የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቆሻሻ ማብላያ ግንባታ እንዲቆም ተደረገ

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቆሻሻ ማብላያ ግንባታ እንዲቆም ተደረገ

(ena) —ጅማ 14/2010 ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢያቸው ሊያስገነባው የነበረውን የፍሳሽ ቆሻሻ ማብላያ ግንባታ እንዲቆም መደረጉ ተገለጸ፡፡

የቆሻሻ ማብለያ ሊገነባ ታቅዶ በነበረበት ቦቼ ቦሬ ቀበሌ “ሰደቻ ሰፈር” ነዋሪ ከሆኑት መካከል አቶ ታጁዲን መሃመድ በሰጡት አስተያየት የማብላያ ግንባታው ሊሰራ የታቀደበት ቦታ በርካታ ሕዝብ በሚኖርበት ሰፈር በመሆኑ በተደጋጋሚ ያቀረቡት ቅሬታ መፍትሔ በማግኘቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

“ቆሻሻ ማብለያው ሰፊ መሬት የሚይዝ በመሆኑ ለጤንነት ጠንቅ ሊሆን ይችላል ከሚል ስጋት በተጨማሪ ከዛሬ ነገ ተነሱ እንባላለን በሚል ፍራቻ ላለፉት 15 ዓመታት ያልተረጋጋ ሕይወት ስንመራ ቆይቷል” ብለዋል።

በእዚህ ምክንያት መኖሪያ ቤት ለመስራት፣ ለማደስና ከመንግስት ጋር ሆነው ማህበራዊ የልማት ተቋማትን ለማስፋፋት መቸገራቸውን አመልክተዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኮራ ጦሽኔ ስለ ሁኔታው ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ በተለምዶ ሰደቻ በሚባለው ሰፈር ከተቋሙ የሚወጣውን ፍሳሽ ቆሻሻ ለማስወገድ የሚያስችል ግንባታ ለማካሄድ ዩኒቨርሲቲው በ1995 ዓ.ም መሬት መረከቡን አስታውሰዋል።

“በወቅቱ መሬቱን ስንረከብ በአካባቢው የነበሩ ቤቶች 98 ብቻ ነበሩ፤ ቦታ ተረክበን ግንባታ ለመጀመር ስንዘጋጅ ተጨማሪ 540 ቤቶች በመሰራታቸውና ዩኒቨርሲቲው ለሁሉም ካሳ ከፍሎ ለማስነሳት አቅም ስለሌለው ግንባታው ሳይጀመር ቀርቷል” ብለዋል፡፡

የቆሻሻ ማብለያው በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ላይ ጉዳት እንደሚያደርስና ከከተማ ልማት አንጻርም አዋጪ አለመሆኑ በኦሮሚያ ክልል አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን መረጋገጡን አቶ ኮራ ገልጸዋል።

” በአሁኑ ወቅትም በሚሰጣቸው ተለዋጭ ቦታ ላይ ግንባታውን ለማካሄድ ስምምነት ላይ ተደርሷል” ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በግቢው ውስጥ የቆሻሻ ማብለያ በመስራትና በማጓጓዝ ችግሩን እየፈታ የሚገኝ ሲሆን በዘላቂነት ለመፍታትም ጥናት የሚያጠና ከፍተኛ ባለሙያዎችን የያዘ ኮሚቴ መቋቋሙን አስረድተዋል።

የጅማ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልማሊክ ሙሳ በበኩላቸው “ከጅማ ዩኒቨርሲቲና ከሆስፒታሉ የሚወጣው ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አደገኛ በመሆኑ ታክሞ መወገድ ይኖርበታል” ብለዋል ፡፡

“ጅማ ዩኒቨርሲቲ ቀድሞ ሊያስገነባ የነበረው የቆሻሻ ማብላያ ብቻ ነበር” ያሉት ኃላፊው፣ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ቆሻሻን የሚያክም ማብለያ በሌላ ቦታ እንዲያስገነባ ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል ።

የኦሮሚያ አካባቢ ጥበቃ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ቦና ያደሳ በበኩላቸው “ዩኒቨርሲቲው የቆሻሻ ማብለያውን እንዳይገነባ የተደረገው አካባቢውን በመበከል በነዋሪዎች ላይ የጤና ጉዳት እንደሚያስከትል በጥናት በመረጋገጡ ነው” ብለዋል ።

ዩኒቨርሲቲው ጥናት በማድረግና ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሕብረተሰቡ ላይ ምንም አይነት የአካባቢ ብክለት የማያደርስ የቆሻሻ ማብላያ እንዲሰራ ድጋፍ እንደሚደረግለተም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የካቲት 2 ቀን 2009 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲው የሚወጣው ፈሳሽ ቆሻሻ አካባቢን እየበከለ እንደሚገኝ መዘገቡ ይታወሳል፡፡