“ገዳ የወደፊቱ የፖለቲካ ስርዓት መሆን ይችላል” ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ

“ገዳ የወደፊቱ የፖለቲካ ስርዓት መሆን ይችላል” ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ

(bbcamharic)—በገዳ ስርዓት ላይ ጥልቅ የምርምር ስራን በመስራት ኤርትራዊው ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ ፈር ቀዳጅ ናቸው። ኢትዮጵያ ያላትን ሀገር በቀል የአስተዳደር ሁኔታም ከ45 ዓመታት በፊት በፃፉት “ኦሮሞ ዴሞክራሲ፡ አን ኢንዲጂኒየስ አፍሪካን ፖለቲካል ሲስተም” (OROMO DEMOCRACY : An Indigenous African Political System) በሚለው መፅሀፋቸውም ማሳየት ችለዋል።

ታኅሳስ 9/2011 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬታቸውን ያገኙት ፕሮፌሰር አስመሮም ስለገዳ ስርዓት እንዲሁም መሰል ሃሳቦች ላይ ያጠነጠነ ቆይታ ከቢቢሲ ጋር አድርገዋል።

• የቢላል አዛን የናፈቃቸው ሀበሾች

• ኢትዮጵያ ውስጥ የጠፉት ጀርመናዊ ፕሮፌሰር ዱካ አልተገኘም

ቢቢሲ፡ የገዳ ስርዓትን ለመመርመር ያነሳሳዎት ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር አስመሮም፡ መጀመሪያ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ስለ የኤርትራ ባህላዊ ስርዓት ማጥናት አቅጄ ነበር። ወቅቱ እንደ አውሮፓውያኑ 1961 ሲሆን የህዝባዊ ግንባር ኃርነት ኤርትራ እንቅስቃሴ ኤርትራ ውስጥ የተጀመረበት ጊዜ ከመሆኑ አንፃር በጊዜው የነበሩት የትምህርት ሚኒስትር ኤርትራ ሄደህ ጥናት እንድታደርግ አንፈቅድልህም አሉኝ። ምንም አማራጭ አልነበረኝም ተመልሼም ወደ አሜሪካ ሄድኩኝ።

በአንድ አጋጣሚ ቤተ መፃህፍት ቁጭ ብየ ስጨነቅ የቤተ መፃህፍቷ ሴትዮ አንተ ከኢትዮጵያ አይደለም እንዴ የመጣኸው የሚል ጥያቄ ጠየቀችኝ።

አዎ የሚል ምላሽ ስሰጣትም አንድ መፅሀፍ ከኢትዮጵያ በቅርቡ እንዳሰተሙ ነገረችኝ። ኤንሪኮ ቸሩሊ የተባለ ጣሊያናዊ ፀሀፊ የፃፈውን ‘ፎክ ሊትሬቸር ኦፍ ዘ ጋላ’ (Folk-literature of the Galla of Southern Abyssinia) የተሰኘ መፅሀፍ ሰጠችኝ።

መፅሀፉን ሳነበው በጣም ነበር ያስደመመኝ፤ በመፅሀፉ ውስጥ የገዳ ስርዓትም ሰፍሯል። እናም መነሻ የሆነኝ እሱ ሲሆን፤ አሱ የጀመረውንም ከዳር ለማድረስ ቆርጬ ተነሳሁ።

ቢቢሲ፡ በአካባቢው ምን ያህል ቆዩ?

ፕሮፌሰር አስመሮም፡ ሁለት ዓመት ያህል በኢትዮጵያ በኩል ቆይቻለሁ። ደርግ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ መመለስ አልቻልኩም። እናም ተሻግሬ በኬንያ በኩል ሶስት ዓመት ቆየሁኝ።

ቢቢሲ፡ ገዳ ስርዓትን ሲመራመሩ በጣም ያስደነቀዎት ነገር ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር አስመሮም፡ በምስራቃዊ አፍሪካ በሙሉ የዕድሜ አደረጃጀት ስርዓት አላቸው። ይህ ፖለቲካዊ ሳይሆን ማህበራዊ ስርዓት ነው። ስርዓቱም የተዘረጋው አንድ ሰው ወደ ሌላኛው በእድሜ የሚሸጋገርበትን ለመቀየስ ነው።

በቴክኖሎጂ ኢ-ፍትሐዊነትን የምትታገለው ኢትዮጵያዊት

በኦሮሞ በኩል ግን ያንን ማህበራዊ ስርዓት ወደተሟላ የፖለቲካ ስርዓት ቀየሩት። በገዳ ፖለቲካ ስርዓት መሠረት ስልጣን ሲወስዱ ገዳ የሚባል መጠሪያ ይኖራቸዋል።

የስልጣን ጊዜያቸውም ተገድቦ በመንበረ ስልጣንም ላይ የሚቆዩት ለስምንት ዓመታት ብቻ ነው። የሕይወት ሙሉ ፕሬዚዳንት የሚባል ነገር በኦሮሞ ዘንድ የለም (ሳቅ)።

እንዲያውም መጭው አባ ገዳ ገቢውን አባ ገዳ በቀና ስልጣኑን እንዲቀበል ያስገድደዋል። የኦሮሞ የጊዜ አቆጣጠር የተፈጠረውም ለዚያ ነው። በኦሮሞ (በቦረና) ጊዜ አቆጣጠር መሰረት ቦረናዎች ሰባት ከዋክብትና ጨረቃ አብረው የሚወጡበትን ወርና ቀን በመታዘብ ብቻ ያውቁታል። በውስጡ ሥልጣንን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘዴ አለው።

የገዳ ስርዓት አራት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ለምሳሌ ስድስት አባላት ያሉትን ጉሚን ብንወስድ የመላው ቦረና ጉባኤ ማለት ሲሆን ህግ ወሳኝና ከሁሉም በላይ የሆነ አካል ማለት ነው፤ ከባለሥልጣናቶቹም ጭምር። በጣም የሚያስገርመው፤ ውሳኔ ላይ የሚደረሰው በስምምነት ነው።

በምርጫ በአንድ ድምፅ በለጥኩኝ ብሎ ውሳኔ ማስተላለፍ አይቻልም በተቃራኒው ተማክረው ውሳኔ ላይ መድረስ አለባቸው። አዳዲስ ዲሞክራሲ ያላቸው ሀገሮች በወንበር ሲደባደቡ እናያለን፤ ይህ በገዳ ስርዓት ሊሆን አይችልም። እንኳን ይሄ ሊሆን ሰው ተራ ተሰጥቶት (ንግግር ለማድረግ) አባ ገዳውን ጨምሮ ማንም ሰው ሊያቋርጠው አይችልም።

• ”አዝማሪዎቻችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው”

ስርዓት ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ቋንቋ አላቸው። የኢትዮጵያ ቋንቋ ተመራማሪዎች የዴሞክራሲ ቋንቋን ለማጥናት መሄድ አለባቸው። እኔ ቋንቋውን ስለማልችል ማድረግ አልችልም። ይህንን ትልቅ ሳይንሳዊ ስርዓት መሆኑን ለማስረዳት ችያለሁ።


ቢቢሲ፡ የኦሮምኛ ቋንቋ ሳይችሉ ጥናቱን ማካሄድ ከባድ አልነበረም?
ፕሮፌሰር አስመሮም፡ እውነት ነው ከባድ ነው። ነገር ግን አማርኛም አቀላጥፎ መናገር የሚችል አንድ ጎበዝ የሆነ አስተርጓሚ ነበረኝ። እሱ ያልኩትን ያስተረጉማል። እናም ማታ ማታ እንፅፈዋለን። በኦሮምኛም ሆነ በእንግሊዝኛ የተሟላ መረጃ ማግኘት ችያለሁ።

ቢቢሲ፡ የገዳ ስርዓት ዘመናዊ አስተዳደር ሊሆን ይችላል?

ፕሮፌሰር አስመሮም፡ በደንብ፤ በአሁኑ መፅሀፌ የመጨረሻ ምዕራፍ ‘ገዳ ኢን ዘ ፊውቸር ኦፍ ኦሮሞ ዴሞክራሲ’ የምጠቅሰው ይህንኑ ነው። የወደፊቱ ትውልድ እንዴት ይጠቀምበታል የሚለውን ግልፅ አድርጎ የሚያመላክት ነው። እስካሁን በሰራሁት ጥናት ስርዓቱን በደንብ መመርመር እንጂ ወደፊት የሚያራምድ ሀሳብ አላቀረብኩም። ጉድለት ይሄ ነው ወይም ነቀፌታየ ይሄ ነው በሚል እንዲሁም ይሻሻል የሚል ሀሳብ አላቀረብኩም።

ይህኛው መፅሀፍ ግን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እንዴት መፍጠር ይቻላል የሚለውን ስትራቴጂ ይቀይሳል። እኔ ሀሳቤን አቅርቤያለሁ እንግዲህ የኦሮሞ ሊቃውንት ተከራክረውበት አሻሽለው ግብር ላይ ሊያውሉት ይችላሉ።

ቢቢሲ፡ የገዳ ስርዓት ውስጥስ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮችስ ምንድን ናቸው?

ፕሮፌሰር አስመሮም፡ ገዳ የተሟላ የፖለቲካ ስርዓት ቢሆንም ሁለት ጉዳዮች መስተካከል ይገባቸዋል። አንደኛው በስርዓቱ ውስጥ ሴቶች ሙሉ በሙሉ የሉም፤ ሊካተቱም ይገባል። ሁለተኛው፤ ስርዓቱ በትውልድ የተከፋፈለ ነው።

በዚህ ትውልድ ክፍፍልም መሰረት ልዩነቱ እስከ 50 ዓመት ሊደርስ ይችላል። በጣም ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ስላለ ለብዙ ስራ መጠቀም ከባድ ያደርገዋል፤ ሰራዊትም ማዘጋጀት አይቻልም።

ቢቢሲ፡ ስለ አዲሱ መፅሀፍ ጥቂት ይንገሩን

ፕሮፌሰር አስመሮም፡ አዲሱ መፅሀፌ አራት አዳዲስ ምዕራፎች የተጨመሩበት ሲሆን፤ የመጀመሪያው መፅሀፌ ከአርባ አምስት አመታት በፊት እንደመፃፉ በነዚህ አሥርት አመታት የተደረገው ለውጥ በሙሉ ተካቶበታል። ‘ገዳ ኢን ዘ ፊውቸር ኦፍ ኦሮሞ ዴሞክራሲ’ የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል።

ዲሞክራቲክ ኢንስቲትዩሽንስ ኦፍ ዘ ቦረና ኦሮሞ (ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በቦረና ኦሮሞ) የሚለው የመጨረሻው ምዕራፍ ነው። ወደፊት ምን ሊሆን ይገባዋል የሚለውንም አቅጣጫ አመላካች ነው። ይህ መፅሀፍ የተፃፈው ለመጪው ትውልድ ነው። ማስታወሻነቱም ለቁቤ ትውልድና ለቄሮ ነው።

ምክንያቱም በስራ ላይ የሚያውለው መጪው ትውልድ ስለሆነ ነው። የአሁኑ ትውልድ ብዙ ኃሳብ አለው ነገር ግን ሁሉም የተውሶ ዕውቀት ነው።

የኛ ዴሞክራሲ የእንግሊዝ ስርዓት ነው፤ ለጊዜው ሊያገለግል ይችላል። ነገር ግን የባዕድ ስርዓት ሰው እንደራሱ አያየውም፤ በሱም አይገዛም። እንደራሳቸው ቅርስም አያዩትም። እሱን የሚያፋልስ ኃይል ሲመጣ ምን ይሆናል? ምንም ማድረግ አይቻልም። የራሳቸው ከሆነ ግን ትግል ይጀመራል። በሁሉም ስርዓት መሠራታዊ የዲሞክራሲ መርሆች አሉ።

ለምሳሌ በአማራ ባህል አንድ አባባል አለ፤ ይህም ‘በሺ ዓመቱ ርስት ለባለቤቱ’ የሚል ነው። ኃያላን መጥተው መሬቱን ሊወስዱ ይችላሉ ሆኖም ግን ርስት ለባለቤቱ መመለሱ አይቀርም። እነዚህ ሀገር በቀል የዴሞክራሲ መርሆች ሊበለፅጉ ይገባል።

ከስድስት ሳምንታት በኋላ መፅሀፉ ይወጣል፤ እናም ተመልሼ የምመጣ ሲሆን፤ የመፅሀፍ ጉብኝትም በተለያዩ የኦሮሞ ዩኒቨርስቲዎች ላይ አካሂዳለሁ።