ይህ ሰው የጠቅላይ ሚኒስቴር ስራ ምን እንደሆነ የነገረው ሰው አለን?

ይህ ሰው የጠቅላይ ሚኒስቴር ስራ ምን እንደሆነ የነገረው ሰው አለን?

ችግኝ ሲተክል፣ ሲያጠጣ ጥሩ አርዓያ ነው አልን፡፡ ጽዳት ውስጥ ገባ፤ ተጨበጨበለት፡፡ ቀጠለና ሹፌር ኾነ፡፡ ከመሪዎች ጋር ቅርርብ ለመፍጠር የዘየደው ዘዴ ነው ተባለ፡፡ አስተዋዋቂ ሆኖ መጣልን፡፡ ከቀድሞ መሪዎቻችን ላይ ያልታየ የአርት ፍቅር ያደረበት መሪ ተባለ፡፡ ማስተዋወቁን ስራዬ ብሎ ያዘው፡፡ ለመጣው ሁሉ ስለቢሮው ዘመናዊነት ስለሰራቸው ፓርኮች አስደማሚ ውበት ተናግሮ አልጠግብ አለ፡፡ የሰሩት ሰዎች እንኳ መጠራጠር ጀመሩ፡፡ አሁን ደግሞ ከሸገር ወጥቶ ጫካ ለጫካ በመዞር ራሱ በካሜራው ውበት ማሳደድ ጀመረ፡፡ ይህ ሰው የጠቅላይ ሚኒስቴር ስራ ምን እንደሆነ የነገረው ሰው አለን? 
 
ዜጎች በየቀኑ በግጭት እየረገፉ ነው፡፡ አንድም ቀን ስለግጭቶች አልተናገረም፡፡ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጎዳው ሰው ቁጥሩ 3 ሚልዮን አልፈዋል፡፡ የብልጽግናን ገጽታ ያበላሻል ተብሎ ስለሱ አይነሳም፡፡ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ፍጥነት ቁልቁለቱን እየተጓዘ ከመሬት ጋር ሊላተም ተቃርበዋል፡፡ የስራ አጥ ቁጥሩ ጨምሯል፡፡ ስለዝህ ሁሉ አይነገርም፡፡ ለስራ አጡ ምንም የስራ ዕድል የማይፈጥሩ ፓርኮች ይዘከራል፤ ይወሳል፡፡ የድምጹ ሲሰለቸን አሁን ደግሞ እንደ ውቢት ኢትዮጵያ ፎቶውን ገጭ አድርጎ ራሱ ማስተዋወቂያ መስራት ጀምሯል፡፡ ምን ግራ የገባው ነገር ነው?

አንዱ ከገጠር የልጅነት ጓደኛውን ሊጠይቅ ወደ ከተማ ይመጣል፡፡ ጓደኛው በአክብሮት ከተቀበለው በኃላ (ጓደኛውን ብቻውን ትቶት ላለመሄድ) አብሮት ወደ ጉዳዩ እንድሄድ ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኛውም እሺ ግን ጥሩ ልብስ ስላልለበስኩ ከልብስህ አውሰኝ ይለዋል፡፡ ጓደኛውም የክት ልብሱን ያውሰዋል፡፡ የክት ልብሱን ሲያደርግ መንገደኛው ሁሉ እሱን እንደ ጌታ ባለልብሱ ጓደኛውን ደግሞ የሱ ሎሌ በሚመስል እይታ ያያቸው ጀመር ፡፡ ባለልብሱ ጓደኛው ነገሩ ከነከነው፡፡
 
የመጀመሪያው ቤት እንደገቡ ለእንግዶች ስለጓደኛው እንድህ ሲል ማስተዋወቅ ጀመረ፡፡ “ጓደኛዬ አብረን አፈር ፈጭተን ጭቃ አቡክተን ነው ያደግነው፡፡ አሁን ያደረገው የክት ልብስ ደግሞ እኔ ያዋስኩት ነው” ይላል፡፡ ጓደኛው በሁኔታው በማዘን ከሰዎቹ ቤት ሲወጡ ስለክት ልብሱ መናገር ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኛውም ተሳስቼ ነው ሁለተኛ አይለምደኝም ይላል፡፡
ሁለተኛው ቤት ሲገቡ ጓደኛውን ካስተዋወቀ በኋላ እንድህ በማለት ያክላል፡፡ “ያደረገው የክት ልብሱ የሱ የራሱ ነው” ይላል፡፡ ጓደኛውም በጉዳዩ በማዘን ለምን ስለልብሱ መናገር አስፈለገ ይለዋል፡፡ ልብሱ የራስክ መሆኑ እኔም አንተም እናውቃለን፡፡ስለልብሱ መናገር አያስፈልግም ይለዋል፡፡ እሺ ሁለተኛ አልናገርም ብሎ በመገዘት ይምላል፡፡
ወደ ሦስተኛው ቤት ሲገቡ እንደተለመደው ካስተዋወቀው በኃላ “ስለክት ልብሱ ምንም አልናገርም” በማለት ንግግሩን ይቋጫል፡፡ ጓደኛው እጅጉን ተናዶ ጥሎት ይሄዳል፡፡
 
ምን ለማለት ነው ጮርቃው በየግዜው የሰውን ሀሳብ እየሰረቀ የኔ ነው የሚለው ነገር አሁን አሁን ተባኖበታል፡፡ የራሱ ሀሳብ እንኳ ቢሆን እንደ ክት ልብሱ ባለቤት ዝምታ ያዋጣው ነበር፡፡ ቤተመንግስቱ እንድታደስ የቀረበው ሀሳብ የቆየ ነው፡፡ የእንጦጦውም ፓርክ ጉዳይም እንድሁ፡፡ አሁን AI ማዕከል ሀሳቡን ያመነጨው እሱ እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ የግዜ ጉዳይ እንጂ ይህም መጋለጡ አይቀርም!
 
“It is better to lead from behind and to put others in front, especially when you celebrate victory when nice things occur. You take the front line when there is danger. Then people will appreciate your leadership.”
— Nelson Mandela