“ፍትህ ለጀዋር መሐመድ እና ለመላው የፖለቲካ እስረኞች !!”

“ፍትህ ለጀዋር መሐመድ እና
ለመላው የፖለቲካ እስረኞች !!”
—-
ጀዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባና ሌሎችም እስርቤት ውስጥ ያለአግባብ ታጉሮ የሚገኙት እስረኞች በፍጹም ሀገር አፍራሽ አይደሉም። እነዚህ ሰዎች በሰላማዊ ትግል የሚያምኑና ምንም አይነት ሀገር የማፍረስ አጀንዳ የሌላቸው መሆኑን፣ ታሪካቸው በግልጽ ይናገራል። እነዚህን ሰዎች ማሰር ፍትህን ማሰር ነው፣ ነፃነትን ማሰር ነው፣ ዴሞክራሲን ማሰር ነው፣ በአጠቃላይ ሀገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር ያላትን ዕድል የሚያጨናግፍ ተግባር ነው። ስለዚህ ሀገር እንዲረጋጋ ከተፈለገ መፍትሔው በፖሎቲካ አቋማቸው ብቻ የተነሳ ለእስር የተዳረጉት እነ ጀዋር መሐመድ በአስቸኳይ ከእስር መፈታት አለባቸው።
 
የኮሎኔል አቢይ መንግስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በተገደለ ማግስት በተቀነባበረ ሴራ ጀዋር መሐመድንና በቀለ ገርባ የመሳሰሉት የኦሮሞ ብሄርተኞች ማሰሩ ለግዜው የጠቀመው ቢመስልም አሁን ላይ ግን ከጥቅሙ ይልቅ ኪሳራው የሚያመዝን መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። የሀጫሉ አስክሬን ሰርቆ ከመንገድ ላይ መልሷል አዲስአበባ ውስጥ ሁከት ለማስነሳት አቅዷል የሚሉ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች ተአማኒነታቸው ቀስ በቀስ በሕዝብ ዘንድ ቀንሷል። በሌላ አነጋገር ለግዜው ሕዝቡ ላይ ውዥንብር ከመፍጠር ውጪ የተነዛው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እነሱ ያሰቡትን ያህል ጥቅም አላመጣም። እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንደሚባለው ሕዝቡ ቀስ በቀስ እውነቱን እየተረዳ መጥቷልና ተቀባይነት አላገኘም። በክሱ ሂደትም እስከአሁን የታየው ነገር ቢኖር እነ ጀዋር መሐመድ ለእስር የሚያበቃቸውን ወንጀል ስለ መፈጸማቸው የሚያሳይ ድርጊትም ሆነ ማስረጃ አልቀረበባቸውም ማለት ይቻላል።
 
ኮሎኔል አቢይ አህመድ የኦሮሞ ሕዝብ መሪ የሆኑትን እነ ጀዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ እና የመሳሰሉትን በማሰር የኦሮሞ ብሄርተኞችንና የኦሮሞ ሕዝብ የነፃነት ተጋድሎ ለማዳከም አቅዶት የነበረው አላማ አልተሳካም። ድርጊቱ መንግስት አስቦት ከነበረው በተቃራኒው የኦሮሞ ብሄርተኞች እንደ አሸን እንዲፈሉ ነው ያደረገው። መንግስት እነ ጀዋርን በማሰሩ በመላው አለም ላይ ተሰራጭቶ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች አንድላይ ሆኖ በአንድ ድምፅ፣ የኮሎኔል አቢይን መንግስት እንዲያወግዙ ነው የዳረጋቸው። የአለማችን ተላላቅ ሚዲያዎች የሰላም ሎሬት አሸናፊው አቢይ አህመድ በሀገሩ ሰላም ማስፈን አልቻለም፣ በሀሳብ የሚሞግቱትን የፖለቲካ ተቀናቃኞች በማሰር አንባገነን ሆኗል በማለት አለም አቀፍ ውግዘት ደርሶበታል። ይሄ በግሉ ለሱም ሆነ ለሀገራችን ትልቅ ኪሳራ ነው። [ፈይሶ ከድር]