ድምፃችን ይሰማ: የአማራ ክልል መንግስት ለሞጣው ጥቃት በራሱ በተጠቂው ሙስሊም ላይ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀ ነው!

ድምፃችን ይሰማ: የአማራ ክልል መንግስት ለሞጣው ጥቃት በራሱ በተጠቂው ሙስሊም ላይ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀ ነው!

ድምፃችን ይሰማ

#EthioMuslims #EthioMuslimCommittee

የአማራ ክልል መንግስት ለሞጣው ጥቃት በራሱ በተጠቂው ሙስሊም ላይ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀ ነው!

በሞጣው የሽብር ጥቃት ታስረው የነበሩት 4 ኃላፊዎች ተፈትተዋል!

ክልሉ ለነጋዴዎች ካሳ በመስጠት ፋንታ አስቸኳይ ግብር እንዲከፍሉ አዟል!

ሰኞ ታህሳስ 27/2012 || አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

©ድምፃችን ይሰማ

በክልሉ ኃላፊዎች እና ፖሊሶች ድጋፍ ጭምር በተቀነባበረ ሁኔታ በሞጣ ከተማ በ4 መስጊዶች እና በሙስሊም የንግድ ተቋማት/ቤቶች ላይ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት አስመልክቶ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ለክልሉ መንግስት ያቀረባቸው 5 ጥያቄዎች እስካሁን ድረስ አልተመለሱም። ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ታስረው የነበሩ 4 የመንግስት ኃላፊዎችም ከእስር እንዲፈቱ ተደርጓል።

ካሁን ቀደም በክልሉ በተፈጸሙት የመስጊድ ጥቃቶች ወቅት የተደረገውም ይኸው ነው። በክልሉ በርካታ መስጊዶች እንዲቃጠሉ እና እንዲፈርሱ ቢደረግም አንድም የተፈረደበት ሰው የለም። እንዲሁ ለማስመሰል ያክል ጥቂት ሰዎች ለጥቂት ቀናት ብቻ ታስረው ይፈታሉ።

በሞጣው ጥቃት ከ400 በላይ ቤቶች እና ሱቆች እንዲቃጠሉ ተደርጓል። የክልሉ መንግስት ግን ኃላፊዎቹ ጭምር እጃቸውን ባስገቡበት ጥቃት ለተዘረፉት ሙስሊም ነጋዴዎች ካሳ በመክፈል እና በማቋቋም ፈንታ ግብር በአስቸኳይ እንዲከፍሉ ትእዛዝ አውጥቷል። ነግደው ቀረጥ የሚከፍሉት መንግስት ሳይጠብቃቸው ቀርቶ በደረሰባቸው ዘረፋ የተጎዱን ነጋዴዎች በማቋቋም ፈንታ ግብር መጠየቅ ፍጹም ኢ-ሰብዓዊነት ነው።

ይህ ሁሉ በደል የማይበቃ ይመስል የክልሉ መስተዳድር ለሞጣው ጥቃት ተጠያቂ ያደረገው ራሳቸውን ሙስሊሞቹን መሆኑ እጅግ አሳዛኝ ነው። ዛሬ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በሰጡት መግለጫ «ሕጋዊ የሆነውን መጅሊስ ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች በመስጊዶቹ ቃጠሎ መሳተፋቸውን» የገለጹ ሲሆን እርምጃ እንደሚወሰድም አያይዘው ገልጸዋል። ይህም ክልሉ እርምጃ የሚወስደው በሙስሊሞቹ ላይ መሆኑን እና ከደቦ ጥቃት እና ዘረፋ መልስ ለመንግስታዊ እርምጃ ሊዳረጉ እንደሚችሉ የሚያመላክት ነው። በድጋሚ የሞጣው ዓይነት ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችልም ይጠቁማል።

ለዚህ ሁሉ ጥቃት ክልላዊ መስተዳድሩ እና የተለየ ተልእኮ ባላቸው ሰዎች ተጽእኖ ስር በመውደቅ ሙስሊሙን ለመከፋፈል እየሰራ ያለው ከህወሃት ዘመን ጀምሮ ያልተለወጠው የአማራ ክልል መጅሊስ ዋነኛ ተጠያቂ መሆናቸው ሊታወቅ እና ለታሪክ ሊመዘገብ ይገባል!

ለእውነት የሚወግንና ለፍትህ የሚተጋ ዜጋን በመፍጠር አገራችንን ወደ ስልጣኔ እናሻግራለን!
አላሁ አክበር!