የኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን የአቶ ለማ መገርሳን ንግግር አላስተላልፍም ማለቱ እያወዛገበ ነው

አቶ ለማ መገርሳ በአደባባይ ከታዩ ሰንበት ብለዋል

(bbcamharic)—በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚተዳደረው ‘ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ’ የመከላከያ ሚንስትሩን አቶ ለማ መገርሳ ድምጽ አላስተላልፍም ማለቱ በድርጅቱ ጋዜጠኞች ዘንድ ቅሬታን ፈጠረ።

ለበርካታ ሳምንታት በመገናኛ ብዙሃን ሳይታዩ ቆይተው የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ፤ ትናንት በአቶ ካቢር ሁሴን ቀብር ላይ ተገኝተው አጭር ንግግር አድርገው ነበር። ይህም የበርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነጋጋሪያ ሆኖ ቆይቷል።

ቀብሩን ለመዘገብ ከተገኙት መገናኛ ብዙሃን መካከል አንዱ የነበረው ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) የአቶ ለማ መገርሳን ድምጽ ከማስተላለፍ መቆጠቡ በድርጅቱ ጋዜጠኞች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል።

የአቶ ለማ ድምጽ አየር ላይ እንዳይውል እንዴት ተከለከለ?

የአቶ ለማ ንግግርን የያዘው የቀብር ስነ-ስርዓቱ ዘገባ በትናንት ዕለት በቀኑ 6 እና 7 ሰዓት ላይ እንደሚሰራጭ በመርሃ ግብሩ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ዜናው ወደ ምሽት እንዲተላለፍ መወሰኑን ቢቢሲ ከድርጅቱ ሰራተኞች ማረጋገጥ ችሏል።

በምሽት 12 እና 1 ሰዓት ዜናዎች ላይ ከዘገባው የአቶ ለማ መገርሳ ድምጽ እንዲወጣ ተደርጎ፤ የክልሉ ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ድምጽ በማካተት እንዲተላለፍ ተደርጓል።

የድርጅቱ ዳይሬክተር ‘የአቶ ለማ ድምጽ ከላይ በመጣ ትዕዛዝ እንዳይተላለፍ ተከልክሏል’ በሚል ምክንያት ድምጻቸው ከዘገባው ተቆርጦ እንዲወጣ መደረጉን ሰምተናል።

ይህ የዳይሬክተሩ ውሳኔ ከድርጅቱ ጋዜጠኞች ጋር አለመግባባትን ፈጥሮ እንደነበርም የኦቢኤን ጋዜጠኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከድርጅቱ ነባር ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ለቢቢሲ፤ ከዚህ ቀደምም የተመረጡ ሰዎች ድምጽ እና ምስል አየር ላይ እንዳይውል ክልከላ ይደረጋል ብሏል።

የአቶ ለማ መገርሳ ድምጽ አይተላለፍም መባሉን ከተቃወሙ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ደግሞ፤ “ይህ ሚዲያ የመንግሥት አፍ ብቻ ነበር። ድርጅቱ በህዝቡ ዘንድ ድጋፍ እና ተደማጭነት እንዲያገኝ ብዙ ከሰሩት መካከል ዋናው አቶ ለማ መገርሳ ናቸው” ያለ ሲሆን፤ “እርሳቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዛሬ ላይ ተዘንግቶ፤ ድምጻቸው ህዝብ ጋር እንዳይደርስ ማድረግ እጅግ ያበሳጫል” ሲል ተናግሯል።

ሌላው ማንነቱን የማንጠቅሰው ጋዜጠኛም “እኚህ ሰው በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። የፖለቲካ ይዘት በሌለው ዘገባ ላይ ድምጻቸው አይተላለፍ ማለቱ ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።

የአቶ ለማ ድምጽ ‘ከላይ በመጣ ትዕዛዝ አይተላለፍም’ ከመባሉ ውጪ ሌላ ድምጻቸው አየር ላይ የማይውልበት ምክንያት እንዳልተሰጠ ጋዜጠኞቹ ተናግርዋል።

በጉዳዩ ላይ የድርጅቱ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዝናቡ አስራት እና ምክትላቸው አቶ ቦጃ ገቢሳ ጋር በተደጋጋሚ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም።

አቶ ለማ በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ ያሉት ምን ነበር?

አቶ ለማ በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ ሲያመሩ ለቀብር የተገኘው ህዝብ ከፍ ባለ ጭብጨባ ነበር የተቀበላቸው። አቶ ለማ ስለ ሟቹ የንግድ ሰው በማስመልከት ያደረጉትን መልካም ንግግር በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲጋሩት ነበር።

አቶ ለማ “ከቢር ሁሴን ትልቅ ትንሹ የሚያውቋቸው ሰው ነበር። ከቢር ሁሴን አባት እና ጓደኛችን ነው። በንግድ ብቻ ሳይሆን ለወገኑ የሚጨነቅ ለኦሮሞ ብሎ ንብረቱን ያጣ ሰው ነው። ገንዘብ ቢኖረውም አንድም ቀን ለራሱ ጊዜ ያልነበረው ሰው ነበር። ኦሮሞ ዛሬ ትልቅ ሰው ነው ያጣው” የሚል ይዘት ያለው ንግግር ነበር ያደረጉት።

አቶ ከቢር ሁሴን ማናቸው?

በአርሲ የተወለዱት አቶ ከቢር ሁሴን ታዋቂ የንግድ ሰው ነበሩ። በዘመናዊ ግብርና ሥራ ትልቅ ስም ያተረፉት አቶ ከቢር፤ የአዳማ ጀነራል ሆስፒታል ባለቤትም ናቸው።

አቶ ካቢር የኦሮሞን ህዝብ መሠረት በማድረግ የተመሰረቱ ባንኮች ስኬታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማደረጋቸው ይነገራል።

ከዚህም በተጨማሪ በኦሮሞ ህዝብ የፖለቲካ ትግል ወቅት የሚጎዱ ሰዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን እንደሚረዱ የሚያውቋቸው መስክረዋል።