ፖለቲካዊ ዓላማ ያነገቡ ጫናዎች ከስራችን አይገቱንም! ከኦ.ኤም.ኤን የተሰጠ መግለጫ

ፖለቲካዊ ዓላማ ያነገቡ ጫናዎች ከስራችን አይገቱንም!

ከኦ.ኤም.ኤን የተሰጠ መግለጫ

ውድ አድማጭ ተመልካቾቻችን

ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ.ኤም.ኤን) የህዝቦችና ብሄር ብሄረሰቦች ሁነኛ ዓይንና ጆሮ ሆኖ በሀቅ እያገለገለ የሚገኝ ሚዲያ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚዲያው ላይ እያተካሄደ የሚገኘውን ፈርጀ ብዙ ወከባና ጫናን አስመልክቶ አንዳንድ እውነታዎችን ለአድማጭ ተመልካቾቻችን ማስገንዘብ የሚዲያው ማኔጅመንት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቷል፡፡ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ባለፉት ስድስት ዓመታት ኦ.ኤም.ኤን በሀገራችን ፍትሐዊ ስርዓት ነግሶ፤ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ ድምጽ ላጡት ድምጽ በመሆን እጅግ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ በሀገራችን ለመጣው ለውጥም እንደ ሚዲያ ግንባር ቀደም ሚናን ተጫውቷል፡፡ ከሰኔ 2010 ጀምሮ መንግሰት በውጪ ለሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ ኦ.ኤም.ኤን ወደ ሀገር ገብቶ አስፈላጊውን የሙያና የሰራ ፈቃድ በማግኘት የሳታላይት ቴለቪዥን ስርጭትና የሚዲያ ሰራዎችን አጠናክሮ እየሰራ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በሀገራችን እየታየ የሚገኘው ሁለንተናዊ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሽግግር አስተማማኝ መሰረት ላይ እንዲገነባና እንዲሳካ እንደ ሚዲያ ተቋም የበኩሉን ሚና እየተወጣ ቆይቷል፡፡ እየተወጣም ይገኛል፡፡ ይሁንና ከጥቅምት 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የሚደርስብን ጫና ከጊዜ ወደ እየበረታ መምጣቱን አድማጭ ተመልካቾቻን የሚገነዘቡት ጉደይ ነው፡፡

በብሮድካስት ባለስልጣን አማካኝነት የደረሱን ቅሬታዎችን ምላሾቻችን

1ኛ. የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሰመልክቶ ባሰራጨነው ዶክውሜንትሪ ዘገባ አስመልክቶ የመንግስት ባለስልጣን በሆኑ ግለሰብ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን (ኢብባ) በኩል የቀረበብን ቅሬታ ሲሆን፤ ዘጋቢ ፊልሙ ሰብሃዊ መብት ረገጣን አስመልክቶ የቀረበ ሲሆን፤ በይዘቱ አንድ የመንግሰት ባለስልጣን በድርጊቱ ውስጥ የነበራቸውን ተሳትፎ አስመልክቶ በዓይን እማኞች መረጃ ሰብስበን፤ በቦታው ተገኝት ትክክለኛነቱን አገራግጠን አጥጋቢ ሆነ ምላሽ በባለስልጠኑ በኩል አቅርበናል፡ በኢብባ በኩል ሲካሄድ የነበረው ክርክርም በዚያው እንዲገታ ሆኗል፡፡

2ኛ. የአገው፤ ቅማንትና በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስመልክቶ ባቀረብናቸው ዘገባዎች ላይ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግሰት ኮሙዩንኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ቅሬታ ቀርቦብ ነበር፡፡ እነዚህን ብሄረሰቦች አስመልክቶ ያሰራጨናቸው ዘገባዎች ትክክለኛነትና ፍትሐዊነት አስረድተን በሚገባ ምላሽ አቅርበናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንደ ሚዲያ የበለጠ የሁሉንም ሓሳብ ፤ አስተያየትና ቅሬታ ለማስተናገድ ባለን ፍላጎት በዘገባዎቹ መብቴ ተነክቷል የሚለው ወገን/ የአማራ ክልል/ ቀርቦ አስፈላጊውን ለአድማጭ ተመልካቾች እንዲያርብ በጽሁፍ ጥሪ አቅርበናል፡፡ ይሁን እንጂ ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ቀርቦ ምላሽ የሚሰጥ ወገን ሳይገኝ ቀርቷል፡፡

3ኛ. በአማራ ክልል በሚገኙት ዮኒቪርሲቲዎች በሚማሩ የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የደረሰውን ችግር አስመልክቶ ያቀረብናቸው ዘገባዎችን አስመልከቶ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር የቀረበብን ቅሬታ ነበር፡፡ የሚገርመው ይሀ በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የደረሰው በድል ትልቅ ሀገራዊ አጅንዳ ሆኖ እያለና የተለያዩ ኮንፈራንሶች ሲካሄደቡት የነበረ መሆኑ እየታወቀ ኦ.ኤም.ኤን ለምን ሀቁን ዘገበ በሚል ክስ ቀርቦብናል፡፡ ይህም ቅሬታ ከላይ ከቀረቡት ጋር ተመሳሳይ እንደመሆኑ መጠን፤ ያቀረብናቸው ዘገባዎች በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረቱና ምንጫቸውም የተረጋገጠ መሆኑን ያለንን መረጃ በማቅረብ አጥጋቢ ምላሽ ሰጥተናል፡፡ ከዚህም አልፎ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር አስመልክቶ በሚንስቴር መ/ቤቱ በኩል ያለውን መረጃና አስተያየት ቀርበው ለህዝቡ እንዲያሰረዱ እንደሚዲያ ዕድል ሰጥተናቸው ነበር፡፡ በተወካያቸው በኩል ከአንዲም ሁለቴ በኦ.ኤም.ኤን ቴለቪዥን ቀርበው መረጃና አስተያየታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

4ኛ. የመጨረሻው መምህር ኃይለ ሚካኤል ታደሰ የተባሉ ግለሰብ በፍቼና ገርባ ጉራቻ ከተሞች በኦፌኮ ሰብሰባ ላይ ያቀረቡትና በቀጥታ ስርጭት የተላለፈ ንግግር ነው፡፡ ይህን አስመልክቶ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን ጴጥሮሳዊያን የቤተክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ህብረት በተሰኘ አካል ያቀረበብን ክስ ነበር፡፡ ንግግሩ በቀጥታ ስርጭት የተላለፈና የኦ.ኤም.ኤን ኤዲቶርያልና ይዘት የሚወክል እንዳልሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡ከስሱም የቀረበብን የሚዲያ፤ የፖርቲና የግለሰብ ሚና ሳይለይ ነው፡፡ ለቀረበብን ለዚህ ክስም የተብራራ ምላሽ ሰጥተናል፡፡ በሐቅና ማስረጃ ላይ ተመሰርተን የሰጠነው መልስ ወደ ጎን በመተው የብሮድካስት ባለስልጣን ባልጠበቅነው ሁኔታ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አድርሶናል፡፡ ማስጠንቀቂያው ፖለቲካዊ ዓላማ እንዳለው የሚያመላክተን ደብዳቤው በቀጥታ ለማይመለከታቸው የመንግሰት አስፈጻሚ አካላት ኮፒ ተደርጎ መላኩ ነበር፡፡ ይህም የሚደረግብን ጫናና ማስፈራሪያ እየበረታ ስለመሆኑ በግልጽ አመላካች ነው፡፡ ከዚህ ክስ አንጻርም እንደ ሚዲያ የተላለፈብን ውሳኔ አግባብነት ሰለለሌው ለሚመለከተው አካል ይግባኝ አቅርበናል፡፡ ባልጠበቅነው ሁናቴ አካሄዳቸውን ቀይረው የተጠቀሰውን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ባለፈው ወር እስኪጽፉብን ድረስ ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር የነበረን የስራ ግንኝነት መልካም ነበር፡፡ እንዲያውም በቅርቡ የባለስልጣኑን ከፍተኛ አመራሮችና ኤክስፐርቶችን የያዘ የልዑካን ቡድን ከስትዲዮያችን ድረስ በመምጣት ጉብኝት አድርገው፤ ከሚዲያው አመራር ጋር የትብብርና የመግባባት መንፈስ በተሞላበት ሁናቴ ምክክር አድርገው አስፈላጊ ምክር ለግስውን ከተመለሱ በኃላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፖለቲካዊ አንድምታ የተጫነው ማስጠንቀቂያ ሲያደርሱን ግርምትን ጭሮብናል፡፡

ከብሮድካስት ባለስልጣን ስርጭታችንን አስመልክቶ ግብረ መልሶች በተከታታይ ሲደርሱን የቆዩ ሲሆን፤ ግብረ መልሶቹ ጠቃሚ ጉዳዮች እንዳሉት ተገንዝበናል፡፡ ይሁንና አሻሚና አከራካሪ ጉዳዮችን እንደ ጣቢያው ውስንነት አድርጎ አቅርቧል፡፡ ለምሳሌ ከገለልተኝነትና ከሃሳብ ብዙሓነት አንጻር እንደ ውስንነት ከቀረቡብን መካከል በእሬቻ ሰሞን የተጠቀምናቸው ባንድራዎች የአባ ገዳ እና የኦሮሞ ህዝብ ትግል መገለጫ የሆነው ባንድራ ሲሆኑ የአንድ ፖርቲ ባንድራ ብቻ የተጠቃመን አስመስሎ ቀርቦብናል፡፡ ከሐሳብ ብዙሓነት አንጻርም አንድ ዓይነት ሐሳብና የፖለቲካ ወገንተኝነት የሚያንጸባርቁ፤ በሀገር አንድነትና ሰላም ላይ ያተኮሩ ዘገባዎች ውስንነት በሚል ቀርቦብናል፡፡ ይሁንና ከሚዲያው ተጨባጭ ተግባራት አንጻር ኦ.ኤም.ኤን በተለያዩ ከ5 ባለይ ቋንዎች የተለያዩ ወገኖች ሐሳብና አመለካከት የሚያቀርብ ሚዲያ መሆኑን ማንም ልክድ አይችልም፡፡ የመጀመሪያው ግብረ መልሱ ሞኒተር በተደረገበት ሰሞን እሬቻ የስላምና የፍቅር በዓል መሆኑን የሚግልጹ ቃለምልልሶች፤ ትንታኔዎችና ዘገባዎች በስፋት ሲቀርቡ ነበር፡፡ ምናልባትም ይህን መሰል ግብረ መልሶች ጣቢያው ላይ ዛሬ በይፋ እየተካደ ላለው ዘመቻ እንደ ግብሃት ለመጠቀም ታስቦ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ አለን፡፡

የሰሞኑ ውክቢያ፤ ጫናና ዘመቻ

በባለፈው እሁድ ማርች 8 አስመልክቶ በነበረው ቀጥታ ሰርጭት ኦ.ኤም.ኤንም ይቅርታ በጠየቀበትና በቀጥታ ስርጭት በተላለፈው የአንዲት ልጅ የግል አስተያየት ምክንያት በማድረግ ከሰሞኑ እየደረሰብን ያለው ውክቢያ፤ ዘመቻና ጫና አድማጭ ተመልካቾቻችን በአጽንኦት እየተከታተሉ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ይህ ክስተት ኦ.ኤም.ኤንን ለማጥፋት ጊዜውና አጋጣሚው አሁን ነው ብለው የተነሱ የተለያዩ ኃይሎች ግንባር ፈጥረው እየተረባረቡ መሆናቸውን በሚገባ የተስተዋለበት ነው፡፡ ጉዳዩ የሙያ ሳይሆን የፖለቲካ አካሄድና ዓላማ መያዙንም የሚያመላክቱ ሁኔታዎች ተገንዝበናል፡፡ አንዱ አመላካች ጉዳይ የሚዲያ ሞኒቴርንግና ሪጉላቶሪ በቀጥታ የሚመለከተው የብሮድካስት ባለስልጣን በክስተቱ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት ሳይሰጥ የመንግሰት አስፈጻሚ አካላት (በተለይም ከጠ/ሚንስትር ጽ/ቤት ባለስልጣናት አቶ ንጉሱ ጥላሁንና ዲ/ን ዳንኤል ክብረት) ትዕዛዝ መሰል መልዕክትን በ30/06/2012 በፋና ብሮድካስትንግ ኮርፖሬት በኩል ማስራጨቱ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፋናና መሰል ሚዲያዎች ኦ.ኤም.ኤንን በተለይ ነጥለው የሚዲያ ዘመቻ መክፈታቸው በእጅጉ የሚያስተዛዝብ ጉዳይ ነው፡፡ በጣም አስገራሚው ጉዳይ ኦ.ኤም.ኤንን በወገንተኝነት የሚወቅሱ እነዚህ ሚዲያዎች፤ የተፈጠረውን ክስተት አስመልክቶ ሰፊ ትነታኔ፤ ቃለ-ምልልስ፤ ቮክስ ፖፒ ስሰሩ ጉዳዩ በዋንኝነት እንደሚመለከተው አካል የኦ.ኤም.ኤንን አስተያየትና ምላሽ እንኳን ለማካተት አልፈለጉም፡፡ እንደ ኦ.ኤም.ኤን የምንከተለው የሙያ መርሆዎችና አሰራር ገድቦን፤ በሌሎች ሚዲያዎች ጉድለት ላይ ማነጣጠር ሰለማንፈልግ እንጂ ሀገርቷን ወደ አደገኛ ቀውስና እልቅት ልወስዳት የሚችል ዘገባ፤ በተወሰነ ብሄር ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ዘመቻ፤ ዓይን ያወጣ ሐሰተኛ ዘገባዎችን በመፈብረክና በማስራጭት ሀገርና ዓለም የሚያውቃቸው የሚዲያ ተቋማት እንዳሉ በሚገባ እንገነዘባለን፡፡ ሁሉም ሊገነዘበው የሚገባው ሐቅ ግን ኦ.ኤም.ኤን የትግል ሚዲያ ሆኖ የተፈጠረ፤ አሁን ላይ ደግሞ እንደ አንድ ነጻ ሚዲያ ( independent media) ራሱን በሙያና ሙያዊ አሰራሮች መልሶ በማዋቀርና በማደራጀት (by enhancing its professionalism) ለሚዲያና ሀሳብ ነጻነት፤ ለዴሞክራሲና ፍትህ በቁርጠኝነት የቆመ፤ አምባገነኖችን በሚዲያ በመታገል አመርቂ ሰኬትን ያስመዘገበ የሚዲያ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ለውክቢያና ፖለቲካዊ ጫና ሳይንበረከክ እንደ ነጻ ሚዲያ ህግና ህግን ተከትለን ከመስራት ወደኃላ አንመለስም፡፡ እንቀጥላለን፡፡

የትኩረት አቅጣጫችን

ኦ.ኤም.ኤን ለምን በኦሮሞ ህዘብ ጉዳይ/ አንድ ክልል ላይ በተለይ አትኩሮት ሰጥቶ ይሰራል? የሚል ጥያቄ አዘል ቅሬታ የሚያቀርቡብን እንዳሉ እንረዳለን፡፡ ይህ በባለስልጣኑ በኩል የሚደርሰን ግብረ መልስንም ይጨምራል፡፡ እንደ ኦ.ኤም.ኤን የማንክደው ሀቅ አለ፡፡ ሚዲያው በቀዳሚነት የተቋቋመው የኦሮሞ ህዝብ ያጋጠመውን ኢፍትሐዊ የሆነ የሚዲያ ሚዛን ለመቀየር ነው፡፡ ለህዝቡ ሐቀኛ ዓይንና ጆሮ ለመሆን ነው፡፡ ይህ ፍትሐዊ ዓላማ፤ በለሌሎችም በጭቆና ስር በነበሩ የዓለም ማህበረስብ ዘንድ የሚታወቅ አሰራር ነው፡፡ ይሁንና የኦሮሞን ህዝብ ማዕከል አድርገን እንሰራለን ስንል፤ ለሌሎች ህዝቦች/ብሄሮች ዕድል አንሰጥም ማለታችን እንዳልሆነ ስራችን እራሱ ይመሰክርልናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኦ.ኤም.ኤን በአፋን ኦሮሞ፤ በአማርኛ፤ በአፈ-ሶማሌ፤ በወላይትኛ፤ ሲዳማ፤ አዲያ እና ሌሎችም የሚሰራጭ ብቸኛ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡ ይህም ለህዝቦች የሃሳብ ነጻነትና ፍትሐዊ የሚዲያ ሸፋን ካለን ቁርጠኛ አቋም ይመነጫል፡፡ በነገራችን ላይ- ብሮድካስት ባለስልጣን ለዚህ አድናቆቱን በተደጋጋሚ በግብረ መልስ ማድረሱን ልብ ይሏል፡፡ አስገራሚው ነገር፤ ከህዝብ በሚሰበሰበው ግብር የሚተዳደሩት መንግስታዊ ሚዲያዎች እንኳን እንደ ኦ.ኤም.ኤን በተለያዩ ቋንቋዎች ስርጭት እንደሌላቸው እየታወቀ ኦ.ኤም.ኤንን ልሙጥና ጽንፈኛ የአንድ ብሄር ብቻ ድምጽ የሆነ ሚዲያ አስመስሎ ለማቅረብ ዘወትር የሚዳዳቸው ኃይሎችን በስፋት ታዝበናል፡፡ በአንድ አማርኛ ቋንቋ ብቻ፤ ተመሳሳይ ሃሳብና የፖለቲካ አመለካከት የሚያሰራጩ ሚዲያዎች በሞሉባት ሀገር ሐቀኛ የብዙሓን ሚዲያ የሆነው ኦ.ኤም.ኤን ላይ ጫናና ውክቢያ መብዛቱን ሲንመለከት ጉዳዩ የሙያ ሳይሆን የፖለቲካ ዘመቻ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ቲፕ ለሚመለከታቸው አካላት መስጠት እንፈልጋለን፡፡ ይሔውም ከጋዜጠኝነት ሙያና ከሚዲያ አሰራር አንጻር ያለን ብቃትና ልምድ ከሌሎች በሀገርቷ ከሚገኙት ሚዲያዎች የተሻለ እንጂ ያነሰ እንዳልሆነ እኛም የምናውቀው፣ አድማጭ ተመልካቾቻችንም የሚመሰክሩትና ከሳሾቻችንም የሚረዱት ሃቅ ነው፡፡ ይህንን መገንዘብ የሚፈልግ አካል በተግባር ካሉት ሚዲያዎች አንጻር በሐቀኝነት ስራዎቻችንን መዝኖ መረዳት ይችላል፡፡ በራችን ለሁሉም ክፍት ነው፡፡

መደምደሚያ

ለአድማጭ ተመልካቾቻችን ቃል የምንገባው ለሃሳብ ነጻነት፤ ለሃሳብ ብዝሃነት፤ ለዴሞከራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ለህዝቦች ድምጽ ከመሆን አንጻር መቼም የማይናወጥ አቋምና ዓላማ አለን፡፡ ታላቁ የኦሮሞ ህዝብ በነጻ ሚዲያ እጦትና ሚዛን መዛባት ያለው ሐቅ እንዲሽረሽርና ለአምባገነናዊ ስርዓት የተመቸ ሁኔታ እንዲፈጠር ዕድል አንሰጥም፡፡ ላለፉት ሰድስት ዓመታት በተግባር እንዳሳየነው ለመረጃና ሐሳብ ነጻነት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ከፍለን ህጋዊ በሆነ መንገድ የሚዲያ ስራችንን እንቀጥላለን፡፡ ህዝባችንም ይህንን በሚገባ ተገንዝቦ እንደተለመደው የራሱን ሚዲያ በቅርበት እንዲከታተልና እንዲያጠናክር ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ለመንግሰት አካላት ያለን መልዕክት የተስፋ ጭላንጭል የታየበትን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ወደ ኃላ ለመመለስና የሚዲያ፤ ሐሳብና የፖለቲካ አመለካከት አፈና መልሶ ማስፈን መሞከር ከእንግዲህ ለማንም አይጠቅምም፡፡የሚሻለው የታየውን በጎ ጅምር በትብብር አጎልብቶ መቀጠል ነው፡፡ በፖለቲካዊ ጫናና ሴራ እንደ ኦ.ኤም.ኤን ያሉትን ከፍተኛ ህዝባዊ መሰረት ያላቸውን የሚዲያ ተቋማት ከስራ ውጪ ለማድረግ መስራት ለማንም አይበጅም፡፡ ይህ በተደጋጋሚ ተሞክሮ በተደጋጋሚ የወደቀ ሰልት መልሶ መሞከር ትርፉ ልፋት ነው፡፡
ለሚዲያ ተቋማትም የሚዲያ ነጻነትንና የሐሳብ ብዝሃነትን የበለጠ ለማጠናከር በጋራ ለጋራ ጥቅም መስራት እንጂ አንድን ሚዲያ ለብቻ ነጥሎ ለመምታት መተባበር ሁሉንም የሚያጠፋ ሁኔታ እንደሚፈጥር ማስገንዘብ እንፈልጋለን፡፡

በመጨረሻም መንግስት OMN ላይ እያደረገ ያለውን ፖለቲካዊ ጫና በማውገዝ ጭምር ከጎናችን በመቆም ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ መብትና ለነጻው ሚዲያ ኢንዱስትሪ እድገት አጋርነታቹን ላሳያቹ ሚዲያዎች ሁሉ የOMN ማኔጅመንት ምስጋናውን ያቀርባል።

የኦ.ኤም.ኤን ማኔጅመንት
መጋቢት 2012
ፊንፊኔ፤ ኦሮሚያ ኢትዮጵያ