የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ተገለጸ

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ተገለጸ

(fanabc)—አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጥቅምት 30 ይወጣል ተብሎ የነበረው ከ42 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኢንጅነር ዘሪሁን አምደ ማሪያም በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓቱን የተራዘመው ከሶፍትዌር ጋር በተገናኘ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ዕጣው የሚወጣበት ሶፍትዌር ማሽን በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ስር እንደነበረ የተነገረ ሲሆን ይህ ደግሞ የህጋዊነትና የፍትሃዊነት ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑ ሶፍትዌር ማሽኑ ቤቱን መገንባትና ማስተዳደር በአዋጅ በተሰጠው የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ስር እንዲሆን የከተማ አስተዳደሩ መወሰኑም ተገልጿል።

እንዲሁም የ40/60 ቁጠባ ቤቶቹን ተረክቦ የማስተላለፍ ኃላፊነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስረ የነበረ ሲሆን ይህ አሰራርም ተገቢ ባለመሆኑ ውሉ ተቋርጦ ቤቶቹን የሚገነባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮ እንዲያስተላልፍ ተደርጓል በማለትም ኃላፊው ገልፀዋል።

ለዕጣው መዘግየትም እነዚህ ምክንያቶች ዋነኞቹ በመሆናቸው፥ በቅርብ ተስተካክሎ ባለ ዕድለኞች የቤት ባለቤት እንደሚሆኑ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ሶፍትዌሩን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮ ጋር የማዋሃዱ ስራ 70 በመቶ መድረሱንም ተገልጿል፡፡

ቢሮው በበጀት ዓመቱ 132ሺ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ የያዘ ሲሆን በቅርብ ለባለ ዕድለኞች ይተላለፋሉ የተባሉት ከ42 ሺህ በላይ እንደሆኑም ኃላፊው አብራርተዋል።

ዕጣው ከዚህ ቀደም ጥቅምት 30 እንዲወጣ መርሃግብር ተይዞለት እንደነበር ይታወሳል፡፡