የግዢ ስርዓት መጓተትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመድሃኒት አቅርቦት ላይ ችግር

የግዢ ስርዓት መጓተትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመድሃኒት አቅርቦት ላይ ችግር እየፈጠረ ነው ተባለ

ምንዛሬ እጥረት በመድሃኒት አቅርቦት ላይ

(fanab) — አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የግዢ ስርዓት መጓተት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመድሃኒት አቅርቦት ላይ አሁንም ችግር እየፈጠረ መሆኑ ተገለፀ።

የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በ2009 በጀት ዓመት አፈፃፀሙ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተወያየ ነው።

ኤጀንሲው በ2009 በጀት ዓመት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከሀገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾች ግዢ መፈፀሙን አስታውቋል።

ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ17 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው ኤጀንሲው ያስታወቀው።

በመድረኩ ላይ 11 የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች አፈጻጸማቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ በዚህም ዝቅተኛው አፈጻጸም 70 በመቶ እንዲሁም ከፍተኛ 85 መሆኑ ነው የተገለፀው።

ይህ ማለትም አንዳቸውም እቅዳቸውን 100 በመቶ ማሳካት እንዳልቻሉ ያሳያል ተብሏል።

ለዚህ በችግርነት ከተጠቀሱት ውስጥ አንደኛው የግዢ ስርዓት መዘግየት ሲሆን፥ ሌላኛው ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው።

አምራቾች የውጭ ምንዛሬ ጠይቀው ከ7 እስከ 8 ወር እንደጠበቁ የሚናገሩ ሲሆን፥ ይህም በአፈጻጸማቸው ላይ ትልቅ ተፅእኖ እንዳሳደረ ተናግረዋል።

የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በበኩሉ ችግሮቹ መኖራቸውን አምኗል።

ኤጀንሲው በ2010 በጀት ዓመት በመድሃኒት አቅርቦቱን የሚያስተጓጉሉ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ በመስራት ለመፍታት እንደሚሰራ አስታውቋል።

በቤተልሄም ጥጋቡ