ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ ሁለት የደረጃ ምስክሮች ተሰምተዋል:: (ጥቅምት 24/2010 ዓ.ም )

ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ ሁለት የደረጃ ምስክሮች ተሰምተዋል:: (ጥቅምት 24/2010 ዓ.ም )

ዶ/ር መረራ ጉዲና

በእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና የክስ መዝገብ 1ኛ ተከሳሽ በሆኑት ዶ/ር መረራ ላይ ሁለት የአቃቤ ህግ የደረጃ ምስክሮች ዛሬ ጥቅምት 24/2010 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ተሰምተዋል፡፡

ከሳሽ የፌደራል አቃቤ ህግ በአጠቃላይ አራት የደረጃ ምስክሮችን በ1ኛ ተከሳሽ ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ እንዳቀረበ ከችሎቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በዛሬው ውሎ ምስክሮቹ ቀርበው ከመሰማታቸው በፊት ምስክሮቹ በመሰማት አለመሰማታቸው ላይ ክርክር አስነስቶ ነበር፡፡ በተከሳሽ ጠበቆች በኩል የተነሳው ክርክር ፍ/ቤቱ ሰኔ 30/2009 ዓ.ም የተከሳሽን መቃወሚያ ብይን በሰጠበት ወቅት የምስክሮቹ ዝርዝር ለተከሳሽ መድረስ የለበትም ብሎ ሲወስን አቃቤ ህግ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ የሰው ምስክሮች እንዳለው አለመግለጹን በማስታወስ፣ ዛሬ ላይ ቀደም ብሎ በመዝገቡ ላይ ያልተጠቀሱ ምስክሮች መሰማት የለባቸውም የሚል ነው፡፡

አቃቤ ህግ በበኩሉ በክስ በዝገቡ ላይ በአጠቃላይ (በየትኛው ተከሳሽ እንደሚመሰክሩ ባይገለጽም) የሰው ምስክሮች እንዳሉት ቀድሞ የገለጸ በመሆኑ ዛሬ የቀረቡት ምስክሮች በ1ኛ ተከሳሽ ላይ እንዲመሰክሩለት ችሎቱን ጠይቋል፡፡ ችሎቱ በበኩሉ የተከሳሽ ጥያቄ አግባብ ቢሆንም፣ በመዝገቡ ላይ ጠቅለል ባለ መልኩ ምስክር መኖሩ ቀድሞ ስለተጠቀሰ ምስክር መስማቱ አግባብ እንደሆነ ወስኗል፡፡

በሌላ በኩል አቃቤ ህግ አሉኝ ካላቸው አራት ምስክሮች መካከል ለዛሬ የቀረቡት ሁለቱ ብቻ ሲሆኑ፣ ቀሪ ሁለቱ በአድራሻቸው ባለመገኘታቸው እንዳልቀረቡለት በመግለጽ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ እንዲታዘዝለት ጠይቋል፡፡ ፖሊስ በበኩሉ ዛሬ ያልቀረቡትን ምስክሮች በአድራሻቸው ፈልጎ በቀጣይ ለማቅረብ በደብዳቤ ችሎቱን መጠየቁን ፍ/ቤቱ ገልጹዋል፡፡ በዚህም የተከሳሽ ጠበቆች ምስክሮቹ የሚመሰክሩት ጭብጥ ተመሳሳይ ከሆነ በተመሳሳይ ቀን እንዲሰሙ እንዲደረግለት ችሎቱን የጠየቀ ቢሆንም፣ አቃቤ ህግ ዛሬ የሚመሰክሩትና በዕለቱ ያልቀረቡት ምስክሮች በተለያየ ጭብጥ ላይ የሚመሰክሩ ስለሆኑ ዛሬ የቀረቡት እንዲሰሙለት ጠይቆ ምስክሮቹ ቀርበው እንዲሰሙ ተደርጓል፡፡

ዛሬ የቀረቡት ምስክሮች የሚመሰክሩበት ጭብጥ ተከሳሹ ዶ/ር መረራ ጉዲና ታህሳስ 14/2009 ዓ.ም ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ከኮምፒተራቸው፣ ሃርድ ዲስክና ከኢሜል አድራሻቸው ሰነዶች ታትመው ሲወጡ ተመለከትን ያሉትን ምስክሮቹ እንደሚያስረዱ በመግለጽ አቃቤ ህግ ጭብጡን አስመዝግቧል፡፡

በመጀመሪያ ምስክርነት የሰጡት አቶ ደራራ አልመው ሲሆኑ፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ፣ ወረዳ 14 ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛ መሆናቸውን የገለጹ ምስክር ናቸው፡፡ ምስክሩ ታህሳስ 14/2009 ማዕከላዊ ለግል ጉዳይ (ጓደኛየን ለመጠየቅ ነው ያሉት) በሄዱበት አጋጣሚ ኮማንደር አሰፋ የተባለ መርማሪ ለታዛቢነት ጠይቋቸው ፍቃደኛ ሆነው እንደታዘቡ ገልጸዋል፡፡ ምስክሩ ወደ ማዕከላዊ የሄዱበት ቀን የስራ ቀን ነው ቢሉም፣ ከሌላኛው (2ኛ ምስክር) ጋር ስራ አስፈቅደው ጓደኛየ ነው ያሉትን ሰው ለመጠየቅ መሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሆኖም ማዕከላዊ ከደረስሁ በኋላ ቶሎሳ የሚባለው ጓደኛየ (ያባቱን ስም የማያስታውሱት) ስልክ ሳይደውልልኝ ክፍለ ሀገር ሄዶ ሳላገኘው ቀረሁ›› ያሉት እኒህ ምስክር፣ በዕለቱ ታዘብሁ ያሉትን አስረድተዋል፡፡

‹‹ዶ/ር መረራ የእኔ ነው ካሉት ኮምፒውተር፣ ሃርድ ዲስክና ኢሜል በግምት 100 ገጽ የሚሆን ጽሁፍ ታትሞ ሲወጣ አይቻለሁ፡፡ ጽሁፎቹ ላይ ዶ/ር መረራ የእኔ ነው ብለው ከፈረሙ በኋላ እኔም በታዛቢነት ፈርሜያለሁ፡፡ ጽሁፎቹ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተጻፉ ናቸው፡፡›› ብለዋል ምስክሩ፡፡

በሁለተኛነት ቀርበው የተሰሙት ሌላኛው ምስክር ደግሞ ጌታቸው ዳንኤል ይባላሉ፡፡ የመንግስት ሰራተኛ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን መኖሪያ አድራሻቸው ደግሞ የካ ክ/ከተማ ወረዳ 10 መሆኑን ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ እኒህ ምስክር ለታዛቢነት ከመጠየቃቸው በፊት ማዕከላዊ ለምን እንደሄዱ ሲጠየቁ ከመጀመሪያው ምስክር ቃል በተጣረሰ መልኩ በግል ጉዳየ ብቻየን ነው የሄድሁት ብለዋል፡፡ ‹‹ከአቶ ደራራ አልመው ጋር አይደለም የሄድሁት፣ ብቻየን የሰነድ መልዕክት ለኮማንደር አሰፋ ለማድረስ በቅርብ አለቃየ ተልኬ ነው የሄድሁት፡፡ መልዕክቱን አድርሼ ስወጣ ነው ኮማንደር አሰፋ ታዛቢ ሁነኝ ብሎ የጠየቀኝ፡፡ አቶ ደራራን ያገኘሁት ከዚህ በኋላ እንጂ አብረን ወደ ማዕከላዊ አልመጣንም›› ብሏል፡፡ የመጀመሪያው ምስክር ግን ከዚህኛው ምስክር ጋር አብረው ከመስሪያ ቤታቸው አስፈቅደቀው እንደመጡ ነበር የገለጹት፡፡

ምስክሩ አቶ ጌታቸው ዳንኤል ምስክርነታቸውን ሲቀጥሉ ‹‹ታህሳስ 14/2009 ዓ.ም በታዛቢነት ማዕከላዊ በተገኘሁበት ወቅት ዶ/ር መረራ የእኔ ነው ባሉት ኮምፒውተር፣ ሃርድ ዲስክና ኢሜል አድራሻቸው ላይ ሰነዶች ታትመው ሲወጡ ተመልክቻለሁ፡፡ ሰነዶቹ ላይ ዶ/ር መረራ ሲፈርሙባቸው እኔም በታዛቢነት ፍርሜያለሁ›› ብለዋል፡፡ የመጀመሪያው ምስክር በግምት 100 ገጽ የሚሆን ጽሁፍ ታትሞ ወጥቷል ሲል ቢመሰክርም፣ ሁለተኛው ምስክር ግን በትክክል የተቆጠሩ 146 ገጾች በአማርኛ፣ ኦሮምኛና እንግሊዝኛ የተጻፉ ጽሁፎች ታትመው መውጣታቸውን መስክረዋል፡፡

ሁለቱም ምስክሮች በታዛቢነታቸው ወቅት ታትመው የወጡ ጽሁፎችን ይዘት እንደማያስታውሱና እንዳላነበቧቸው መስክረዋል፡፡ በሌላ በኩል የመጀመሪያው ምስክር ሁለቱም ታዛቢዎች (ምስክሮች) የአንድ መስሪያ ቤት ሰራተኞች እንደሆኑ ቢገልጽም፣ ሁለተኛው ምስክር የአንድ መስሪያ ቤት ሰራተኞች አይደለንም ሲል መስክሯል፡፡

ፍ/ቤቱ ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለህዳር 21/2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የዛሬውን የፍ/ቤት ውሎ ለመከታተል በፍርድ ቤት የተገኘው በርካታ ሰው ሲሆን፣ ችሎቱ ሞልቶ፣ ሂደቱን ገብተው ያልተከታተሉ ሰዎች ችሎቱ እስኪጠናቀቅ የችሎት በር አካባቢ ሆነው ሲጠባበቁ ውለዋል፡፡BBN DAILY NEWS
NOVEMBER 6-2017
የህዋሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ በፖለቲካዊ ችግር የተነሳ በድጋሚ ስብሰባ ተቀመጠ..,..ስኳር ጭኖ ወደኬኒያ ሊጓዝ የነበረው ድርጅት ክስ ሊመሰረትበት ነው… በህዋሀት የሚመራው ሜቴክ አቅም የሌለው ድርጅት የሚሉና ተመሳሳይ ዜናዎችን ይዘናልተከታተሉት