የፖለቲካ እስረኞች ሳይፈቱ የሚደረግ ምርጫ በጀት ከመፍጀት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።

የፖለቲካ እስረኞች ሳይፈቱ የሚደረግ ምርጫ በጀት ከመፍጀት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።

የብልጥግና መንግስት ዋና ዋና የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን ሰብስቦ አስሮ ይቅርና ቢፈቱ እንኳን ከእንግዲህ ትርጉም ያለው ፉክክር የሚታይበት ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል የፖለቲካ ምህዳር አለ ለማለት አያስደፍርም። ትናንት የተካሄደው የትዊተር ዘመቻ ይህን አፈና በማሳወቅ ረገድ ስኬታማ ነበር። #FreeAllPoliticalPrisonersInEthiopia የሚለው ሃሽታግ ከ230 ሺህ በላይ ጊዜ ትዊት ተደርጓል። በርካታ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት ሃላፊዎችና ተቋማት በጥሞና እንደሚከታተሉት ጥርጥር የለውም። በዘመቻው መከፋቱን ያልሸሸገው የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤትም ዛሬ መግለጫ አውጥቶበታል። አንዳንድ የኦሮሚያ ብልጥግና ሰዎችም በጥዋት ዘመቻው ላይ አስተያየት ሰተዋል። ዘመቻው የአጭር ጊዜ ግቡን መቷል ማለት ነው። አስተባባሪዎቹ ሊመሰገኑ ይገባል።
 
ማህበራዊ ሚዲያ ላይ እስረኞችን የሚያብጠለጥሉትና እንደ ጀግና የሚፎክሩት የኦሮሚያ ብልጥግና የፌስቡክ አዝማቾች ግን የማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ድምፃቸው ምነው አልተሰማም? የመጀመሪያው ቀን ሃሙስ በተደረገው ስብሰባ የአማራ ብልጥግና ማኮ አባላት ማይኩን አናስነካም ብለው መዋላቸውን ሰማሁ። የአማራ ብልጥግና ፅ/ቤት ሃላፊው አብረሃም አለኸኝ፤ ርእሰ መስተዳደሩ አገኘሁ ተሻገር ፤ የንግድ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ፤ ፀጋ አራጌና የመሳሰሉት በኦሮሚያ ፤ በፊንፊኔና በቤኒሻንጉል ስላሉ “የአስተዳደር ድክመቶች” እየተቀባበሉ ተናግረዋል። ፀጋ አራጌና ሌሎችም አስፈላጊ ከሆነ ከብልጥግና ፓርቲ ሊወጡ እንደሚችሉ መዛታቸውን ጭምር ምንጮች ነግረውኛል። ብልጥግና ካለኛ ቀፎ ነው የሚል እሳቤ አሳድረዋል ማለት ነው። ሌላው ቅሬታ “የትህነግ ሃይልን ያንበረከከው የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ቢሆንም በቂ ክሬዲት አልተሰጠውም” የሚል ነበር። በተመሳሳይ ይህንን ሃይል ወደ ቤኒሻንጉልና ሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች እንደሚያስገቡ የዛቱት አዴፓዎች በመጀመሪያው ቀን ከኦዴፓ ሰዎች ይህ ነው የሚባል ትችት አልገጠማቸውም።
 
ባይሆን በሁለተኛው ቀን ስብሰባ በተለይ የቤኒሻንጉል የአፋርና የሶማሊ ብልጥግና ፓርቲ የማኮ አባላት (የዞንና የወረዳ አመራሮች) አዴፓዎችን ክፉኛ ወቅጠዋቸዋል። እናንተ የምትሰብኩን ኢትዮጵያዊነት ከአማራነት የዘለለ አይደለም ተብለዋል። የምናውቃቸው የኦዴፓ የፌስቡክ አርበኞች ጭራቸውን ሸጉጠው የጦፈ ክርክሩን ሲከታተሉ እንደነበር ሰምቻለሁ። ባይሆን ከኦዴፓ መረር ያለ መልስ የመለሰው #ሞገስ_ኢደኤ ነው። ከብአዴን ወደ ኦፒዲኦ እንደኮበለለ የሚነገርለት ሞገስ ባደረገው ዘለግ ያለ ንግግር እናንተ መተከልን እንወስዳለን ስትሉ እኛም #የአሶሳን #የድሬደዋን #የራያን #የፊንፊኔን ጉዳይ መቆስቆስ አቅቶን አይደለም ሀገር ይረጋጋ ብለን ነው ብሏል።
 
ብልጥግና በሚል ባነር የተሰባሰቡ ሃይሎች ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ፤ ፌዴራሊዝሙ ላይ ፤ ህገ መንግስቱ ላይ ፤ የክልል አወቃቀሩ ላይ ፤ ፍትሃዊ ውክልና ላይ ፤ የስልጣን ክፍፍል ላይ ፤ ቋንቋ ላይና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ያላቸው የአመለካከት ልዩነት ሊታረቅ የሚችል አይደለም። በተለይ ከብአዴን (አዴፓ) ፍላጎት ጋር። በእርግጥ አሁን ለሚታየው ፈር የለቀቀ የአማራ ብሄርተኝነት ብአዴንን መውቀስ አስቸጋሪ ነው። ከአራት አመታት በፊት ለምሳሌ አቶ #ገዱ_አንዳርጋቸው ህገ መንግስቱ የብሄር ብሄረሰቦችን ጥያቄ የሚመልስ እንደሆነና ሙሉ ለሙሉ ልታጣጥለው የሚገባ ሰነድ እንዳልሆነ በልበ ሙሉነት ያስረዳ ነበር፤ #ንጉሱ_ጥላሁን ዋለለኝ መኮንን ያነሳው የብሔር ጥያቄ ተገቢ መሆኑንና ትግል መደረጉ አግባብ እንደሆነ በሚዲያ ይናገር ነበር። #አገኘሁ_ተሻገር አሁን ያለውን የፌዴራል አወቃቀር ሽንጣቸውን ይዘው ከሚከራከሩለት ውስጥ ዋነኛው ነበር። ዶ/ር
 
#አምባቸው_መኮንን የፊንፊኔ ልዩ ጥቅም ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ያስረዳ ነበር። #ደመቀ_መኮንን ከዛም አለፍ ብሎ ኢትዮጵያዊነትን ለሌሎች ለማስተማር መሞከር ጉዳት እንጂ ትርፍ የሌለው “የትምክህት አመለካከት ነው” ይል ነበር። እነዚህ ሰዎች ድንገት #አብይ_አህመድ የሚባል በኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ካባ የአማራ ብሔርተኝነትን የሚያቀነቅን ኦሮሞ ከኦዴፓ ውስጥ ሲወጣ ግራ ተጋቡ። ይህ ሰው ባህር ዳር ሄዶ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ሲሰድብና ኢትዮጵያን “ወደ ቀደመ ክብሯ” እመልሳታለሁ የሚል አርካይክ አስተሳሰብ ይዞ ብቅ ሲል ምን ይበሉ?! እነሱ ላይ መፍረድ አስቸጋሪ ነው። ዛሬ ለአብይ አህመድ ምስጋና ይግባውና ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን ሰው-በላ (cannibal)፤ አራጅ ፤ ያልሰለጠነ፤ ሳቬጅ እያሉ መግለጽ mainstream ፖለቲካ ሆኗል። የመንግስት ባለስልጣናት ሚዲያዎችና የፓርቲ ልሳኖች ያለ ምንም ሃፍረት ሌላውን ህዝብ በዚህ መልክ ሲገልፁ እንሰማለን። አብይ ሀገሪቱን “ወደ ቀድሞ ክብሯ” በጥሩ ሆኔታ እየመለሳት ነው። [የህዝቦችን ግድያ መቃወምና ለማስቀረት መታገል አግባብ ነው። ነገር ግን የቃላትን ሃይልና ዘለቄታዊ ጉዳት መረዳት ብስለት ነው]።
 
በርካታ ሆድ-አደር የኦዴፓ አባላት ያሉትን ያህል አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ቅሬታ ያላቸው አሉ። ነገር ግን ሃሳባቸውን ቢገልፁ አብይ አህመድ እንደተለመደው የብሄርተኝነት ታፔላ ለጥፎ ይበላናል ብለው ይፈራሉ። በዚህ መሃል የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ ለማንሳት የሚደፍር የለም። ትግል ከተደረገባቸው የቄሮ ጥያቄዎች ውስጥ የተመለሰ አንዳችም ጥያቄ አላየንም። እንደውም ግድያና አፈናው እየከፋ ነው የሄደው። ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ቢደረግ ይህን የዞረበት ፓርቲ ማንገዳገድ ከባድ አይሆንም ነበር። ይህን የተረዳው አብይ አሁንም የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታት ፍላጎት የለውም። ጭራሽ ከአሰረው ከስድስት ወር በኋላም “ሀገራዊ ሆኔታና የፖለቲካ አሰላለፍ” በሚል ርእስ በተሰራጨው ሰነድ “እንደ ጃዋር ያሉ ዋልታ ረገጦች..” የሚል ፅሁፍ እንደሰነቀረበት ሰምቻለሁ። ሰውዬው ግለሰቡን አስሮትም ያባንነዋል።
 
ባጠቃላይ የሁለቱ ቀን ስብሰባ ሲጠናቀቅ በወጣው መግለጫ በሙሉ ስምምነት የወጡ ለማስመሰል ቢሞከርም እውነታው ግን ስብሰባው በሽኩቻ የተሞላ ነበር። ከሁለት ሳምንት በኋላ ደግሞ የብልጥግና ጉባኤ መች መደረግ እንዳለበት የሚወስን የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ይደረጋል። አብይ ምንም ማህበራዊ መሰረት ሳይኖረው በጮሌነትና በጨበጣ ምን ያህል መጓዝ እንደሚችል በጋራ የምናየው ይሆናል። ምርጫውን በጉልበት አሸንፌ እቀጥላለሁ ካለም ኢህአዴግ በ 2015 ምርጫውን በዝረራ አሸነፍኩ ብሎ አውርቶ ሳይጨርስ የተቀጣጠለውን የቄሮ እንቅስቃሴ ማስታወስ ይገባል። ህዝብ በቃኝ ካለ ያ የማይደገምበት ምንም ምክንያት የለም። ለማንኛውም አፈናን የመታገልና የማጋለጥ እንቅስቃሴው በሁሉም መስክ መቀጠል ይኖርበታል። #የፖለቲካ_እስረኞች_ይፈቱ