና በክልሉ ልዩ ኃይል አባላት መካከል ከሁለት ሳምንት በፊት በነበረ ግጭት ነው 12ቱ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላት በታጣቂዎቹ መገደላቸውን የተናገሩት።

በደቡብ አሮሚያ ጉጂ ዞን በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በቀድሞ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባል የነበሩና በአሁን ወቅት በጫካ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ባሉ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እየተካሄደ መሆኑን ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

“በጉሚ ኤልደሎ ወረዳ ግጭት ተከስቶ 12 የኦሮሚያ የልዩ ኃይል የፖሊስ አባላት ተገድለዋል። የሞቱት ቁጥራቸው ስንት እንደሆኑ ባናውቅም ከታጣቂዎቹም የተገሉ አሉ” ሲሉ አቶ ማሊቻ ዲቃ ጉዳቱ በሁለቱም በኩል መሆኑን አመልከተዋል።

ራሳቸውን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ብለው የሚጠሩት ታጣቂዎች በምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ ዞኖች እና በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ ዞን ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱና መንግሥትም ታጣቂ ቡድኖቹን ለመቆጣጠር እርምጃ ሲወስድ መቆየቱ ይታወቃል።

ታጣቂው ቡድን በሰላማዊው የፖለቲካ መድረክ ላይ ለመሳተፍ ከተስማማው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር ጋር እራሳን የለየ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ‘ኦነግ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል የለውም’ ሲሉ በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።

በጉጂ ዞን ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ኃይል በአከባቢው ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ አቶ ማሊቻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የአካባቢው ነዋሪዎች የእለት ከእለት ሕይወታቸውን መቀጠል አልቻሉም። ገበሬው ማረስ አልቻለም፤ አርብቶ አደሩም ከብቱን ማርባት አልቻለም። ‘የመንግሥት ደጋፊ ናችሁ’ እየተባሉ ታፍነው የተወሰዱ ሰዎችም አሉ። በስልክ ማስፈራሪያ የደረሳቸውም አሉ” ይላሉ።

የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር በዞኑ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና መደበኛ ፖሊሶች ተሰማርተው ይገኛሉ።

በተለይ በዞኑ በሚገኙት ሰባ በሩ፣ በጎሮ ዶላ እና ሻኪሶ ወረዳ ግጭቶች እንደቀጠሉ የሚናገሩት ምክትል አስተዳዳሪው፤ “በሁለቱም በኩል ሰው ይሞታል። በታጣቂዎች በኩል ምን ያክል ሰው እንደሞተ ግን የምናውቀው ነገር የለም” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የአገር ሽማግሌዎች እና አባ ገዳዎችም ታጣቂዎቹ ነፍጥ ጥለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጠይቀዋቸው እንደነበረ የሚያስታውሱት አቶ ማሊቻ፤ “ከዚህ በፊት እጃቸውን የሰጡ አሉ። አሁን ግን በመነጋገር የሚመለሱበት ደረጃ ላይ አይደሉም” ይላሉ።

በቢሲ ከሦስት ወራት በፊት በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ ስላለው የጸጥታ ችግር ከምክትል ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር።

በወቅቱ ጀነራል ብርሃኑ መንግሥት በወሰደው ኦፕሬሽን “በአካባቢ የነበሩ ኃይሎች ላይ እርምጃ ተወስዶ አከባቢው ነጻ ወጥቷል” ብለው ነበር።

“በምዕራብ እና ምስራቅ ጉጂ ሕዝቡን እያስገደዱ ቡና እያስመጡ ወደ ኬንያ አሻግረው ይሸጡ ነበር። ሕዝብ ሲንገላታ ቆይቷል። ይህ የሆነው ደግሞ መንግሥት ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት የኃይል እርምጃ ሳይወስድ በመቅረቱ ነበር። ኦፕሬሽን ካካሄድን በኋላ ሁለቱም ጉጂዎች ነጻ ወጥቷል። አሁን መደበቂያ ሲያጡ ወደ ሶሎሎ [ኬንያ እና ኢትዮጵያ ድንበር አዋሳኝ] ሸሽተዋል” በማለት ተናግረው ነበር።