ጀዋር መሀመድ የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጠ

ጀዋር መሀመድ የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጠ

ጀዋር መሀመድ መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ‘ፍትሕ አዳራሽ’ ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል። ጀዋር የእምነት ክህደት ቃሉን በሰጠበት ወቅት ክስ የተመሰረተበት ወንጀል ሰርቶ ሳይሆን በሁለት አላማዎች ምክንያት እንደሆነ አስረድቷል። የመጀመሪያው አላማ ጀዋርና ፓርቲው ኦፌኮ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ስላላቸው ገዢው ፓርቲ ከእነርሱ ጋር ተወዳድሮ መጪውን 6ኛ ሀገራዊ ምርጫ የሚያሸንፍበት እድል ስለሌለ እነርሱን ከምርጫው ለማስወጣት የተጠቀሙበት ዘዴ መሆኑን ተናግሯል።
 
ሁለተኛው አላማ ደግሞ በእርሱ እና በኦሮሞ ህዝብ ትግል ላይ ለአመታት ሲነዛ የቆየውን ገጽታን የማጠልሸት ቀጣይ አላማ ከግብ ለማድረስ የታለመ እንደሆነ ተናግሯል። በመቀጠልም ምንም የሰራው ወንጀል እንደሌለ እንዲሁም ውንጀላዎቹን ለመፈፀም የሚያበቃ ማንነትና የኃላ ታሪክ እንደሌለው በመግለጽ በክሱ ይዘት ላይ አስተያየቱን ሰጥቷል።
 
ጀዋር የኦርቶዶክስ እምነት አመራሮች ላይ ጥቃት እንዲደርስ መመሪያ ሰጥተሃል በማለት የተመሰረተበት ክስ ላይ በሰጠው አስተያየት እሱ ራሱ ብዝሀ ማንነት ባላቸው ቤተሰቦች መሀል ተወልዶ ማደጉንና አሁንም የሚኖረው በተመሳሳይ መልኩ መሆኑን ገልጿል። አክሎም “ለኔ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እንዲጠቁ ማድረግ ማለት በእናቴ በኩል ያሉ እልፍ አእላፍ ዘመዶቼ ላይ ጦርነት እንደማወጅ ነው። እና የራስን ግማሽ አካል ቆርጦ እንደ መጣል ይቆጠራል” ብሏል። ከቤተሰቡ አባላት ባሻገር የትግል ጓደኞቹና የግል ጠባቂዎቹ የሃይማኖት ስብጥር ኦርቶዶክስ፣ ሙስሊም፣ ፕሮቴስታንት እና ዋቄፈታን የሚያካትት በመሆናቸው አንዱን ሃይማኖት ነጥሎ የጥቃት ኢላማ ለማድረግ ቢሞክር በምንም ሁኔታ እነዚህ ወዳጆቹ ሊተባበሩትና አብረውት ሊሰሩ እንደማይችሉ ተናግሯል።
 
ጀዋር በሁለተኛነት ብሔር ብሔረሰቦችን አጋጭተሀል በሚል የቀረበበት የክስ ጭብጥ ላይ አስተያየቱን ሲሰጥ የብሄር ጭቆናን መታገሉን፣ ነገር ግን ትግሉ የሰላማዊ ትግልን መርህ ባከበረ መልኩ እንደነበረ አስረድቷል። በተጨማሪም “በአሰቃቂ የብሔር ጭቆና ዉስጥ ተወልዶ ወደ ነፃነት ትግሉ እንደተቀላቀለ ሰው፤ ጥርሱንም በኦሮሞ ህዝብ ትግል ዉስጥ እንደነቀለ ሰው፤ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ፖለቲካዊ ጭቆና ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛና ማህበራዊ መድልዎ እንዲቆም በገሀድ ድምፄን ከፍ አድርጌ መታገሌን በፍጹም አልክድም። እኮራበታለሁም!
 
በዚህ ትግል ዉስጥ ከተሳታፊነት እስከ አመራር በነበረኝ ሚና የብሔር ጭቆና እና መድልዎ ተወግዶ እኩልነት ፍትሀዊነትና ብዝሀነት እንዲሰፍን ተናገሪያለሁ፣ ፅፊያለሁ፣ አደራጅቻለሁ እንጂ የትኛዉም ብሔር እንዲገለል ለጥቃት እንዲጋለጥ አስቤ ምንም ነገር ሰርቼ አላዉቅም” ብሏል። ይህንኑ ሀሳብ ለማጠናከርም ጀዋር በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ካበረከተው አስተዋጾዎች መካከል 6ቱን በአብነት ጠቅሷል።
በህወሀት መራሹ ስርአት ላይ ተቀጣጥሎ የነበረው ህዝባዊ ወላፈን ሰላማዊውን በኦሮሚያ ውስጥ የሚኖር የትግራይ ተወላጅ ለጥቃት ሳያጋልጥ ለውጥ ማምጣት መቻሉ ጀዋር ሲመራው የነበረው ትግል ኢላማውም ሆነ እርምጃው በጨቋኝ ሥርአት ላይ እንጂ በብሔር ላይ ያነጣጠረ አለመሆኑን በማሳያነት አቅርቧል። አክሎም ሀምሌ 2010 ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ በቅድሚያ ወደ ባህር ዳር በመጓዝ በአማራ እና በኦሮሞ ፖለቲካዊ ማህበረሰቦች መካካል የነበሩ ታሪካዊና ወቅታዊ ቁርሾዎች በውይይት ተፈተዉ ሠላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲሳካ ወጣቶች ግፊት እንዲያደርጉ ጥረት ማድረጉን፣ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልል የድንበር ግጭት እንዲፈታ ያበረከተውን ከፍተኛ አስተዋጾ፣ በሐረሪ ክልል በሐረር ከተማ አስተዳደር እና በገጠር ነዋሪዎች መካከል የነበረ አለመግባባት ለመፍታት ያደረገውን ጥረት እንዲሁም በድሬደዋ ከተማ በየጊዜዉ እየተከሰተ የሰዉ ህይወት ሲቀጥፍና የንብረት ውድመት ሲያስከትል የነበረዉ የብሔር ግጭት እንዲያበቃ የሰራውን ስራ አብራርቷል።
 
በተጨማሪም ምንም እንኳን አሁን ያለንበት ሁኔታ በመንግስት ቸልታ የተነሳ ጥሩ ባይሆንም በምእራቡ የሀገራችን ክፍል ሰላም እንዲሰፍን ያበረከተውን አስተዋጾ በምሳሌነት ጠቅሷል። አያይዞም “የዛሬ ሁለት አመት ገደማ በምእራቡ የሀገራችን ክፍል መጠነ ሰፊ የብሔር ግጭት እና የመንግሥት መዋቅር መፈራረስ ተከስቶ የመንግሥት ሀላፊዎች እንኳን ወደ አከባቢው ዝር ማለት ባልቻሉበት ወቅት በዚህ ፋይል አብሮኝ ከተከሰሰዉ የትግል ጓዴ በቀለ ገርባ ጋር በመሆን ለህይወታችን አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ወደ ሥፍራው በመጓዝ ከፊንፊኔ ነቀምቴ ደምቢዶሎ አሶሳ ድረስ በየከተማው ህዝቡን በማወያየት እና በማረጋጋት የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ፣ ሥራ ያቆሙ የመንግስት ተቋማት ወደ ስራ እንዲመለሱ፣ ተቆራርጦ የነበረው ህዝብ ዳግም እንዲገናኝና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ እንዲንሰራራ ለማድረግ ችለናል” ብሏል።
 
በሶስተኛነት በትጥቅ ትግል መንግሥትን በማስወገድ ሥልጣን ለመያዝ ወጣቶችን ሲያደራጅ እና ሲያስታጥቅ ነበር የሚለው የክስ ጭብጥ ላይ አስተያየቱን የሰጠው ጀዋር ስለሰላማዊ ትግል ስታንፎርድ፣ ኦክስፎርድ እና ኮሎምቢያ ዪኒቨርሰቲዎች በዘርፉ ትልቅ ምርምር ካደረጉ ምሁራን የንድፍ ሀሳብ እና የተግባር እውቀት መቅሰሙን፣ ከህንድ እስከ ሰርቢያ በመጓዝ ጥናትና ምርምር በሚያደርጉ ተቋማት ዉስጥ በመስራት በስትራቴጂው አተገባበር ላይ ግንዛቤ ማዳበሩን፣ የአረብ ሀገራትን አምባገነኖች የናጠው ህዝባዊ አመጽን (አረብ ስፕሪንግን) በአማካሪነትና በተንታኝነት ለማገልገል እድል ማግኘቱን ገልጾ፤ የሰላማዊ ትግልን ዘዴዎች ከቄሮ እንቅስቃሴ ጋር በማዋሀድ የተገኘውን ድል አስታውሷል። “ስለሆነም ዕውቀቱ ያለኝን በተጨባጭም ውጤታማ የሆንኩበትን ሰላማዊ የትግል ስልት በመተው ወደ ትጥቅ ትግል የምዞርበት ምንም ምክንያት የለኝም” ብሏል።
 
በመጨረሻም በክሱ ወስጥ የተካተቱት ውንጀላዎች መሰረተ ቢስ መሆናቸውን እና እሱን ብቻ ሳይሆን የኦሮሞን ህዝብና የነፃነት ትግሉን የማጥላላት እና ስም የማጉደፍ ዓላማ ያነገበ መሆኑን ተናግሯል። ሀሳቡን ለማጠናከርም “ይህ ትግል ከተጀመረበት ከአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን አንስቶ የኦሮሞ ህዝብ የሚደርስበትን እኮኖሚያዊ ብዝበዛ፣ ፖለቲካዊ ጭቆናና የማንነት ድምሰሳን ሲቃወም የሌሎች ብሄሮች ጥላቻ ተደርጎ ሲፈረጅና ሲዘመትበት ነበር። ይሄው የኦሮሞን ህዝብ ትግል የማጥላላት እስትራቴጂ በዚህ ክስ ውስጥም በስፋት ተንፀባርቋል። እንቁውን የነፃነት ድምፅ የሆነውን አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን በገዳዮች ያጣው የኦሮሞ ህዝብ ሆኖ ሳለ በሺዎች የታሰረውም የኦሮሞ ህዝብ ነው። ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የተከፈተውም የኦሮሞ ህዝብ ላይ ነው። የመንግስት አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርቱ የአርቲስቱን መገደል ተከትሎ ከሞቱት 123 ዜጎች መካከል እጅጉኑ የሚበዛው ኦሮሞ መሆኑን ያመለክታል። በሌላ በኩል አብዛኛው ሟችም በፖሊስ እንደተገደሉ ያሳያል። አብዛኛውን ግድያ የፈፀመው መንግስት ሆኖ ሳለ በመንግስት ሚዲያዎች እና በሌሎችም የኦሮሞ ህዝብ የዘር ማጥፋት እንደፈፀመ በማድረግ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አድርገውታል። የሚዲያ ፍረጃ ዘመቻውም ሆነ ይህ ክስ ተበዳዩን ኦሮሞ እንደበዳይ ለማቅረብ አንገቱን ለማስደፋት እና አፉን ለማስያዝ በሌሎች ዘንድም እንዲፈራና አንዲጠላ በማድረግ ተሰሚነትና ተዓማኒነት በማሳጣት የጭቆናና የአፈና ሥርዓት ለማስቀጠል ነው” በማለት አስረድቷል።
አያይዞም በእርሱ ላይ በመንግስትና በፖለቲካ ባላንጣዎቹ ፕሮፖጋንዳ እና የስም ማጥፋት ውንጀላዎች ሲፈጸሙበት መቆየቱን አስታውሶ የአሁኑን አዲስ የሚያደርገዉ ለፍትህ እና ለርትዕ ቆሜያለሁ በሚለዉ የአቃቤ ህግ ማህተም ኦፊሴላዊ ሆኖ መቅረቡ መሆኑን ተናግሯል።