ፍትሓዊና አካታች ያልሆነ ምርጫ ዴሞክራሲን ሊያዋልድ አይችልም!

ፍትሓዊና አካታች ያልሆነ ምርጫ ዴሞክራሲን ሊያዋልድ አይችልም!

(ወቅታዊ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክቶ ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌከ) የተሰጠ መግለጫ)
ፓርቲያችን፤ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ላለፉት ሦስት ዓመታት የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር በሀገራችን እንድካሄድ ያለመታከት መግለጫዎችን ሲያወጣና ሁሉንም ሲመክር ቆይቷል፡፡ በተለይም በብሔራዊ መግባባት ያልታጀበ ምርጫ ሀገሪቷን ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር እንደማያወጣት ደጋግመን አስገንዝበናል፡፡ በተለይም በአንድ ፓርቲ የበላይነት የተጠመደው ገዥው ፓርቲ ለምናቀርበው የውይይት ጥያቄ ሁሉ ወደ ደንቆሮ ውይይት በመቀየሩ የሀገራችን ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ እያሸጋገረ ነው፡፡ የሰሞኑ የፖለቲካ ትያትርም የዚህ ገታራ አቋሙ ውጤት ነው፡፡
 
ይህ ኦፌኮ ተገፍቶ የወጣበትና በእርግጠኝነትም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የማይወክል ምርጫ ቀደም ብሎ የነበረውን ስጋታችንን ከማረጋገጥ ውጭ፤ ምርጫ ውስጥ ከገቡት ፓርቲዎችም የቅሬታ ጩኼት መስማት ተችሏል፡፡ የምርጫው አጠቃላይ አካሄድ የሕዝብን ስሜት ለመሳብ ባለመቻሉና ጠለቅ ብለው ሲመለከቱትም የገዥውን ፓርቲ ፍላጎት ባለመሟላቱ የመራጮች ምዝገባ ሦስት ጊዜ ተራዝሟል፡፡ እራሱ ምርጫ ቦርድ እንዳመነው ቦርዱ የማያውቃቸው ሰባ ዘጠኝ የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው ተገኝተዋል፡፡ በመቶዎች በሚቆጠሩ የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ አልተካሄደም፡፡ እንደ ኦሮምያ ባሉ ክልሎች ላይ ደግሞ የፖለቲካ ድራማውን የሚያሳምሩ በመቶዎች በሚቆጠሩ ወረዳዎች ውስጥ ገዥው ፓርቲ የተወዳደረው ከራሱ ጋር ብቻ ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ ጦርነት ስለሆነ ምርጫ የለም፡፡ በጥቅሉ ሃምሳ በመቶው ከምርጫ ውጭ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ውሎ አድሮ የዚህን ምስቅልቅል ጉዞ ውጤት ለመተንበይ የግድ የፓርቲ አባል መሆን አያስፈልግም፡፡
 
ተቀናቀኞቻችን ሳይቀሩ እንደተረዱልን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና ኦፌኮ ተገፍተው በመውጣታቸው ለማንም አልጠቀመም፡፡ ከሁሉም በላይ ከሦስት ዓመታት በፊት በኦሮሞ ወጣቶች ደም የተገኘው ለውጥ በዋናነት የሚደግፏቸው ድርጅቶቻቸው ከምርጫው ውጭ በመሆናቸው በኦሮሞ ሕዝብ የነፃነት ትግል ታሪክ ውስጥ አንድ ትልቅ ጥቁር ነጥብ ሆኖ እንደሚኖር በግልፅ ቋንቋ ለሕዝባችን የመብት ትግል ዳግመኛ ክህደትም ይመስለናል፡፡ በምንም ተአምር የሀገራችንን ፍላጎቶች የማያሟላ ምርጫ ማለትም፤ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትንና ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን የማይፈጥር ከሆነ ለሚሊዮኖች የሚሆን ልማትና ብልፅግናንም አያመጣም፡፡ ስለሆነም፤ በኛ በኩል ለሁሉም የሀገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች የምናቀርበው የመፍትኼ ሐሳብ፣
 
1. በአስቸኳይ ሁሉን አካታች የጋራ መንግስት እንዲቋቋምና ያልተሳካውን የመንግስት ተቋማት ተሃድሶ እንዲቀጥል፣
 
2. በአስቸኳይ ሁሉን አካታች ብሔራዊ የመግባባት ድርድር እንዲጀመር፣
 
3. የጋራ መንግስቱ በጋራ የሚፈጥር ፍኖተ ካርታ እንዲመቻችና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ ፍትሓዊና ተቀባይነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ የሚሉ ናቸው፡፡
 
በመጨረሻም፤ በዚህ ወሳኝ ታሪካዊ ወቅት ላይ ሁሉም ለአገራችን ቅን እና ገንቢ አሳቢ የሆናችሁ መላው ኢትዮጵያዊያንና ዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ ከጥረታችን ጎን ቁማችሁ ለአገራችን ዘላቂ ሠላምና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንድከወን እንዲታግዙን የከበረ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ
ፊንፊኔ፤ ሰኔ 16/2013 ዓ.ል
እባብ ከእባብ ጋር