የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል መንግስትን አስጠነቀቀ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል መንግስትን አስጠነቀቀ

በተስፋለም ወልደየስ 

(ethiopiainsider)የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል መንግስት ምርጫ ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ “በአፋጣኝ እንዲያቆም” አሳሰበ። ክልሉ “ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥል” ድርጊቱ የሚቀጥል ከሆነ፤ ምክር ቤቱ “በሕገ መንግስቱ እና ሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ስልጣን ለመተግበር እንደሚገደድ” አስጠንቅቋል።

ምክር ቤቱ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው ለትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ከቀናት በፊት በላከው ደብዳቤ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ባለ ሶስት ገጽ ደብዳቤ “የኢ.ፌ.ዲ.ሪ  ሕገ መንግስትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንዲከበር ስለማሳሰብ” የሚል ርዕስ ይዟል።

ባለፈው ሰኔ ወር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤነትን የተረከቡት አቶ አደም ፋራህ ፊርማ የሰፈረበት ደብዳቤው፤ ምክር ቤቱ “የሕገ መንግስቱ ጠባቂ” መሆኑን አስታውሷል። የትግራይ ክልል መንግስት የራሱን የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ጭምር እያካሄደው ያለው እንቅስቃሴም “ግልጽ የሆነ የሕገ መንግስት ጥሰት ነው” ሲል ወንጅሏል።

ፎቶ፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት

ምክር ቤቱ ተጣሱ ያላቸውን የሕገ መንግስት አንቀጾች በደብዳቤው ዘርዝሯል። የፖለቲካ መብቶችን ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንዲሁም ምርጫን በሚመለከት ህጎችን የማውጣት ስልጣን ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን ያነሳው ደብዳቤው ይህም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 51 (15) እና 55 (2) (መ) መደንገጉን ጠቅሷል።

በፌደራል እና በክልል የምርጫ ክልሎች የሚደረጉ፤ ነጻ እና ትክክለኛ ምርጫዎችን በገለልተኝነት ማካሄድ የሚችለው፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ መሆኑ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 መደንገጉንም ደብዳቤው ጠቁሟል። በዚሁ የሕገ መንግስት አንቀጽ፤ የምርጫ ቦርድ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሾሙ ያመላከተው ደብዳቤው ይህም “በክልል ደረጃ የሚቋቋም የምርጫ ቦርድ ያለመኖሩ” ማሳያ እንደሆነ አብራርቷል።

የትግራይ ክልል ስድስተኛውን ዙር ምርጫ በክልሉ እንዲካሂድ ወስኖ እየተንቀሳቀሰ ያለው፤ እነዚህን የሕገ መንግስት አንቀጾች እና ባለፈው ዓመት የጸደቀውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ በጣሰ መልኩ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤው አትቷል። ክልሉ ስልጣን በራሱ ምርጫ ለማካሄድ የወሰነው ውሳኔ እና ይህንኑ ለማስፈጸም እያደረገው ያለው እንቅስቃሴ፤ ከሕገ መንግስቱ እና ከምርጫ ህጉ ጋር ከመቃረኑ ባሻገር፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሰኔ 3፤ 2012 የሰጠውን ውሳኔ “ያላከበረ ነው” ሲል ተችቷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ ወር ባካሄደው ስብሰባ፤ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዲራዘም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። ምክር ቤቱ ከውሳኔው ላይ የደረሰው፤ ምርጫ ማራዘምን በተመለከተ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት የውሳኔ ሀሳብ ካቀረበለት በኋላ ነበር። ምክር ቤቱ ከምርጫ ማራዘም ውሳኔ ላይ የደረሰው እንዴት እንደነበር ለትግራይ ክልል በጻፈው ደብዳቤ መግቢያ ላይ ዘርዘር አድርጎ አስቀምጧል።

%
</p data-lazy-src=