ግሸን መድኃኒት ቤት ለአትሌቶች የአበረታች ንጥረ ነገር ይሸጣል ..

ግሸን መድኃኒት ቤት ለአትሌቶች የአበረታች ንጥረ ነገር ይሸጣል መባሉን አጣጣለ

ግሸን መድኃኒት ቤት

መድኃኒት ቤቱ ኢፒኦ አበረታች ንጥረ ነገር መሆኑን አላውቅም ነበር ብሏል

(Ethiopian reporter) — የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን የዜና አውታር የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የሩጫ ድል ጀርባ ‹‹የግሸን መድኃኒት ቤት አበረታች መድኃኒት ሽያጭ ነው፤›› ማለቱን መድኃኒት ቤቱ አጣጥሏል፡፡

በዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ዘ ጋርዲያን እትሙ፣ የጀርመኑ ኤአርዲና የሆላንድ ሚድያ በጋራ ምርመራ አድርገናል ባሉት መረጃ መሠረት ግሸን መድኃኒት ቤቶች ያለ ሐኪም ትዕዛዝ አበረታች መድኃኒቶችን ለአትሌቶች እንደሚሸጥ ዘግበዋል፡፡

ይኸውም መድኃኒት በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ ከሚገኙት መድኃኒት ቤቶች አንዱ ከሆነው ግሸን መድኃኒት ቤት፣ አትሌቶች በቀላሉ መግዛት እንደቻሉ በዘገባቸው ጠቅሰዋል፡፡ በዘገባው ላይ የተጠቀሰው EPO (Erythropoientin) የተባለው መድኃኒት ሲሆን፣ ለቀይ የደም ሴል መመረት የሚጠቅም ኤንዛይም እንደሆነና ያለ ሐኪም ፈቃድ መግዛት እንደማይቻል የግሸን መድኃኒት ቤቶች ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አማከለች ሉሉ አብራርተዋል፡፡

ግሸን መድኃኒት ቤት፣ ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በሞናርክ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፣ የተጠቀሰው መድኃኒት አበረታች ንጥረ ነገር መሆኑን ዘገባው እስከተጠናከረበት ድረስ አለማወቃቸውን ወ/ሮ አማከለች ገልጸዋል፡፡

‹‹መድኃኒቱን በኩላሊት ሕመም ለሚሰቃዩና ለተለያዩ የካንሰር ሕሙማን ሕክምና የሚውልና በመርፌ የሚሰጥ ሲሆን፣ በዶክተር ትዕዛዝ በማዘዣ ወረቀት የሚሽጥ መድኃኒት ነው፤›› በማለት ወ/ሮ አማከለች አስረድተዋል፡፡

መድኃኒቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በኢቢጂ ሜዲቴክ ኢትዮጵያና አተማ በተባሉ ድርጅቶች በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር ባለው የምግብ የመድኃኒትና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ተመዝግቦና ተፈቅዶ አገር ውስጥ እንደገባ ተገልጿል፡፡

ዘ ጋርዲያን መድኃኒት ቤቱ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒቱ እንደሚሸጥና ለዚህም የካሜራ መረጃ እንዳለው ቢጠቁምም፣ በቀን ውስጥ ከ300 በላይ ደንበኞች እንደሚያስተናግዱና ችግሩም ከተከሰተ አጣርተው በቅርቡ እንደሚያሳውቁ የግሸን መድኃኒቶች ዋና ሥራ አስኪያጅ አስታውቀዋል፡፡