ግዴታውን የማይወጣና ያልተወጣ ምርጫ ቦርድ፣ ግዴታቸውን የሚወጡ ክልሎችን ማስፈራራት አይችልም!

ግዴታውን የማይወጣና ያልተወጣ ምርጫ ቦርድ፣ ግዴታቸውን የሚወጡ ክልሎችን ማስፈራራት አይችልም!
=======================

1. የምርጫ ቦርድ፣ ምርጫ የማስፈጸም ግዴታ እንጂ ምርጫ የማገድ ሥልጣን አልተሰጠውም።

2. አንቀጽ 102፣ አገራዊው (“ብሔራዊ” ) ምርጫ ቦርድ ስለ መቋቋሙ፣ ስለ አባላቱ አሿሿም፣ እና ምርጫን በገለልተኝነት ለማስፈጸም ስላለበት ኃላፊነት ይደነግጋል እንጂ፣ ምርጫን ሁሉ የማስፈጸም ሥልጣን በብቸኝነት (exclusively) ለዚህ ተቋም ተሰጥቶታል አይልም።

3. “ብሔራዊ” ምርጫ ቦርድ በአንቀጽ 102 መሠረት ተቋቁሟል ብሎ ማለት፣ ምርጫን የማስፈጸም ሥራ በፌደራል መንግሥቱ የሥልጣን ወሰን ሥር ነው (በመሆኑም ክልሎች ምርጫን በማስፈጸም ጉዳይ ላይ ምንም ሥልጣን የላቸውም) ማለት አይደለም።

4. “ብሔራዊ” ምርጫ ቦርድ ይኖራል ማለት፣ በክልሎቹ ውስጥ፣ በክልሎቹ ሕገ-መንግሥታት ወይም አግባብነት ባላቸው ክልላዊ አዋጆች አማካኝነት፣ ክልላዊ የምርጫ አስፈጻሚ አካል ማቋቋም አይቻልም ማለት አይደለም።

5. ክልላዊ ምርጫን ለማካሄድ፣ “የብሔራዊ” ምርጫ ቦርድ ተጠይቆ፣ በፖለቲካ ወገንተኝነት ምክንያት አላስፈጽምም ካለ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታውን አልተወጣም፣ ወይም ሊወጣ አልፈለገም ማለት ነው። ለዚህም፣ ተጠያቂ ሊደረግ ይገባዋል።

6. “ብሔራዊ” ምርጫ ቦርድ፣ በክልሎች ውስጥ ምርጫ የማስፈጸም ግዴታውን አልወጣም በማለቱ ምክንያት፣ ክልሎች በራሳቸው የምርጫ አስፈጻሚ አካል አማካኝነት ምርጫ ለማከናወን የሚያደርጉትን ጥረት፣ ማንኳሰስ፣ ለማገድ መሞከር፣ እና ሕጋዊ እውቅና እንደሌለው በማስመሰል መግለጫ መስጠት፣ ምርጫን ማወክ በመሆኑ፣ በወንጀል የሚያስጠይቅ ተግባር ነው።

7. የፌደራል “መንግሥቱ” ምርጫ የማድረግ ግዴታውን መወጣት ባለመፈለጉ ብቻ፣ የክልሎችን የምርጫ ሂደት ማስተጓጎል አይችልም። መሞከርም፣ ወንጀል ነው። በሕግ አግባብ ተከባብሮ የመኖር ግዴታውንም እየዘነጋ መሆኑም ሊነገረው ይገባል። በፌደራሉ ሕገ-መንግሥት፣ አንቀጽ 50(8) በተደነገገው መሠረት፣ የፌደራል መንግሥቱ የክልሎችን ሥልጣን፣ ክልሎችም የፌደራሉን መንግሥት ሥልጣን፣ ማክበር ይገባቸዋልና።

8. ሰሞኑን፣ አንዳንድ “የአዲስ አበባ ከተማ ጠበቆች” (ሕግ የማያውቁ የሕግ ባለሙያዎች) በ”አንዳንድ” የ FM ሬድዮ ስርጭቶች ላይ፣ “የፌደራል መንግሥቱ፣ ምርጫ በሚያደርጉ ክልሎች ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት” ሲሉ የለገሱት ምክር፣ ምንም የሕግ መሠረት የሌለውና ኃላፊነት የጎደለው ንግግር ነው።

9. እነዚህ “በአንዳንድ” የFM ሬድዮ ስርጭቶች ላይ የቀረቡ “አንዳንድ የከተማው ጠበቆች፣” የትግራይ ክልል ምርጫ ካካሄደ፣ (ሕገ-ወጡ) “የፌደራል” መንግሥት”፣ ከፌደሬሽን ምክር ቤት የፌደራል ጣልቃ-ገብነት ትዕዛዝ አስወጥቶ፣ ትግራይን በፌደራል ኃይሎች ማጥቃት አለበት ሲሉ ተደምጠዋል። (ይህቺ እንኳን፣ የግጭትን ውጤት የማያውቁ የከተማ ነገረ-በሎች ከንቱ ትንኮሳ ነች ብለን ልንተዋትም እንችላለን።)

የሆነ ሆኖ ግን፣ በሕግ አግባብ (በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62(9) እና በአዋጅ ቁ. 359/2003) መሠረት፣ የፌደራል ጣልቃ-ገብነት የሚታዘዘው፣ በክልሎች ጥያቄና ግብዣ፣ መጠነ-ሰፊና ከክልሉ አቅም በላይ የሆኑ፦

ሀ) የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣

ለ) የሕግና ሥርዓት መደፍረስ፣

ሐ) ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚፈታተን አደጋ ሲከሰት ብቻ ነው።

አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳየው፣ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ መግባት እንዳለበት ሳይሆን፣ ክልሎች፣ በፌደራሉ መንግሥት “ጣልቃ በመግባት” ሥርዓት ማስፈን እንዳለባቸው ነው።(ሕጉ አይልም እንጂ!)

10. ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታን፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም እንኳን ሆኖ ለመወጣት መሞከር (እንደ ትግራይ ክልል)፣ የሚደገፍ፣ የሚበረታታ፣ እና የሚያስሸልም ተግባር እንጂ የሚያስተች ተግባር አይደለም።

ኧረ ለመሆኑ፣ ክልሎች ምርጫ በማድረጋቸው የፌደራል መንግሥቱም ሆነ ሌላ ማንኛውም አካል፣ ምኑ ይጎዳል፣ የትኛው መብቱ ይነካልና ነው፣ ሕገ-ወጡ የአብይ ቡድን ቢያንስ በአንፃራዊነት ሕጋውያን የሆኑትን ለማጥቃት፣ ይሄን ያህል በመመረር የሚሯሯጠው?

#ብኩን_ምርጫ_ቦርድ_ብኩን_መንግሥት!

(Shared again, because NEBE is persisting in its irresponsible act of provoking a civil war by arrogating to itself the power it doesn’t have, the power to prevent Regional elections.)