“ያለን አማራጭ ውይይት ብቻ ነው” ጀዋር መሐመድ

“ያለን አማራጭ ውይይት ብቻ ነው” ጀዋር መሐመድ

በኦሮሚያ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ የሃገር ሽማግሌዎች እና ፖለቲከኞች ዛሬ ከሰዓት በሰጡት የጋራ መግለጫ ወጣቶች ከሰሞኑ ከተከሰተው ግጭት እራሳቸውን እዲቆጥቡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከትናንት በስቲያ በጀዋር ሞሐመድ መኖሪያ ቤት ከተፈጠረው ክስተት በኋላ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደው ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ በግጭት ቢያንስ 12 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ታውቋል።

ዛሬ ከሰዓት መግለጫ የሰጡት ፖለቲከኞች ወጣቶች እንዲረጋጉ እና ሠላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በጀዋር ሞሐመድ መኖሪያ ቤት በተሰጠው መግለጫ ላይ፤ ጀዋር ሞሐመድን ጨምሮ የኦነግ ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳ፣ ሌንጮ ባቲ፣ ከማል ገልቹ እና ሌሎች የፖለቲካ ሰዎች ተካፋይ ነበሩ።

ጀዋር መሐመድ

በመኖሪያ ቤቱ የተፈጸመውን ክስተት ካወገዘ በኋላ ይህ ‘ሸር’ የኦሮሞን ህዝብ በጣም ‘አስከፍቷል’ ብሏል። ጀዋር እሱን በመደገፍ ወጣቶች ያሳዩትን ድጋፍ አድንቆ “ከዚህ በላይ ኩራት ሊሰማኝ አይችልም” ሲል ተደምጧል።

“ይህን ህዝብ ለመንካት ለሚያስብ ኃይል መልዕክት ደርሶታል” ያለ ሲሆን፤ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር የሰጡት መግለጫ “ኃላፊነት የተሞላበት ስለሆነ ሊመሰገኑ ይገባል” ብሏል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝድነት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በጀዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት ላይ የተፈጸመው ክስተት “መሆን ያልነበረበት ትልቅ ስህተት ነው” ማለታቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ መልኩ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነርም ከክልሉ ምክትል ፕሬዝደንት ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ ሰጥተው ነበር።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው በኩላቸው ‘ጀዋር መሐመድ ለተከታዮቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው ልታሰር ነው፣ ጥቃት ሊደርስብኝ ነው በማለት ያስተላለፉት መልዕክት ስህተት ነው’ ብለው ነበር።

ጀዋር ዛሬ ከሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር በሰጠው መግለጫ “ቄሮዎች ላሳዩት አንድነት እናመሰግናቸዋለን። ይህችን ሃገር የሚያስተዳድረው መንግሥት ሰው የሚገደልበት እና የሚሸበርበት ጊዜ ማለፉን ማወቅ አለበት” ብሏል።

“እንደ አንድ ታጋይ እና እንደ አንድ ፖለቲከኛ ለዚህ መንግሥት ማሳወቅ የምፈልገው ህዝብ የማይፈልገው ነገር በፍፁም ተፈጻሚ ሊሆን አይችልም።… ይህንም ህዝቡ አረጋግጧል” ሲልም ተደምጧል።

“ያለን አማራጭ አንድ እና አንድ ብቻ ነው። ይህም ውይይት ብቻ ነው” ብሏል።

ትግላችንን ወደ የብሄር እና ኃይማኖት ግጭት ለመቀየር የሞከሩ ኃይሎች አሉ ያለው ጀዋር ይህንን ኃይል ወጣቶች መቆጣጠር በመቻላቸው አድናቆቱን አቅርቧል።

በቀጣዮቹ ቀናት ለተከሰተው ችግር ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር ውይይት አድርገን መፍትሄ እንሰጣለን ያለው ጀዋር፤ “ጉልበተኞች በጉልበታቸው ከቀጠሉ ግን ልክ እንደ ትላንቱ መፍትሄ ፈልግ እንልሃለን። …. አሁን ወደ ማረጋጋት ተመለሱ። ግን ሁል ጊዜም እንደምላችሁ ንቁ ሁኑ። አንድ ዓይናችሁን ብቻ ዘግታችሁ ተኙ” ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

ብ/ጄ ከማል ገልቹ

ብርጋዴር ጄነራል ከማል ገልቹ በቅርቡ የክልሉ የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ በመሆን አገልግለው ነበር። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲን ይመራሉ።

በአዳማ፣ በአምቦ እንዲሁም ሻሸመኔን በመጥቀስ በእነዚህ ስፍራዎች የሰዎች ህይወት እያለፈ መሆኑን እና ይህም በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።

“ጥያቄያችሁ ትክክል ነው። ለውጡ መንገዱን ስቷል። ይሁን እንጂ ትዕግስተኛ መሆን ሞኝነት አይደለም” ያሉት ብ/ጄ ከማል ገልቹ፤ ሁኔታዎች በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነ የሚጎዳው ሃገር የሚመራው ፓርቲ ነው ብለዋል።

ብ/ጄ ከማል ወጣቶች የአከባቢያቸውን ሰላም እንዲያስከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ገላሳ ዲልቦ

ገላሳ ዲልቦ ከኦነግ መስራቾች መካከል አንዱ ናቸው። አቶ ገላሳ በመካከላችን የተፈጠረው አለመግባባት እና ግጭት እንዲቆም ለማሳሰብ ነው የመጣነው ብለዋል። አቶ ገለሳ “ያላችሁን ብስጭት ገልጻችኋል፤ የከፈላችሁት መስዋዕትነት ይበቃል። አሁን በሰላም ወደ ቀያችሁ መመለስ አለባችሁ” ብለዋል።

የክልሉ ምክትል ፕሬዝደንት ‘የሰላም ተስፋ በውስጣችን ዘርቷል’ ያሉ ሲሆን፤ ሰላም በአስቸኳይ ወርዶ ህዝቡ ወደተለመደው የዕለተ ተዕለት እንቅስቃሴው እንዲመለስ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዳውድ ኢብሳ

የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በበኩላቸው፤ ወጣቱ የሚያደርገው ትግል ሌሎች ብሄሮችን እና ሃይማኖትን የሚጋፋ መሆን እንደሌለበት አሳስበዋል።

በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ከእስር መለቀቅ ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ይሆናል ብለዋል።