የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ስለቀድሞተማሪው ሽመልስ ምስክርነት…!

የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ስለቀድሞ
ተማሪው ሽመልስ ምስክርነት…!


Leaked News አፈትላኪ ዜናዎች
የዛሬ ሦስት ሳምንት ገደማ፣ በአሜሪካ በነበረኝ ቆይታ፣ ሜሪላንድ አካባቢ ወደ አንድ ትልቅ የምግብ ማዕከል(Food Court) አምርቼ ነበር፡፡

“ምን ዓይነት ምግብ ልብላ፤” እያልኩ እያሰብኩ፤ ከአንደኛው ረድፍ ወደ አንደኛው ረድፍ በምዘዋወርበት ጊዜ፤ አንዲት በፍልስፍና የተመረቀች ተማሪዬን በሥራ ገበታዋ ላይ አገኘኋት፡፡ ከባለቤቷ እና ከልጇ ጋር እንደመጡ ነገረችኝ፡፡ እኔም አሜሪካን ሀገር ተጋብዤ እንደመጣሁ፣ በቅርብም ወደ ቦስተን ባለቤቴን እና ልጄን ለመጠየቅ እንደምሔድ ነገርኳት፡፡ በመገናኘታችንም ኹለታችንም በጣም ደስ አለን፡፡

ድንገት “ዶ/ር” አለችኝ፤ “ሽመልስ አብዲሳ (የክፍል ጓደኛዋ ስለነበር) የፕሌቶን ሪፓብሊክ፣ በሚገባ አንብቧል፡፡” አለችኝ፡፡ ይኸንንም ስትል፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያለ፣ የPolitical Philosophy ኮርሱን በሚገባ ተከታትሎ ገቢራዊ እንዳደረገው እየጠቆመችኝ ነበር፡፡

እኔም “እከሊት” አልኳትና፣ ”መች ይህ ብቻ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቆ ለመረዳት በእጅጉ የጣረ ሰው ነው፡፡ በተለይም፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ ታሪክ ህልው መኾን፣ የፈጠረውን ልዩ የታሪክ አንድምታ የተረዳ ሰው ነው፡፡ ይህም ማለት፤ ሽመልስ የኦሮሞን ሕዝብ ትልቅነት እና አኩሪ ታሪክ የተቀበለ እና የሚያውቅ ምሁር ነው፡፡” አልኳት፡፡

ከልጅቱ ጋር ከተነጋገርነው ቁምነገር በተጨማሪ፣ በInstitute of Human Right የድኅረ ምረቃ ተማሪ በነበረበት ጊዜ፤ የመመረቂያ ጽሑፉን፤ በአማካሪነት እና በመምህርነት አብሬው ለኹለት ዓመታት ቆይቻለሁ፡፡ የጥናቱ ትኩረት “በነጻነት እና ሥርዓታዊነት (Liberty and Order) መካከል ያለውን ግንኙነት እና ቅራኔ” በመፈተሸ፤ ከሔግል እስከ አይዛያ በርሊን የጻፉትን የፍልስፍና ደርሳናት መርምሮ ጥናቱን አቅርቧል፡፡

በዚህ የትምህርት ሒደት እና በጥናትና ምርምሩ ያከማቸው ምሁራዊ ጥሪት፤ አኹን ለደረሰበት ከፍተኛ ኃላፊነት በእጅጉ ይረዳዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በመጨረሻም፤ ሽመልስን፣ ባለቤቱን፣ ወላጅ አባቱን፣ በተለይም የዛሬ 12 ዓመት ጊንጪ በወላጆቹ ቤት ግብዣ ተደርጎልኝ ከመቀመጫቸው ተነስተው “ልጄን ሰጥቼሀለሁ” ላሉኝ እናቱ፣ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ሽመልስም፤ በተሠየመበት የሥራ ገበታ ለሀገሩ ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንኳን ደስ አለህ፣ እንኳን ደስ አለን፡፡


‹የአብዲሳ አጋ ልጅ›

በዲ/ን ዳንኤል ክብረት

ከወራት በፊት አቶ ፍጹም አረጋ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ እያለ ለሥራ ጉዳይ ወደ ቢሮው ሄጄ ነበር፡፡ አንድ ረዘም ደልደል ያለ፣ ፈገግታ ከፊቱ የማይጠፋ ሰው አገኘሁ፡፡ ከዚያ በፊት በአካል አግኝቼው አላውቅም፡፡ እርሱ ግን እንደሚያውቀኝ ነገረኝ፡፡ በተደጋጋሚ ስሄድ እዚያው ቢሮ በሥራ ተጠምዶ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከመቀራረብ ብዛት ተግባባን፡፡ ከተግባባን ላይቀር ብለን ስለ ሀገሪቱ ሁኔታ ማውራት ቀጠልን፡፡

በተለይም ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፣ ስለ ሀገሪቱ ታሪክ፣ በታሪክ ውስጥ የተከሠቱ ነገሮችን እንዴት ማረም እንደምንችል፣ የሕዝቦች መቀራረብ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል እናወራ ነበር፡፡ ከሚነግረኝ ነገሮች ሰውዬው የፍልስፍናና የታሪክ ዕውቀቱ ሰፋና ጠለቅ ያለ መሆኑን ተረዳሁት፡፡ በተለይ ደግሞ የዶክተር ዳኛቸው አሰፋ አድናቂም ደቀ መዝሙርም መሆኑን ስረዳ ነገሮችን ሊያይበት የሚችለውን መነጽር ገመትኩት፡፡

ለሽመልስ የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ የጠቅላላው ታሪካችን አካል ነው፡፡ የተሻለው የመግባቢያ መንገድ የጎደለውን መሙላትና ያለውን የጋራ አድርጎ ይዞ መቀጠል ነው፡፡ ችግሮቹን እኛው ፈጠርናቸው፤ መፍትሔውንም እኛው ማምጣት እንችላለን፡፡ አንዱ የሌላውን ታሪክና ባሕል ሊፈልገው የሚገባው ያለእርሱ ሙሉ ስለማይሆን ነው፡፡ የጎደለብንን ፍለጋ ወደ ሌሎች ወገኖቻችን መሄድ አለብን፡፡ እዚያ ስንሄድ ሌላ ነገር ሳይሆን የምናገኘው ጎድሎ የቀረብንን የራሳችንን ነው የምናገኘው፡፡ የኢትዮጵያ ተቃራኒ ትርክቶችን የማቃኛው መንገድ ማሟላት ነው፡፡ መግፋትና ማጥፋት አይደለም – ይላል ሽመልስ፡፡ የቤተ መንግሥቱን የሙዝየም ሥራ ለልዩ ልዩ አካላት በሚያስጎበኝበት ጊዜ – ያለፉትን ታሪኮቻችንን በጋራ መቀበል፣ ችግሮቹንም በጋራ ማረም፣ የዛሬውንም በጋራ መጻፍ እንደሚገባን በአጽንዖት ያነሣ ነበር፡፡

ከዚህ ሰው ጋር ላለፉት ስድስት ወራት አብሬው ሠርቻለሁ፡፡ እጅግ የተወሳሰቡ ነገሮችን ማቅለል፤ መክሊት ካለው ሰው ጋር ሁሉ መሥራት፣ ሰውን በሰውነቱ ብቻ ማየት፣ ሊሞግቱትና ሊከራከሩት የሚችሉትን ሁሉ በጨዋነት መስማትና መቀበል፣ ነገሮችን በቀናነት መውሰድ፣ እጅግ መንግሥትን ከሚቃወሙ አጥብቀው እስከሚደግፉ፤ ከወጣቶች እስከ አንጋፋዎች ለመነጋገርና አብሮ ለመሥራት መዘጋጀት ስጦታዎቹ ናቸው፤ – ይህ ሁሉ ሲሆን ደግሞ ከቀልድና ጨዋታ ዐዋቂነት ጋር፡፡

ሽመልስ አብዲሳ፡፡ (ስንቀልድ የአብዲሳ አጋ ልጅ እንለዋለን)፡፡ ዛሬ የኦሮምያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነ፡፡ ሽመልስ ኢትዮጵያን በተረዳበት መንገድ ክልሉን ከመራው ለኢትዮጵያ መጻዒ ዕድሏ ብሩኅ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያን የሚወዱ ሁሉ በሞያቸውና በዕውቀታቸው ቢያግዙት የምንፈልጋትን ሀገር ለማግኘት አንዱ መንገድ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

Zerihun Gemechu


Ethiopia | Shimeles Abdisa | ዲያቆን ዳንኤል እና ዶ/ር ዳኛቸው ስለ ሽመልስ አብዲሳ | Daniel kibret and Dr Dagnachew

Kumaa Dammaqsaa amma immoo ‘Kumaa Deebisaa Abdiisaa’ ta’ee dhufe. Dhugaan jedha, kanaanis hin milkooftan!!


በቅርብ ጊዜ በዶ/ር አብይ አህመድ ከተዋቀረው ካቢኔ ጋር ከተወያዩ በኋላ