Kichuu

ፌዴራል ፖሊስ በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ቤተሰቦች

ፌዴራል ፖሊስ በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ቤተሰቦች ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው አለ

ፌዴራል ፖሊስ በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ቤተሰቦች ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው አለ

(ethiopianreporter) — የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችና ባለሀብቶች፣ ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆኑን ለፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

መርማሪ ቡድኑ ተፅዕኖ መኖሩን የገለጸው፣ ነሐሴ 17 እና 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ለሦስተኛ ጊዜ ያቀረባቸው የስኳር ኮርፖሬሽን፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው በመጠየቃቸው ነው፡፡

መርማሪ ቡድኑ እንደገለጸው፣ ተጠርጣሪዎቹ እንኳን ከእስር ተለቀው በእስር ላይ እያሉም በቤተሰቦቻቸውና በጓደኞቻቸው አማካይነት በምስክሮችና ይሠሩባቸው በነበሩባቸው ተቋማት ሠራተኞች ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው፡፡ እነሱ ቢለቀቁ ደግሞ ያላቸውን ተሰሚነትና ግንኙነት በመጠቀም ያልተሰበሰቡ ሰነዶችን የማስጠፋት፣ ምስክሮችን የማባበልና የማስፈራራት አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ፣ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ እንደሚቃወም አስረድቷል፡፡

ከስኳር ኮርፖሬሽን ከተንዳሆ፣ ከመተሐራ፣ ከኩራዝ ኦሞ ቁጥር አምስት በድምሩ 13 ተጠርጣሪዎች ቀርበዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ የ57 ምስክሮች ቃል መቀበሉን፣ በርካታ ሰነዶችን ከተለያዩ ተቋማት መሰብሰቡን፣ የተጠርጣሪዎችን ሀብት በማጥናት የወንጀል ፍሬ የሆኑትን ማሳገዱን አስረድቶ፣ የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመው በአሥር የስኳር ፕሮጀክቶች ላይ  በመሆኑ፣ በጣም ውስብስብ መሆኑንና ያለምንም እረፍት እየሠራ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በቀጣይ የምርመራ ቀናት የ59 ምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው፣ ከየተቋማቱ የፋይናንስ ሰነዶችን በተጠርጣሪዎቹ ተባባሪዎችና ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አማካይነት እያሸሹ መሆናቸውን፣ የተወሰኑ ሰነዶችን በግለሰቦች እጅ እያሉ መያዛቸውን በመናገር፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት አመልክቷል፡፡

ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት 20 ሚሊዮን ብር ያላግባብ ተከፍሏቸዋል የተባሉትና ለባቱ ኮንስትራክሽን የተሰጠ የመሬት ምንጣሮ በመንጠቅ ለየማነ ጠቅላላ ተቋራጭ በመስጠት ከ216 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ተጠርጥረው የታሰሩት አቶ የማነ ግርማይ፣ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ መሣሪያ ማስተኮሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ይዞ የሄደ ቢሆንም፣ መሣሪያ በማስተኮስ ላለመያዝ ሙከራ ካደረጉ በኋላ፣ ወደሚያውቁት ባለሥልጣን ከደወሉና እጃቸውን እንዲሰጡ ሲነገራቸው በቁጥጥር ሥር ሊውሉ መቻላቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸውም ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆናቸውንም አክሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ‹‹ለምን በወቅቱ ሪፖርት አላደረጋችሁም?›› በማለት ጥያቄ በማንሳት፣ እንደዚህ ያለ ድርጊት መፈጸም እንዳልነበረበት አስታውቋል፡፡

በኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ተጠርጥረው የታሰሩት፣ የጄጄአይኢሲ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዲዮ ኦን ባለሥልጣናትን ቻይና በመውሰድ ያዝናኑ እንደነበር፣ ወ/ሮ ሳሌም ከበደና አቶ ብርሃኑ ሐረጎት የተባሉት ተጠርጣሪዎች ደግሞ ከቻይናውያን በአካውንታቸው ገንዘብ እንደገባላቸው ማስረጃዎች ማግኘቱን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

በሌላ የምርመራ መዝገብ በቀረቡት እነ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ላይ መርማሪ ቡድኑ በተፈቀደለት ጊዜ የተለያዩ ሰነዶችን ማስተርጎሙን፣ የተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበሉን፣ የተለያዩ ሰነዶችን ሰብስቦ የትንተና ሥራ ማከናወኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተረከባቸው መዝገቦች ላይ ከተከሳሾቹ ቃል አለመቀበሉን ገልጾ፣ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡

በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ የነበሩት እነ ወ/ሮ ፀዳለ ማሞም ቀርበው ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በተፈቀደለት ጊዜ ዘጠኝ ምስክሮችንና ሁለት የግዢ ኤክስፐርቶችን ማነጋገሩን፣ የአራት ተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበሉን፣ ከፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ስድስት ጥራዝ ሰነዶችን መሰብሰቡን፣ ንብረታቸውን ማሳገዱንና ሌሎች በርካታ የምርመራ ሥራዎችን ማከናወኑን አስረድቷል፡፡ የአንድ ተጠርጣሪን ቃል፣ የአራት ምስክሮችን ቃል መቀበልና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር ቢሮ ተጨማሪ የኦዲት የምርመራ ሰነዶችን መቀበል እንደሚቀረው አብራርቶ የጠየቀው መርማሪ ቡድኑ፣ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት አመልክቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተጠርጣሪዎቹ ላይ አከናወንኩ ባላቸውና ይቀሩኛል ባላቸው የምርመራ ሥራዎች ላይ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ተመሳሳይ የሆነ ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ሠርቻለሁና ይቀሩኛል የሚላቸው ነገሮች ተመሳሳይ መሆናቸው፣ ይቀረኛል የሚላቸው ሥራዎች ተጠርጣሪዎቹ ሳይታሰሩ መሥራት የሚችላቸውና በመንግሥት ተቋም ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹን ማሰር ሳያስፈልግ ማጣራትና መሰብሰብ የነበረበትን መረጃና ማስረጃ እነሱን አስሮ ወደ ፍለጋ መግባቱ ሕጋዊ ይዘት የሌለው በመሆኑ፣ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ፣ የመርማሪ ቡድኑን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን ውድቅ በማድረግ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው ተጨማሪ 14 ቀናት ውስጥ፣ የስምንትና 12 ቀናትን ፈቅዷል፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽንና የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተጠርጣሪዎች ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣንና የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት ስኳር ፕሮጀክት ተጠርጣሪዎች ለነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

በየማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ የፋይናንስና ንብረት ዕግድ ይነሳልኝ ጥያቄ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ የቀረበ ቢሆንም፣ የግራ ቀኙ ተከራካሪዎች አስተያየት ሰጥተውበት ማለትም ዕግድ የጠየቀው መርማሪ ፖሊስ ሦስተኛ ወገንን፣ የፋይናንስ እንቅስቃሴንና የሠራተኛ ደመወዝን በማሰብ እንዴት ታግዶ መቆየት እንዳለበት ሐሳብ እንዲያቀርብ፣ ድርጅቱ ደግሞ በምን ሁኔታ ዕግዱ መነሳት እንዳለበት እንዲሁ ሐሳብ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት በተመሳሳይ የቀጠሮ ቀን እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

Exit mobile version