ጃዋር! ለማ! አብይ!እንግዲህ ስለ ሰሞኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማውጋት ግድ ከሆነ ሶስቱ ኦሮሞዎች መነሳታቸው ግድ ይሆናል።

ጃዋር! ለማ! አብይ! (ኦሮሚያ እጆችዋን ወደ ልጆችዋ ትዘረጋለች)

እንግዲህ ስለ ሰሞኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማውጋት ግድ ከሆነ ሶስቱ ኦሮሞዎች መነሳታቸው ግድ ይሆናል።

ጃዋር ጠንካራ የኦሮሞ ህዝብ ድጋፍ እንዳለው ይታወቃል። ያም ሆኖ ጃዋርን የማይደግፉ ኦሮሞዎችም አሉ። ማለትም የጃዋር ጉዳይ ሲነሳ ዝምታን የሚመርጡ ኦሮሞዎች ጥቂት አልነበሩም። ዛሬ ግን ሁኔታው ተቀይሮአል። ጃዋር በኦሮሞ ጉዳይ ላይ ወይም ባመነበት አጀንዳ ላይ እጁን ከሚንበለበል እሳት ውስጥ ለመጨመር እንደማያመነታ በትክክል ታይቶአል። ጠላቶቹ እንደሚጽፉት ጃዋር “የሳይበር አርበኛ” አይደለም። ዛሬ ዛሬ ዝምታን የመረጡ ኦሮሞዎች ጭምር ለጃዋር ባርኔጣቸውን እያነሱለት ነው። ኑረንበርግ – ጀርመን ላይ ለጃዋር የተደረገለትን አቀባበል የተከታተለ የኦሮሞ ህዝብ ወዳጅ ጉንጮቹ በእንባ መታጠባቸው ግድ ነው። የልቤን ልናገር? እኔ የተሰማኝ እንዲያ ነው። በዚህ አለም ላይ የህዝብን ክብር ከማግኘት በላይ ምን ታላቅ ነገር ይኖራል? ከቶ የለም። ሌላ ትንታግ ኦሮሞ ወጣት ካልቀደመኝ “ጃዋር መሐመድ” በሚል ርእስ 423 ገጾች ያሉት መጽሃፍ እየታየኝ ነው። በርግጥ፣ ገና አልወሰንኩም።

በውነቱ ህዝብን ማታለል አይቻልም። ህዝብ ይታገሳል እንጂ አይቸኩልም። የለማ መገርሳ ጉዳይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ማርሽ ቀያሪ እና ታሪካዊ እንደሚሆን የሚታመን ነው። ያም ሆኖ አብይ መሰሪ ፖለቲከኛ ነው ብዬ አላመንኩም። የአብይ መንገድ የተሳሳተ ሊመስል ይችላል። ወሬ በዝቶበታል። እሱም አልተጠነቀቀም። “ኦሮሞ የኔው ነው። የትም አይሄድም” የሚል ግምቱ ዋልታ ረገጥ ስህተት ሆነ። ሌሎች ሊጠቀሙበት በማሰብ እንደ መድሃኒት ቤቱ አርማ (እባብ) አንገቱ ላይ መጠምጠማቸውን ልብ ያለ አይመስለኝም። አብይ የኦሮሞን ህዝብ አፍኖ ሌሎችን ለመጥቀም የሚሰራ ተንኮለኛ ሰው ነው ብዬ ግን አላምንም።

እስኪ አስቡት?

የወያኔን ተንኮለኛ ሴራ ለማክሽፍ አብይ EPPን ከመመስረት በቀር ከቶ ሌላ ምን አማራጭ ነበረው? በርግጥ ትናንት ለማ መገርሳ VOA በተባለው ሚድያ የተናገረውን፥ Sony በተባለች ረጅም እድሜ አብራኝ በኖረች ሬድዮ ሰምቻለሁ።

ወይ መከራ!?

ለማ መገርሳ የሚለውም ልክ ነው። የሚጣል አባባል አልነበረውም። የበሰለ፣ የሚከበር፥ የሚያሳምን ስነ አመክኖአዊ አሳብ ነው የሰነዘረው። በዚህ መካከል ግን ድምጽዋን ደብቃ በሳቅ የምትፍለቀለቅው ወያኔ ሆና ተገኘች። ወያኔ ዳግም ከዳካ- አራራ ቤተመንግስት እጅዋና እግርዋ እንደማይግባ ታውቃለች። አሳምራ ታውቃለች። ጥቅልላ ነው መቐለ የገባች። ስለዚህ የቀራት ብቸኛ አማራጭ በትርምስ ውስጥ ጥቅም ማፈላለግ ብቻ ሆኖአል። በዚህ መሃል (እኔን ጨምሮ) ስንቶቻችን ሳናውቅ በተዘዋዋሪ የወያኔ መጠቀሚያ እንሆን ይሆን?

አብይ፥ ጃዋር እና ለማ ሚኒሶታ ላይ ሲተቃቅፉ እንዳየናቸው ዳግም ሩቅ አላሚ – ሩቅ አዳሪ ይሆኑ ዘንድ እመኛለሁ። የቱለማ ኦሮሞ እንደመሆኔ፥ የአድአ እና የፎቃ ጎሳ ኦሮሞ እንደመሆኔ ምኞቴ ይኸው ነው። የኦሮሞ የፖለቲካ ሃይሎች አደናቃፊ ግለሰቦችን ገለል እያደረጉ የመጨረሻውን ረጅም ሳቅ በጋራ እንዲስቁ እመኛለሁ።

እስካሁን ገላሳ ድልቦ፥ ሌንጮ ለታ፥ ዳውድ ኢብሳ፥ በቀለ ገርባ፥ መረራ ጉዲና፥ ጃዋር መሓመድ፥ ለማ መገርሳ፣ አብይ አህመድ እና ሌሎች የኦሮሞ ልጆችን አንዱን ከሌላው አበላልጬ ማየት አልቻልኩም። በፍጹም አልችልም። ለኔ አንድ ናቸው። የአባጋዳ ልጆች!!

ኢትዮጵያ ታበጽህ ኢደዊሃ ሃበ ደቃ! (ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ ልጆችዋ ትዘረጋለች!) የሚለውን ሳይንስ ማመን ይሻላል።

ዋቃ ጉራቻ ይቅር ይበለኝ እንጂ – እንደው ሳስበው አምላክ የኢትዮጵያን ጉዳይ መከታተል ሰልችቶት የተወው ይመስለኛል።

Tesfaye Gebreab


Kunoo akkanatti Afaan Oromoo Afaan Partii Badhaadhinaa gochaa jiran.


As #LammaaisNotalone coming up from different angles by brave Oromos why few opportunists: Brihanu Lenjiso, Leencoo Bati, Hundee Dhugassa and Amin JUNEDIN March with enemies?