ፍርድ ቤት የአቶ በቀለ ገርባን የተከሳሽነት ቃል አደመጠ – ነሃሴ 08/2009

ፍርድ ቤት የአቶ በቀለ ገርባን የተከሳሽነት ቃል አደመጠ – ነሃሴ 08/2009

* ጠቅላይ ሚንስቴር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ለመከላከያ ምስክርነት በፍርድ ቤቱ እንዲጠሩ ተከሳሾች አመልክተዋል።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት በነሃሴ 08/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በእነ ጉርሳ አያኖ የክስ መዝገብ የተከሳሾቹን የመከላከያ ምስክር ለመስማት የተሰየመው ችሎት ባለው ጊዜ መጣበብ ምክንያት በቅድሚያ የ4 ተከሳሾችን የመከላከያ ምስክር ለመስማት ተሰይሞ ነበር። በተከሳሾች ጠቅላይ ሚንስቴር ሀይለማርያም ደሳለኝን ጨምር ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ያካተተው የሰው ማስረጃ ዝርዝርና የሰነድ ማስረጃ ዝርዝር ላይ አስተያየት አለኝ ያለው አቃቤ ህግ “በተከሳሾቹ ላይ የቀረቡት የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች የሚያስረዱት ነገር ምንድናው? አስፈላጊነታቸው ለምን እንደሆነ ስላልተገለፀ እንዲሁም ተቃዎሟችንን በፅሁፍ ለማቅረብ ጊዜ ስለሚያስፈልገን ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን” ቢልም አስተያየቱ በተከሳሽ ጠበቆች ተቃውሞ ገጥሞታል፤ የተከሳሽ ጠበቆቹ ደንበኞቻቸው ይከላከሉ ተብለው ብይን ከተላለፈባቸው ቀን ጀምሮ የሰውና የሰነድ መከላከያ ማስረጃዎቻቸውን ለአቃቤ ህግ በሚደርስ በቂ ኮፒ ለፍርድ ቤቱ እንዳስገቡ ገልፀው አቃቤ ህግ በነዚህ ማስረጃዎች ላይ ተቃውሞ በፅሁፍ ለማስገባት በቂ ጊዜ ነበረው ብለዋል። የሁለቱን ክርክር የተመለከተው ፍርድ ቤት ማስረጃዎቹ መደመጥ እንዲቀጥሉ አዞ አቃቤ ህግ አለኝ የሚለውን ተቃውሞ ወደፊት በሚኖሩት ቀጠሮዎች ማቅረብ ይችላል ብለዋል።

ተከሳሾቹ የተከሳሽነት ቃላችንን እንሰጣለን ባሉት መሰረት ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን ቃል ወደ ለመስማት በክስ አቀራረብ ቅድመ ተከተል መሰረት የኦፌኮን አመራር የሆኑትን አቶ ጉርሜሳ አያኖ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ አዲሱ ቡላላ እንዲሁም አቶ በቀለ ገርባ የቀረበባቸውን ክስ ላይ ያላቸውን አስተያየት፣ ለእስር ሲዳረጉ በፖሊስ እና ሲቪል በለበሱ ሰዎች የደረሰባቸውን እንግልት እና በብሄራዊ ደህንነት ሪፖርት ላይ የቀረበባቸውን ውንጀላ አስመልክቶ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡

1ኛ ተከሳሽ አቶ ጉርሜሳ አያኖ፡ “ የተመሰረተብኝ ክስ የፈጠራ ነው። እኔ በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ነኝ፤ የምንቀሳቀሰውም የፓርቲውን ህገ ደንብ እና አለማ ተከትዬ ነው። በ2006 ዓ.ም የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን ተከትሎ በተነሳው ችግር ለመንግስት በፓርቲያችን በኩል ‘መንግስት ለውይይት በሩን ይክፈት’ ብለን ደብዳቤ አስገብተናል፤ በ2008 ዓ.ም የተቀናጀ ማስተር ፕላኑ ጉዳይ ድጋሚ በተነሳ ጊዜ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ የሰው ህይወት ላይ ጉዳት ደረሰ ፓርቲያችንም በድጋሚ መግለጫ አውጥቷል፤ መንግስት የውይይት በር ከፍቶ ከህዝብ ጋር እንዲወያይ ጠይቀናል። ህገ መንግስታዊ መብቴን ተጠቅሜ ነው ጥያቄ ያቀረብኩት፤ በክሱ ላይ በቢሮ ውስጥ ስብሰባ በማድረግ ይላል እኔ አስከማውቀው ድረስ በቢሮአችን የሚደረጉት ስብሰባዎች ፓርቲያችን አባል የሆነበት የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ አመራር ስብሰባ፣ የኦፌኮን አመራሮች ስብሰባ እና የወጣቶች ሊግ ስብሰባ ናቸው ከዚህ ውጪ በቢሮ ውስጥ የሚደረግ ምንም ስብሰባ የለም። አመፁ በተነሳበት ወቅት ማስተር ፕላኑ በሚያካትተው ቡራዩ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ተጉዤ ነበር፤ ከብራዮ ከተማ ከንቲባ ጋርም ተወያይቼ ነበር፤ በወቅቱ የስብሰባ አዳራሾች ተይዘው ስለነበር ስብሰባውን በሌላ ቀን ለማድረግ ከመግባባት ላይ ደርሰን ነበር፤ ፓርቲያችን ሰለማዊና በህግ የሚያምን ስለነበረ አንደም ቀን ከየትኛውም አካል ቅሬታ ቀርቦበት አያውቅም። በብሄራዊ ደህንነት ሪፖረት ላይ የተጠቀሰው ቀንና ሰአት የሌለው ህገ መንግስታዊ የመከላከል መብቴ አንዲገፈፍ ሆኗል።

2ኛ ተከሳሽ አቶ ደጀኔ ጣፋ፡ “ፍርድ ቤቱ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ ስህተት ተሰርቷል፤ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ አሸዋ ሜዳ አዲስ አበባ ውስጥ ያለ ቦታ ተደርጎ ነው የተጠቀሰው፤ ይህ ስህተት ነው። አሸዋ ሜዳ የቡራዮ ከተማ አካል ነው ስለዚህ በብርበራ ወቅት የመጡት ታዛቢዎች ከአዲስ አበባ ወደ ቡራዩ ነው እንጂ ፍርድ ቤቱ እንደተረዳው መኖሪያ ቤቴ ከሚገኝበት አካባቢ አይደለም። በታህሳስ 14/2008 በቁጥጥር ስውል አዲስ አበባ አራዳ ፈርድ ቤት አቅራቢያ ነበርኩ። ከዛው ከፍርድ ቤት የብርበራ ወረቀት ማቅረብ ይችል ነበር። ወደ ቤቴ ወሰዱኝ በ5 መኪና 21 ፖሊስ ነበሩ ሰፈሩ በወታደር ተከቦ ነበር፤ እቤት ስንገባ የብርበራ ፈቃድ አሳዩኝ አልኳቸው፤ የለንም ብለው በግድ ገቡ፤ ተፈተሹ ብላቸውም ፖሊስ አይፈተሽም በማለት እምቢ አሉ። በቴ ጠባብ ነበር ብዛት ያለቸው ፖሊሶችና ደህንነቶች ነበሩ፤ ሳሎኑን ተፈትሾ ከጨረስን በኋላ ወደ መኝታቤት ገብተው መደርደሪያ ላይ ያሉ መፅሃፎችን በርብራው ወሰዱ ወደ ሳሎን ስንመለስ አንድ ሲቪል የለበሰ ፖሊስ ከያዘው ቦርሳ ውስጥ ወረቀት እያወጣ ሳለ ባለቤቴና ልጄ አይተውት ዘለው ያዙት መሳሪያ የታጠቁ ፖሊሶች ባለቤቴና ልጄ ላይ ደቅነው በሆዳቸው እንዲተኙ አረጓቸው፤ በጣም ነበር የደነገጥኩት። የኦነግ ሰነድ ተብሎ የተያዘው ሰነድ እራሳቸው ይዘውት የመጡት ስለሆነ አልፈርምም አልኩም በወቅቱ የነበረችውም ታዛቢ አልፈረመችበትም። አሁን ከክሱ ጋር ተያይዞ የምታዩት ሰነድ ላይ ያለው ፊርማ አስመስሎ የተሰራ ነው የእኔ አይደለም። በክሱ እንደተጠቀሰው ‘የአሸባሪ ድርጅት ሚድያ’ ኦ ኤም ኤን (OMN) ጋር ኢንተርቪው አድርጓል የሚለው በየትኛውም የኢትዮጵያ ህግ ኦ ኤም ኤን የአሸባሪ ሚድያ አልተባለም፤ ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር ስብሰባ ተቀምጠህ ነበር የተባለውም እንኳን ስብሰባ ልቀመጥ አንድም ቀን አግኝቻቸው አላውቅም ኦፌኮንን የመሰረትነው እሳቸው በእስር ላይ እያሉ ነው። በደህንነት ሪፖርት ላይ የታሰሩ እስረኞችን ለማስለቀቅ በሀይል ሲንቀሳቀስ ነበር ይላል፤ በ2006 ዓ.ም ማስተር ፕላኑን ተቃውመው የታሰሩና በኦሮምያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሽብር የተከሰሱ ከ200 በላይ እስረኞች ጥብቅና ቆሜ ተከራክሬ ነፃ እንዲወጡ አድርጌአለሁ። በሀይል እስረኛ ለማስፈታት አስቤ አላውቅም”

3ኛ ተከሳሽ አዲሱ ቡላላ፡ “የተያዝኩት ታህሳስ 14/2009 ነው። ወደምማርበት ዩንቲ ዩንቨርስቲ ስሄድ ነው የተያዝኩት፤ ከተማውን ብዙ ካዞሩኝ በኋላ አመሻሱ ላይ ነው ለፍተሻ ወደ ምኖርበት ቤት ይዘውኝ የሄዱት፤ ቤቴ በወታድር ተከቦ ነበር። ካሜራና የያዙ ሰዎች አብረው ነበሩ፤ የፊል ፕሮዳክሽን በበር የሚመስለው። ወደ ፍተሻ ከገቡ በኋላ ብዙ መፃኅፍጽና መጥሄቶች በርብረው ወስደዋል፤ ቤቴ ውስጥ መስኮት አለ መስኮቱ ወደ ውጪ የሚያሳይ ነው፤ መስኮቱ ያለበት ክፍል ስንገባ ሻንጣ ውስጥ የተጠቀለለ ነገር አገኙ፤ ምንድነው ብለው ሲጠይቁኝ እንደማላውቅና ተመላላሽ ሰራተኛ አለጭኝ ምንአልባት ይሷ እንደሚሆን ነገርኳቸው፤ የተጠቀለለው ነገር ሲፈታ የኦነግ ባንዲራ ነበር። የኔ አይደለምአልፈርምም አልኳቸው፤ እንድፈርም ያስገድዱኝ ነበር። በወቅቱ የነበሩት ታዛቢዎች እንድፈርም ያባብሉኝ ነበር፤ አንዷን ታዛቢ እዚሁ ፍርድ ቤት ስትመላለስ አያት ነበር፤ ‘የምትፈርመው ከኔ ቤት ተገኘ ብለህ እንጂ የኔ ነው ብለህ አይደለም’ ይሉኝ ነበር በመጨረሻም አስገድደው አስፈረሙኝ። ሌላው ተገኘ የተባለው ፈላየር ነው፤ ፈላየር ለህዝብ የሚበተን ብዙ ወረቀት ነው፤ ቤቴ የተገኘው ግን 2 ፈላየር ነው፤ እኔ ሁለት ፈላየር የማስቀምጠው ምን ላረገው ነው!? እራሳቸው ይዘው የመጡትን ነው እንደማስረጃ ያቀረቡብኝ።”

4ኛ ተከሳሽ አቶ በቀለ ገርባ፡ “ተከላከል ስለተባልኩበት ገዳይ ነው የማወራው። በዋናነት አንድ ግለሰብ ከምእራብ ወለጋ ዞን ደውሎልህ ህዝብ ከመንግስር ስልጣኑን እየሰደ ነው ሲልህ መሆን ያለበትም ይሄ ነው ብለህ ህገወጥነትን አበረታተሀል የሚል ነው። እኔ እድሜ ልኬን ለህግ እና ለህገመንግስት የቆምኩ ሰው ነኝ፤ በተመሳሳይ ክስ ታስሬ የተፈታው ወቅት ፓርቲዬ የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርግበት ወቅት ነበር። እኔም ፓርቲዬን ወክዬ ህዝቡ በምርጫ እንዲሳተፍ ስቀሰቅስ ነበር፤ በህገወጥነት የማምን ብሆን ኖሮ ህዝብ ምርጫ ላይ እንዲሳተፍ አላደርግም ነበር። በተለያየ የገጠር ከተሞች እየዞርን የምርጫ ቅስቀሳ ስናደርግ ደህንነቶች በየመንገዱ እያስቆሙና ጫካ ውስጥ እያስገቡን ንበረታችንን፣ ሪከርድ ያረግነውን ጭምር ይወስዱብን ነበር፤ ይሄ ሁሉ በደል እየደረሰብን ለአንደም ሰከንድ በሰላማዊ መንገድ ከመታገል ውጭ አስቤ አላውቅም። ውጭ በነበርኩ ሰዓት በኦሮሞ ጥናት ማህበር በጋበዘኝ መሰረት ንግግር አድርጌያለሁ ይህ አንድም ህገ ወጥ ንግግር የለውም። በሰላማዊ የትግል መንገድ ላይ ያለኝ ቁርጠኝነት የማይቀየር ነው። ለዚህም ነው የማርቲን ሉተር ኪንግስ መፅሃፍ በአገሪቱ ትልልቅ ቋንቋዎች ኦሮምኛና አማርኛ የተረጎምት። ከመታሰሬ ጥቂት ቀደም ብሎ ህዝቡ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርብ፣ ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በግል የፌስቡክ አካውንቴ ገልጬ ነበር። መሬታችንን ለጉራጌና ለስልጤ አሳልፈን አንሰጥብ ብለኋል የተባለው ከቆምኩለት የእኩልነት አለማ ጋር ፈፅሞ የሚጣረስ ነው፤ በብሄሮች መካከል እኩልነት እንዲኖር እንጂ ልዩነት እንዲሰፋ አንድም ቀን ሰርቼ አላውቅም፤ ይሄ እኔን አይገልጽም።”

ተከሳሾቹ የተከሳሽነ ቃላቸውን በሚሰጡበተት ጊዜ የመሃል ዳኛው (በከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት) በተደጋጋሚ እያቋረጣቸውና ክሳቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ሲነግሯቸው እንደነበር ለማየት ተስተውሏል። የኦፌኮን ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ የተከሳሽነት ቃላቸውን በሚሰጡበት ጊዜ በእጅ መዳፋቸው ላይ የፃፉትን ማስታወሻ ጎንበስ እያሉ ሲያነቡ ተስተውሏል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደዘገበው ተከሳሾች ከቂሊንጦ እስር ቤት ምንም አይነት ማስታወሻ ወረቀትም ሆነ ፅሁፍ ያለበትም ነገር ይዘው እንዲወጡ አይፈቀድላቸውም።
Source ;Ethiopia Human Rights Project

 

Dr. MereraGudina's

 

Hell on earth