ጉቱ አበራ-“እወድሻለሁ ብሎ መንገር ሳይሆን ልክ እንደ ዓመት በዓል ያለ የደስታ ስሜት ነው መፍጠር የፈለኩት”

ጉቱ አበራ-“እወድሻለሁ ብሎ መንገር ሳይሆን ልክ እንደ ዓመት በዓል ያለ የደስታ ስሜት ነው መፍጠር የፈለኩት”

(bbc)—ሀዋነዋ (Hawanawa) ለወራት መልካም ዜና ለራቀው የኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ የተወሰነም ቢሆን እስትፋስ የሰጠ ሙዚቃ ነበር። የሙዚቃው ቪዲዮ በተለቀቀ በሰአታት ውስጥ ነበር የብዙዎችን ቀልብ የገዛው። እንዲህ ያሉ አስተያየቶችን መቀበሉን ሙዚቀኛውም ይናገራል።

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው ነገር ጥሩ እንዳልሆነ እናውቃለን። አንዳንዴ ግን እረፍት ያስፈልጋል። አንዳንዶቹ በዚህ ሙዚቃ እረፍት እናደርጋለን፤ ከዛ ተመልሰን ወደ ጭንቀታችን እንመለሳለን ይሉኛል (ሳቅ)›› ይላል ጉቱ።

ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በአዲስ ስራው ብቅ ያለው ጉቱ አበራ በኦሮምኛ ያቀነቀነው ሙዚቃ ቋንቋውን በማይናገሩ አድማጮች ዘንድም ከፍተኛ ተቀባይነትን አትርፎለታል።

ሀዋነዋ (Hawanawa) ለህይወት ዘመኔ እፈለግሻለሁ እንደማለት ነው። ግጥሙም ዜማውንም ራሱ ጉቱ ጽፎታል። ነገር ግን ሙዚቃውን ያቀናበረችው ሚራ ቲሩቼልቫም (Mira Thiruchelvam) ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራት። ጉቱ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ለሚራ እውቅናውን ሰጥቷል።

ጉቱ ማነው?

የተወለደው በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ መንዲ ከተማ ውስጥ ነው። የ16 አመት ታዳጊ ሆኖ ነበር ቤተሰቦቹ በስደት ወደ ሚኖሩባት ኖርዌይ ከ 12 አመት በፊት የሄደው። ከልጅነቱ ጀምሮ ከፍተኛ የሙዚቃ ፍላጎት እንደነበረው የሚናገረው ጉቱ ኖርዌይ ከሄደ በኋላ ወደ ጥሩ ሙዚቀኞች እየሄደ ሙዚቃን በመማር አዲስ ነገር ለመፍጠር እና በተለይም የፊውዥን ሙዚቃዎች ላይ አተኩሮ መስራት ጀመረ።

በሶሻል ወርክ እና አንትሮፖሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን የያዘው ጉቱ በሞያው ሶሻል ወርከር ነው። የትምርት ዝግጅቱም ለሙዚቃ ስራው እገዛ እንዳደረገለት ይናገራል፡፡

‹‹ስራዬ እኮ እሱ ነው፤ ወደ ሙዚቃ ግን ጠቅልዬ መግባቴ ነው መሰለኝ አሁንስ (ሳቅ)። ከሆነልኝማ ሙዚቃውን እመርጣለሁ። ግን አንድ ነገር እርግጠኛ ነኝ፤ እስከመጨረሻው ሙዚቃን እሰራለሁ›. ሲል ይናገራል።

“በኖርዌይ የኦሮሞን ሙዚቃ ወደ ዓለም መድረክ ለማምጣት ጥረት ማድረግ ጀመርኩኝ፤ በዚህም ምክንያት የተለያዩ አገር ሙዚቃዎችን በመጨማመር የሚሰራ ፋርገስ ፒል (Fargespill) የተሰኘ የሙዚቃ ባንድ አባል ሆንኩኝ።” የሚለው ጉቱ ከዚህ በኋላ የኦሮምኛ እና የምዕራብውያን ሙዚቃ በመቀላቀል መድረክ ላይ ማቅረብ መጀመሩን ይናገራል። ኦሮሚያ በሎ (ሰፊዋ ኦሮሚያ) የሚለው ሙዚቃ ከበርካታ ሰዎች ጋር እንዳስተዋወቀውም ለቢቢሲ ገልጿል። ከዚህም የተነሳ በኖርዌይ ንጉስና ንግሥቱቷ ፊት ለፊት ተጋብዞ መጫወቱንም ይናገራል።

ኦሮሚያ በሎ የሚለው ሙዚቃ ቅድሚያ የተጫወተው ሌላ ድምጻዊ ሲሆን፣ ኦሮምኛ የማይችሉ የባንዱ አባላትን በማሰልጠን በተለያዩ መድረኮች ላይ በጋራ ስራውን አቅርቧል። ጉቱ አበራ የተሰኘ የሙዚቃ ባንድንም ማቋቋሙን ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ወቅት ተናግሯል።

ጉቱ ስለ አዲሱ ሙዚቃው አጠር ያለ ቆይታ ከበቢሲ ጋር አድርጎ ነበር፡፡

ቢቢሲ- ሀዋነዋ የተሰኘው ነጠላ ቪዲዮህ ከወጣ ገና አንድ ሳምንት አለሞላውም፣ ነግር ግን በኢትዮጵያ ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች እጅግ ተወዶልሃል። ጠብቀህው ነበር?

ጉቱ አበራ- ይህ ስራዬ ለየት ብሎ የተሰራ ነው። ሀዋናዋም ለመያዝ የሚቀል እና ሳቢ መጠሪያ ነው። ሙዚቃው አዲስ ስለሆነ ነው መሰለኝ ብዙ ሰዎች መልዕክቶችን እየላኩልኝ ነው። በርታ ጥሩ ነው እያሉኝ ነው። ይህ ሙዚቃ የተወሰነ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ስለመጣ ሰዎች ዝግጁ አይሆኑም በሚል ምናልባት ተደማጭነቱ ላይ ጫና ያመጣ ይሆን ብዬ ሰግቼ ነበር። ግን ደግሞ ሙዚቃው በጥሩ ጥራት መሰራቱን ደግሞ አውቃለሁ። በቀጥታ መሳሪያዎች ነው የተቀረፀው። ስኬሉም ትንሽ ይለያል። የእኛ አገር ሙዚቃ ፔንታ ቶኒክ ነው፣ ይሄ ደግሞ በተለይ ኳየሮቹ በሌላ ስኬል ነው የገቡት። ስለዚህ በተለይ ከወጣቱ ትውልድ አድማጭ አገኛለሁ ብዬ አስቤ ነበር። ነገር ግን እንደዚህ ቶሎ ብዙ ተቀባይ አገኛለሁ ብዬ ግን አልጠበኩም። ስለዚህ ይሄንን ያህል ባልጠብቅም የተወሰነ ግምት ግን ነበረኝ።

በዚህ ሙዚቃ ደስ ያለኝ ነገር ቢኖር እስከዛሬ መልክት ከሚልኩልኝ አድናቂዎች ውጪ አዳዲስ አድናቂዎች አፍርቻለሁ። ይህ ሙዚቃ በኦሮምኛም ሆነ በአማርኛ ከሚዘፈኑ ዘፈኖች ለየት ያለ መልክ በመያዙ ምክንያት ይመስለኛል። ከመላው ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ መልክቶች እየደረሱኝ ነው። ጥሩ ነው ብለውኛል።

ቢቢሲ- በኦሮምኛ ሙዚቃዎች ውስጥ የፍቅር ዘፈኖች ብዙ ግዜ በውስጣቸው ሰም እና ወርቅ አላቸው፤ አንዳንዴ ስለ አገር ወይም ፖለቲካዊ መልክት ይይዛሉ። ሃዋነዋ ሰምና ወርቅ ይኖረው ይሆን?

ጉቱ አበራ-ይህ ሙዚቃ በውስጡ የተለየ መልክት አልያዘም፣ በግልፅ ከሚገልፀው የፍቅር መልክት ውጪ። እኔ ተወልጄ ያደኩት ወለጋ ውስጥ ነው። ይሄን ዘፈን ደግሞ ለሸዋ ልጅ ነው የዘፈንኩት። የጥበብ ስራው ላይ ትኩረት አድርጌአለሁ። ሁሉም ሰው የኦሮምኛ ሙዚቃን እንዲያዳምጥ እና ጥበባችን ከፍ እንዲል የፈለኩት እንጂ ምንም ፖለቲካዊ መልዕክት የለውም።

ቢቢሲ- የሙዚቃ ቪዲዮውም ሆ ሙዚቃው ከኦሮሞ እና ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በተጨማሪ የአፍሪካ መልክ የሚሰጡ ነገሮች አሉት። በተጨማሪም ወደ ኋላ አስርተ አመታትን ሄደህ ከባህል ባሻገርም የዘመን ህብር ፈጥረሃል። እንዴት ይህንን ለመፍጠር አሰብክ?

ጉቱ አበራ- ሙዚቃው እንደሰማሽው ተለዋዋጭ (ዳይናሚክ) ነው። መጀመሪያ ሲገባ በቤዝ ጌታር እና በፕርኪሽን እጀምራለሁ፤ መጨረሻ ላይ ደግሞ በጣም ሞቅ ብሎ ያልቃል። ቪዲዮውም እሱን ነው የሚመስለው። መጀመሪያ እኔ እና እሷ ቀስ ብለን ሳይክል እየነዳን እንሄዳለን ከዛ ጭፈራውም ከሙዚቃው ጋር ከፍ ይላል። ስለዚህ የሙዚቃ ቪዲዮው ታስቦበት ነው የተሰራው። ሌላው በቀጥታ የሙዚቃ መሳሪያ ስለተሰራ ድምጹ ተፈጥሮአዊ ነው።

ስለዘመን ስናወራ ደግሞ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከ 1970 እና 1980 ዎቹ በጣም ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ነበር። እኔ በተለይም የዚያን ግዜ የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች በበለጠ እወዳለሁ፤ አዳምጣለሁ። እናም ወደዚያ መመለስ እና ከዚያ መጀመር ነው የፈለኩት። አሁን ያለው ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ያኔ እንደነበረው ብቃት ላይ አይደለም። በአሊ ቢራ እና አለማየሁ እሸቴ ጊዜ ኢትዮ ጃዝ በጣም ያደገበት ወቅት ነበር። አሁንም እነርሱ ትልቅ ናቸው፤ አከብራቸዋለሁ።

እኔ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ገና ያልተነካ ነው ብዬ ነው የማምነው። በተለይ ከጥሩ ባለሞያዎች ጋር ቢሰራበት አዲስ ነገር መስራት ይቻላል። ስለዚህ ነው በኔም ስራ በዚህ መልኩ አዲስ ነገር መስራት የፈለግነው፣ ደግሞም አድርገነዋል።

በተጨማሪም አቀናባሪዋ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ታጠናለች እና ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ያላት እውቀት በጣም ጥልቅ ነው። ስለዚህ ለእርሷ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከሌሎች አይነት ሙዚቃዎች ጋር ማቀናበር አልከበዳትም። ሀዋነዋ ሙዚቃው ጃዝ፣ ብሉዝ፣ ራያ/ወሎ፣ አፍሮ፣ ኢቺሳ፣ ጌሎ፣ ሸጎዬ ምቶች የተቀላቀለበት ነው። ይሄ ብቻ ሳይሆን ችክችካ እና አፍሮ ቢትስም አሉበት። ስለዚህ አንዱን ሪትም የማይወድ ቢያንስ ሌላውን እንዲወድ አድርገን ነው የቀረጽነው።

እርሷ እንደ ባለሞያ ስታቀናብር እኔ አብሬያት ስለበርኩ በምፈልገው መልኩ ለመቅረፅ ችያለሁ። ስለዚህ ያ ለሙዚቃው ጣዕም የራሱ አበርክቶ እንዲኖረው አድርጓል።

ቢቢሲ- የሙዚቃ ቪዲዮህ የመብራት አጠቃቀሙ በጣም ፈካ ያለ ነው። ቅድም አንተም እንዳለከው የዘፈንህን ግጥም የማይሰሙ ሰዎችም ሙዚቃህን ወደውልሃል። የሃዋነዋ ግጥም ክሊፑ ላይ ከተጠቀምከው የመብራት ሴቲንግ ጋር ይገናኛል?

ጉቱ አበራ- የኔ ፍላጎት ታሪኩን መንገር ብቻ አይደለም። ስሜቱን መፍጠር ላይ ነበር ትኩረት ያደረኩት። ሰዎች ሙዚቃውን ሲሰሙ ደስተኛ ይሆናሉ፣ ቀለማቱን እንዲሁም የተቀረፀበት ቦታ የሚፈጥረው ስሜት አለ። የሙዚቃ ቪዲዮ ሲሰራ ልክ እንደ ፊልም ታሪኩን መንገር አይደለም ዋና አላማው፣ ሰዎች ስሜቱ እንዲሰማቸው አድርጎ መፍጠር ነው። እኔም ልክ እንደ አመት በዓል ያለ የደስታ ስሜት ነው መፍጠር የፈለግኩት። በአጠቃላይ ግጥሙ የፍቅር ነው፤ ነገር ግን አንድ ሰው እወድሻለሁ ብሎ መንገር ሳይሆን ልክ እንደ አመት በዓል ያለ የደስታ ስሜት ነው መፍጠር የፈለኩት። አድማጮቼ ስሜቱን ወድደውታል ብዬ አስባለሁ።

እንደ መሰናበቻ

ጉቱ አድናቂዎቹን ‹‹በጣም አመሰግናለሁ። አዳዲስ ሙዚቃ በቅርቡ ሰርቼ ለመመለስ እሞክራለሁ። ያላችሁኝን መልካም ነግሮች በሙሉ አከብራለሁ። እናም ታትሬ እንደምሰራ ቃል እገባላችኋለሁ። በቅርቡ ደግሞ በመድረክ ላይ እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ›› ሲል አመስግኗችኋል። አክሎም ‹‹አልበሜ በ ያዝነው የፈረንጆች አመት መጨረሻ፤ ካልሆነ ደግሞ 2022 መጀመሪያ ይወጣል ብዬ አስባለሁ። ከዛ በፊት አንድ ነጠላ ዜማ መስራቴ ግን አይቀርም›› ብሏል።