የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አዲሱ የቋንቋ ፖሊሲ በአፋጣኝ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲጸድቅ ጠየቀ።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አዲሱ የቋንቋ ፖሊሲ በአፋጣኝ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲጸድቅ ጠየቀ።

ሶማሊኛ፤ ኦሮሚኛ፤ ትግርኛና አፋርኛ ቋንቋዎችን ከአማርኛ በተጨማሪ ለፌድራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ያጨው የቋንቋ የፖሊሲ ረቂቅ ትናንት በምኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል። ጉዳዩ «ለበርካታ ጊዜያት ተነስቶ የጠፋ፤ የፖለቲካ መሳሪያ ሆኖ ሲንከባለል ዛሬ የደረሰ» ነው ያለው ኦነግ «አሁንም ይኸ ውሳኔ በሥራ ስለሚተረጎምበት ሁኔታ የሚታወቅ ነገር የለም» ሲል ጥርጣሬውን ገልጿል።
ስድስት አመታት ፈጅቷል የተባለውን የፖሊሲ ጥናት ያከናወኑ ባለሙያዎች እንዳሉት የፖሊሲ ረቂቁን ለመተግበር የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ፤ ከ10 እስከ 15 አመታት የሚወስድ ጊዜ እና ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ዛሬ ባወጣው መግለጫ «በሕግ እና በታሪክ የኦሮሞ ሕዝብ ሐብት እና የኦሮሚያ አካል» ናቸው ያላቸው የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች እጣ-ፈንታ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲወሰን ጭምር ጠይቋል።

DW Amharic