የኮሌራው ምሥጢር! የቴድሮስ “የጥቅምት ዱብ ዕዳ”? Goolgule

የኮሌራው ምሥጢር! የቴድሮስ “የጥቅምት ዱብ ዕዳ”? Goolgule

(GoolGule) – በህወሃት/ኢህአዴግ ከፍተኛ የገንዘብ ድጎማና ድጋፍ ለዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ዳይሬክተርነት የሚወዳደረው ቴድሮስ አድሃኖም የመመረጡ ጉዳይ አደጋ ገጥሞታል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበረበት ወቅት ሦስት የኮሌራ ወረርሽኞች በምሥጢር እንዲያዙ ማድረጉ ለዳይሬክተርነት እንዳይበቃ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ እንደ አሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይህ ጉዳይ የቴድሮስ “የጥቅምት ዱብ ዕዳ” ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡

ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ሜይ 13፤2017 ዓም “የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅትን ለመምራት የሚወዳደረው እጩ ወረርሽኝ በመደበቅ ተከሰሰ” በሚል ርዕስ ባስነበበው ዜና የቴድሮስን የመመረጥ ተስፋ ስለሚያጨልመው የኮሌራ ወረርሽኝ ምሥጢር በዝርዝር አትቷል፡፡

በያዝነው የግንቦት ወር (ከሜይ 22፣ 2017) ጀምሮ በጄኔቫ በሚካሄደው የአንድ ሳምንት ስብሰባ ድርጅቱን ለመምራት ከሚወዳደሩት ሦስት እጩዎች (ቴድሮስን ጨምሮ እንግሊዛዊው ዶ/ር ዴቪድ ናባሮና ፓኪስታናዊቷ ዶ/ር ሳኒያ ኒሽታር) መካከል አንዱ የዳይሬክተርነቱን ቦታ ይወስዳል፡፡ ስብሰባው ሊጀመር አንድ ሳምንት አካባቢ ሲቀረው በቴድሮስ ላይ የቀረበው ይህ ክስ ራሱንም ያስደነገጠው ይመስላል፤ “አልገረመኝም ግን ቅሬታን አሳድሮብኛል፤ ይህ ባለቀ ሰዓት የሚካሄድ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው” ብሎታል፡፡

ምሥጢሩን ይፋ ያደረጉት የቴድሮስ ተፎካካሪ የሆኑት የዶ/ር ናባሮ ኢ-መደበኛ አማካሪና በጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ የኦኒል የብሔራዊና ዓለምአቀፍ የጤና ሕግ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ሎውረንስ ጎስቲን ናቸው፡፡ ጎስቲን እንደሚሉት ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበረበት ዓመታት (2005 – 2012) እኤአ በ2006፣ 2009 እና 2011 በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ይፋ እንዳይሆን በምሥጢር እንዲያዝ አድርጓል፤ ይህም ዓለምአቀፉን የጤና ጥበቃ ድርጅት እንዳይመራ ከበቂ በላይ ምክንያት መሆን ይችላል የሚል መከራከሪያ ነው፡፡

ዶ/ር ናባሮ ስለጉዳዩ ሲጠየቁ “እኔ በጭራሽ ይህንን አላውቅም፤ ዶ/ር ቴድሮስ ብቃት ያለው የጤና ባለሙያ ነው፤ ጎስቲን ይህንን የተናገረው እኔን ሳያማክር ነው፤ ሆኖም ግን ቴድሮስ እውነቱን መናገር፤ ለረጅም ጊዜ የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ሪፖርት ማድረግ፤ እውነትን መናገር ይገባዋል” በማለት ከቻይና በስልክ ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግረዋል፡፡ ጎስቲን ከኢመደበኛ አማካሪነት በተጨማሪ ከናባሮ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው መሆኑ ቢታወቅም ጎስቲን ይህንን ያጋለጡት ለዓለምአቀፉ ድርጅት ከመቆርቆር የተነሳ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ቴድሮስ አድሃኖም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበረባቸው ዓመታት ጎስቲን በሚመሩት ተቋም ጥሪ እየተደረገለት በጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ “የተከበሩ” ተብሎ ንግግሮችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ ዓይነቱን የምዕራባውያን “ወዳጅነት” ነበር ቴድሮስ እንደ ብቃት መለኪያ አድርጎ ሲያቀርብ የነበረው፡፡

የዛሬ አሥር ዓመት አካባቢ በኢትዮጵያ የኮሌራ በሽታ ተነስቶ እኤአ በ2007ዓም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 700 ያህል ሕዝብ ሲልቅና ከ60ሺህ በላይ በበሽታው ሲጠቃ የህወሃት ሹሞች “ውሃ ተቅማጥ” ነው ከማለት ባላለፈ የሽታውን መከሰት ሲክዱ ነበር፡፡ ዜናው በዓለምአቀፍ ሚዲያ ላይ ቢዘገብም “የድርብ አኻዝ” ዕድገት ስሌቱን የሚያዛባና ቱሪዝምን የሚደናቅፍ ሆኖ በመገኘቱ የሰዎች መሞት ለህወሃት ብዙም አላስጨነቀውም፡፡ ቴድሮስም በወቅቱ ከአውሮጳና አሜሪካ የሚሰጠውን ትዕዛዝ በመፈጸም ተግባር ተይዞ “ዛሬን” አላሰበም ነበር፡፡ ይኸው በሽታ አሁን ደግሞ “አተት” (አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት) የሚል የቁልምጫ ስም ተሰጥቶታል፡፡

የኮሌራ ወረርሽኝ በተደጋጋሚ በሚከሰትበት ወቅት ከህወሃት/ኢህአዴግ የበላይ ሹሞች ሚዲያውም ሆነ የጤና ሠራተኞች “ኮሌራ” የሚለውን ቃል እንዳይጠቀሙ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ሆኖም በድብቅ እንዲወጣ በተደረገ የሰገራ ናሙና ምርመራ በርግጥ የኮሌራ ወረርሽን ለመከሰቱ ዓለምአቀፍ የጤና ባለሙያዎች ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ዘገባው በዝርዝር እንደሚያስረዳው ከዚህ በፊት የበሽታው ወረርሽን ታይቶባቸው በማይታወቀው በጉጂ፣ በባሌ እና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች እኤአ ከሴፕቴምበር 15 እስከ ኦክቶበር 9፣ 2006ዓም (መስከረም5 እስከ 29፤1999ዓም) ቦታዎቹን የቃኙና ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች ኮሌራ በአካባቢዎቹና አጎራባች ክልሎችና ዞኖች መከሰቱን አረጋግጠዋል፡፡ (ኒው ዮርክ ታይምስ የጠቀሰውን የባለሙያዎቹን ዘገባ እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል)፡፡

በኢትዮጵያ ማንኛውንም ተቃውሞ በማፈን ለህዝብን ስቃይ “ጥሪ አይቀበልም” ሲል የኖረው ህወሃት/ኢህአዴግ አሁን በራሱ ገመድ ለመታነቅ ጊዜው የደረሰበት ይመስላል፡፡ በርካታ ገንዘብ በማፍሰስ ለምርጫ ውድድር ያቀረበው ዕጩ ተወዳዳሪ በዚህ ሁኔታ መከሰሱ ባለቀ ሰዓት ተስፋ አስቆራጭ ሆኖበታል፤ ቴድሮስም ይህንኑ ያመነ ይመስላል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት በዕጩነት ሲቀርብ የተጠየቀውን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ አቅቶት ሲጨነቅ የነበረው ቴድሮስ አድሃኖም፤ ይህንን በመጨረሻ ሰዓት ላይ የተከፈተበትን የተቀነባበረ ዘመቻ ለመቋቋም አይችልም የሚል አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡ የኮ/ሎ ጎሹ ወልዴን አስደናቂ ብቃት ባስናፈቀ መልኩ ቴድሮስ ያቀረበው የምረጡኝ ቃለ ምልልስ ጎልጉል በዘገበበት ወቅት የሕዝብንም ኃፍረት አብሮ ዘግቦ ነበር፡፡

በአሜሪካ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲካሄድ በህዳር ወር መጀመሪያ ምርጫው ከመደረጉ በፊት በጥቅምት ወር አንዱ ዕጩ ስለ ሌላኛው ጊዜ ጠብቆ የሚያወጣው ምሥጢር አለ፡፡ ይህ በተለምዶ “የጥቅምት ዱብ ዕዳ” (the October Surprise) በሚባለው የመመረጥ ዕድላቸው በቀላሉ እንዲሳካ የተደረገላቸው የመኖሩን ያህል በአስከፊ ሁኔታ ሽንፈትን እንዲከናነቡ የተደረጉም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ የተደበቀው የኮሌራ ምሥጢር የቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ “የጥቅምት ዱብ ዕዳ” ይሆን?

1 Comment

  1. No matter how long the night is the day shall follow! The 26 years darkness Tewodros and his hynea group hiding in shall doon be expossed to light, although they polish themselves as genuine individuals behind their guns!!They may dream to escape! Really?????????

Comments are closed.