የጥል ግድግዳ የሆኑ የጥላቻ ሃውልቶችን ማፍረስ ያስታርቃል እንጂ አያጣላም፤ ጥላቻንም አያሳይም!!!

የጥል ግድግዳ የሆኑ የጥላቻ ሃውልቶችን ማፍረስ ያስታርቃል እንጂ አያጣላም፤ ጥላቻንም አያሳይም!!! (Tsegaye Ararssa)
==============
ለዓመታት ጥላቻና ዘር ማጥፋት የፈፀሙ ነገሥታትን ሃውልት ማቆምና ገዳይን እያወደሱ መኖር ነው ጥላቻ። በግፈኛ ነገሥታት ለተጎዱ ሰዎች ክብርና አገርን ከታሪኩ ጋር ለማስታረቅ ሲባል የነዚህን ገዳዮች የጥላቻና የንቀት ምልክት የሆነ ሃውልት ይፍረስ ማለት ጥላቻ ሊሆን አይችልም።

ለመሆኑ የገዳዮች መታሰቢያ የሆነ የጥላቻ ሃውልት ይፍረስ ማለት እንዴት ነው ማንን ከማን የሚያጣላው? ለምን? ለምንድነውስ በዚህ ምክንያት እንበጣበጣለን የሚባለው? ነው ወይስ የጥላቻ ሃውልት ከፈረሰ እና እኛ እንደልብ መጥላት ካልተፈቀደልን እንበጠብጣለን ነው? ስንገድላችሁም ዝም በሉ፣ ገዳይነታችንን ስናወድስም ዝም ብላችሁ አብራችሁን ጨፍሩ፤ ካልጨፈራችሁ እንጨርሳችኋለን የሚል አንድምታ እንዳለውስ ለምን አይታሰብም?

አንዳንዶች የሃውልት ይፍረስ ጥያቄ የፖለቲካ ትርፍ ፈላጊዎች ጥቄቃ ነው፤ እንጂ የሕዝቡ ጥያቄ የሃውልት ይፍረስ ሳይሆን የዳቦ ጥያቄ ነው ይላሉ። በእውነቱ ሃውልት ይፍረስ በማለት የሚገኝ የፖለቲካ ኪሳራ ይኖር ይሆናል እንጂ የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ ሁሉም ሰው ያውቀዋል። በአንፃሩ ይህን ክስ የሚያቀርቡ ሰዎች አዲስ የግፍ ሃውልት እንገንባ የሚሉትን ጀብደኞች አይወቅሱም። አዲስ (የጣይቱ) ሃውልት ግንባታም ከዳቦ ጥያቄ እንዴት እንደሚቀድም አያስረዱም። እነዚህ ሰዎች፣ የግፍ ሃውልት ይፍረስ የሚለው ጥያቄ የፍትህ ጥያቄ መሆኑን ይረሳሉ። የፍትህ ጥያቄ ደግሞ ከኢኮኖሚ ጥያቄ ጋር አይጋጭም። በክብደትም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባ እንደሆን እንጂ ከኢኮኖሚ ጥያቄ አያንስም። ቅደም ተከተላዊ አትኩሮት ይሰጠው ቢባል እንኳን የጥያቄዎቹን ቅደም ተከተል የሚወስነው የጥያቄዎቹ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ነው እንጂ፣ “አንገብጋቢ ጥያቄህን እኛ እናውቅልሃለን!” የሚሉ የግፈኛ ሥርዓት ወራሽና ባላደራ ግለሰቦች አይደሉም።

የምኒልክ ሃውልት ይፍረስ መባሉ የማይታረቅ ቅራኔ ይፈጥራል የሚሉ ማስፈራሪያዎችም ይሰነዘራሉ። ስለእውነት ከተነጋገርን ግን የጥላቻ ሃውልት ማፍረስ የማይታረቅ ቅራኔ አይፈጥርም። እንዲያውም ለታሪክ ህፀፅ እውቅና ሰጥቶ የግፍ ምልክት የሆነ ሃውልትን ማፍረስ፣ ግፍን በጋራ ለመኮነን እድል ሰጥቶ አገርን ያስታርቃል።

የፍትህ ጉዳይ ችላ ሊባል የሚገባ ጉዳይ አይደለም። የፍትህ ጉዳይ ችላ ተብሎ የጋራ የሆነ ወደፊት (shared future) ሊኖር አይችልም። በተለይ ደሞ ችላ እንድንል የሚጠየቀው የገዳዮች አዳፋ ታሪክ ተመርጦ ሲሆንና ዛሬም እንዲገነባ የሚጠየቀው የገዳዮች ግፍን የሚያገንን ሌላ የጥላቻ ሃውልት ሲሆን!!! የፍትህ ጥያቄ የትም፣ መቼም፣ ከማንኛውም ጥያቄ ፊተኛና ቀዳሚ ነው። የፍትህ ጥያቄን፣ የፍትህ ጥያቄ የሚያደርገው ይሄ ለነገ ተብሎ በይደር ይቆይ ማለት አለመቻሉ ነው። The question of justice can not wait!!!

አሮጌ ሃውልት ከማፍረስ አዲስ ታሪክ መስራት ይሻላል የሚሉም አልጠፉም። ይህ ትውልድ የራሱን አኩሪ ታሪክ እየሰራ ነው። ከሚሰራው አዲስ ታሪክ አንዱ ደግሞ ግፍንና የግፍን መሠረት ምልክቱ ከሆኑት የመታሰቢያ ሃውልቶቹ ጭምር ማፈራረስ ነው። በዛ ላይ፣ አዲስ ታሪክ ለመሥራት የግድ አዳፋ የታሪክ ድሪቶን መደረብ የለብንም። አዲስ ታሪክ እየስራንም ታሪካዊ ግፍን እናፈርሳለን። ምልክቶቹንም ጭምር። ይህን ማድረግ አስፈላጊነቱ፣ በኪነ-ጥበብ በኩል የግፈኛ ነገስታትን ቆሻሻ ለማጠብና ሥርዓቱን ለማስዋብ (aestheticize ለማድረግ) የሚደረግ ጥረት፣ ክርፉቱንም ለመቀነስ የመሞከር (deodorize የማድረግ) ተግባር ሙሉ በሙሉ መቆም ስለአለበት ነው።

ገዳይን የሚያጀግን፥ ዘራፊ ቀማኛን የሚያፀድቅ ከንቱ የሥልጣን ጠባቂዎች (የapologists of power) የጥበብ ውጤት–እንደምኒልክ ሃውልት ያለውን ማለት ነው– አደባባይህ ላይ እያቆምክና እየዘከርክ የምትሰራው አዲስ ታሪክ የለም፤ አይኖርም። ስለዚህ የምኒልክና ሌሎች የግፍ ሃውልቶች መፍረሳቸው እርቅን እንጂ ጠብን አያመጣም።

አንዳዶች ሃውልቱ ይፍረስ ማለት የሃውልቱን መቆም የሚደግፉ ሰዎችን መብት ይጥሳል የሚል መሠረተቢስ ክርክር ያነሳሉ። የዚህ ሃውልት ደጋፊዎች፣ ይህን ሃውልት በኦሮምያም ሆነ በተስፋፊ ነገሥታቱ በወረራ በተያዙትና በተዋሃዱት ክልሎች ውስጥ የማቆም አንዳችም መብት የላቸውም። አገሩን እንደ አንድ አገር ቢያዩት ኖሮና የሌላው መጎዳት የራሳቸውም እንደሆነ የሚያስቡ ትሁታን ቢሆኑማ ይሄን ግፍ አፍረውበት ከሁላችንም ጋር አውግዘው፥ ሃውልቱን አፍርሰው፣ በመከባበር ለመኖር ቃል ይገቡ ነበር። በእርግጥ፣ ይህን አዳፋ ታሪክ እያወሩ ለመኖርና እንደቅርሳቸው ለማቆየት ከፈለጉ እዛው መንደራቸው ወስደው ማቆም ይችላሉ። መብታቸው ይሄ ነው እንጂ፣ በጨፈጨፉት ሕዝብ መሬት ላይ ሃውልቱን አቁመነው እየተወደስንበትና እየተጋነንበት እንኑር ማለት መብታቸው አይደለም።

“በታሪኩ ትንታኔ ላይ ስምምነት በሌለበት ሁኔታ እንዴት ይፍረስ ይባላል?”የሚል ጥያቄ የሚያነሱም አሉ። በትንታኔው ላይ ስምምነት ከሌለ (መስማማት እንኳን አለ!) ታድያ መግባባት በሌለበት ታሪክ ላይ ተመርኪዘን ሃውልት አቁመን አለመግባባትን ለምን ይበልጥ እንዲሰፋ እናደርጋለን?

‘ተከባብሮ ለመኖር ሲባል ይቅር’ የሚሉም አሉ። የጨፈጨፍናቸው ሰዎች ላይ የገዳያቸውን ሃውልት አቁሞ መኖር፣ መከባበር አይደለም። ይሄ የጥፋት ማስታወሻና መዘከሪያ ሃውልት ይነሳ ሲባል ‘እንተላለቃለን’ ማለትም መከባበር ሳይሆን ‘ትናንት ጨፍጭፈንና ነጥቀን ዛሬ ደግሞ እያዋረድናችሁ ካልኖርን በቤታችሁ ውስጥ እንዋጋችኋለን፤ እንጨርሳችኋለን’ ብሎ እንደማስፈራራት ነው። ይሄ ደሞ ባለው ውጥረት ላይ እሳት ጭሮ ቤንዚን ማርከፈከፍ ነው።

ሌላው የክርክር መስመር ደግሞ ይሄ ነው፦”ኦሮሞ ታሪክ ሰርቶ የሚያጋራ ትልቅ ሕዝብ እንጂ ያለፈ ቁስል የሚያስታውስ ትንሽ ሕዝብ አይደለም።” ኦሮሞ ታሪክ ሰርቶ ድሉንም ተጋርቶ የሚኖር ሕዝብ መሆኑ ግልፅ ነው። ዛሬም እየታየ ነው። ያለፈ ቁስል አያስታውስም ብሎ ማለት ግን ‘ትውስታውን እኔ አውቅለታለሁ፣ የሚያስታውሰውም ቁስሉን አይደለም’ እያሉ መታበይ ነው። እብሪት ነው። ኦሮሞ ምንን ማስታወስ እንዳለበት ምንን መርጦ መርሳት እንዳለበት ማንም ሊነግረው አይችልም። አንተ የምትፈልገውን ብቻ እንዲያስታውስልህ የምትፈልግ ከሆነ ታሪኩን እንዲያስታውስ ሳይሆን አንተን እንዲያስታውስህ እየጠየከው ነው። በአንተ ጭንቅላት ትውስታውን እንዲያደራጅ እየጠየክ ነው። የራሱን ታሪክ አስታውሶ ፍትህ መጠየቁ፥ የጥላቻ መዘከሪያ ሃውልት ይፍረስ ማለቱ ትልቅነት እንጂ ትንሽነት አይደለም። ትልቅነትን/ትንሽነትን አንተ የምትወስንለት የማይረባ ሕዝብ አይደለም። ባንተ መስፈርት ትልቅ መባል እራሱ መቅለል ነው። አንድ ከትንሽ ሕዝብ የወጣ ልሂቅ ለትልቁ ሕዝብ የታላቅነትን መስፈርት አስቀምጦ የእራሱ ምኞት በወለደው መስፈርት ትልቅነቱን ‘አቅልለህ አሳነስከው’ ለማለት መድፈሩ በአሪረቱ ውስጥ ያለውን ታሪካዊውን የትርክት ሥልጣን መዛነፍ ( the asymmetry in discursive power) ያሳያል።

የግፍ ሃውልትን ማፍረስ ጨለምተኝነትነው፣ አምባገነንነት ነውም ይባላል። የፍትህ ጥያቄ ማንሳት ጨለምተኝነት አይደለም። ኢፍትሃዊነትን ኮንኖ የፍትሃዊ ሥርዓት ተስፋን መፈንጠቅ፥ የተስፋ ብርሃን ማምጣት/ማማጣት ነው እንጂ!!! ፍትህን መጠየቅ አምባገነነት ሊሆን አይችልም። አምባገነንነት ሥልጣንን በመጠቀም ሌሎች ላይ የራስን ሃሳብ በጉልበት መጫን ነው። የፍትህ ጥያቄ እንዴት ነው አምባገነንነት ይሚሆነው?

‘የምኒልክ ወረራና የኃይል ተግባር እንደ ጥፋት የሚወሰድ አይደለም፤ የወቅቱ የፖለቲካ አካሄድና ሥልጣን ማደራጃ መንገድ እንጂ’ የሚሉም አሉ። በወቅቱ ሥልጣን የሚደራጀው በወረራና በመስፋፋት ብቻ አልነበረም። ከ ማግና ካርታ (1215)፥ ክእንግሊዙ አብዮት (1608)፣ ከፈረንሳይ አብዮት (1789)፥ ከአሜሪካ ምስረታ (1776፣ 1787)፥ ከሄይቲ የጥቁሮች አብዮትና ነፃነት (1804)፥ በኋላ የተቋቋመ አገር ነው ኢትዮጵያ። በዘመኑም መስፈርት እንኳን የምኒልክ መንግሥት የተጠቀመው የመጨረሻ አውሬያዊና አረመኔያዊ(savage and barbaric) የመንግሥት አመሰራረት ሂደት ነበረ። ለዚህም ማስረጃ የሚሆን በወቅቱ የተፃፉ ብዙ ፀኅፍት የፃፉት የታሪክ ሰነዶች አሉ።

እውነት የዘመኑ የፖለቲካ አካሄድ ይሄ ነው ቢባል እንኳን የተፈፀመውን ግፍ ትክክል አያደርገውም። አገሮች በቅኝ የሚያዙበት ጊዜ መሆኑም ተግባሩን ትክክል አያደርገውም። ስለዚህም ነው ቅኝ ግዛት ተኮንኖ የፈራረሰው። ቅኝ አገሮችም ነፃ የወጡት። ኢምፓየሮችም የፈራረሱት። ስለዚህም ነው እነዚያ አገሮችም ዛሬ ዛሬ የተስፋፊ ነገሥታትን ተግባር እያወገዙ፥ ተበዳዮችን ይቅርታ እየጠይቁ፥ መታሰብያ ሃውልቶችን እያፈረሱ፥ ሕዝብን ከሕዝብ፣ አገርንና መንግሥትን ከታሪክ ውርሱና ከራሱ ጋር ለማስታረቅ እየታተሩ ያሉት።

#YesMenelikMustFall #No2TayituStatueinFinfinnee

1 Comment

  1. One of my great grand father named Bati Bixxirro was one of the victim by the genocidal barbaric action of Menilik.He said this”yamililik,cidhaanko miserable fincaanko hinmurtu”.This is a message for generation for a cruel genocidal action taken to the Oromo people.Such dirty history needs to be cleaned and cleared that hampers and intemediate, as a gap between this generation of the two society.It is being foolish to resonate,the past mistake as if its,legitmate,than taking a corrective action by the educated generation of 21st century. The two nations are highly assimilated and sharing many things in common.However the truth never be denied.

Comments are closed.