በመቀሌ ኤርፖርት የተያዙት ታጣቂዎች የፌዴራል ፖሊስ አባላት መሆናቸው ተገለጸ

በመቀሌ ኤርፖርት የተያዙት ታጣቂዎች የፌዴራል ፖሊስ አባላት መሆናቸው ተገለጸ


በመቀሌ ኤርፖርት የተያዙት ታጣቂዎች የፌዴራል ፖሊስ አባላት መሆናቸው ተገለጸ

(ethiopianreporter)—–እሑድ ሐምሌ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አየር ኃይል አውሮፕላን መቀሌ አሉላ አባነጋ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እንደደረሱ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ታጣቂዎች፣ የፌዴራል ፖሊስ የኤርፖርት ጥበቃ አባላት እንደሆኑ ተገለጸ፡፡

ታማኝ የዜና ምንጮች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኤርፖርት ጥበቃ አባላት የታጠቁ ስለሆኑ በሲቪል አውሮፕላን ሊጓጓዙ አይችሉም፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር ኃይል አንቶኖቭ አውሮፕላን ቅዳሜ ዕለት ከደብረ ዘይት አየር ኃይል በመነሳት ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እንዳረፉ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ አርባ የሚሆኑ የኤርፖርት ጥበቃ አባላትን ከቦሌ አሳፍሮ ወደ መቀሌ ኤርፖርት ቢቃረብም፣ በነበረው የአየር ሁኔታ ምክንያት ማረፍ ባለመቻሉ ተመልሶ ወደ ደብረ ዘይት ለመብረር ተገዷል፡፡

አውሮፕላኑ የቴክኒክ እክል የነበረበት በመሆኑ ተለውጦ በምትኩ L100 (C130) አሜሪካ ሠራሽ ኸርኩለስ አውሮፕላን በማግሥቱ 40 የኤርፖርት ጥበቃ አባላትን አሳፍሮ ወደ መቀሌ በሰላም ከበረረ በኋላ፣ የጥበቃ አባላቱን አውርዶ ወደ ደብረ ዘይት አየር ኃይል እንደተመለሰ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ይሁን እንጂ ለምን ተልዕኮ እንደተላኩ ጥርጣሬ ያደረበት የትግራይ ክልል ፖሊስ፣ የኤርፖርት ጥበቃ ዲቪዚዮን አባላቱን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ በማድረግ ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ሁኔታው እንደተጣራ የጥበቃ አባላቱ ይፈታሉ ሲሉ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመረጃ ልውውጥ የተፈጠረ ክፍተት የፈጠረው ችግር ነው፤›› ብለዋል ምንጮች፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር የጠየቃቸው የትግራይ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳዒ ኃለፎም፣ ‹‹ተራ አሉባልታ ነው›› ሲሉ ዜናውን አጣጥለውታል፡፡