የኦሮሚያ ክልል መንግስት ብስለት ከጎደለው መግለጫው እንዲታቀብ ኦነግ አሳሰበ።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ብስለት ከጎደለው መግለጫው እንዲታቀብ ኦነግ አሳሰበ።

ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ/ም
ባለፈው ሳምንት የኦሮሚያ ክልል መንግስት ”ሕዝቡ ከአገር ጥቅም በተቃራኒ ከቆሙት አካላት ሊጠነቀቅ ይገባል” ሲል በሰጠው መግለጫ በግብፅ የሚደገፍ ቡድንና ወያኔ ከሀገር ጥቅም በተቃራኒ የቆሙ ናቸው ማለቱ ይታወሳል፡፡

በክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ሶስተኛውከሀገር ጥቅም በተቃራኒ የቆሙት ቡድኖች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው ያሉ ሲሆን ምርጫ መራዘሙን መነሻ ምክንያት በማድረግ በአቋራጭ ስልጣን የሚፈልጉ አካላት ናቸው” ብለው ነበር።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ፓርቲያችን በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት ነው።

በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችም ጋር በጋራ መግባባት ይሰራል፤ መንግስት የገለፀው የፖለቲካ ድርጅት አይነት አይደለንም፣ እስከምናውቀውም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንዲህ አይነት ድርጅት የለም ብለዋል፡፡

ለሚዲያ ፍጆታ ሊያውለው ፈልጎት ከሆነ ከመንግስት የማይጠበቅ ነው ያሉ ሲሆን በትክክል የትኛውን የፖለቲካ ድርጅት ከሀገር ጥቅም ተቃራኒ የቆመ እንደሆነ አለመናገር ውዥንብር መንዛት ይባላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የብሔር ፣የኢኮኖሚ፣የባህል ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት ታግሏል፤ እነዚህ ጥያቄዎቹ አሁንም አልተመለሱለትም፤ ከለውጡ በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር በተመሳሳይ እስራትን ግድያን፣መፈናቀልን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰቱም ቀጥሏል፣ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አልተቻለም ፣ ህገ ወጥነት ሰፍኗል ፣ ህግና ስርአትን ማስጠበቅ አልተቻለም ፣ ህዝቡ ከፍተኛ ቅሬታ ላይ ነው ብለዋል አቶ ቀጀላ፡፡

ይሄን የሚያወሳስቡት በመንግስት መዋቅር ላይ ያሉት ናቸው፣ ይሄን መለወጥ ካልተቻለ፣ ራስ ምታት ነው በብዙ ዕጥፍ ጨምሮ በቀጣይ የሚጠብቀን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ቀጀላ ከግጭትና ከቁልቁለት መንገድ የሚታደገን ሁላችንም ፓርቲዎች ያስቀመጥነውን ሀሳብ በጠረጴዛ ላይ በማስቀመጥ ተወያይቶ የተግባባንበትን አማካይ ውሳኔ ማስቀጠል ነው ብለዋል፡፡

እናንተ የራሳችሁ ጉዳይ የኔ መንገድ ብቻ ነው የሚተገበረው ብሎ የማይተረጎም ህገ መንግስት ለመተርጎም ማገላበጥ ከቀድሞዎቹ ስርአቶች አለመማር ነውም ብለዋል፡፡

ፓርላማው ስልጣኑ መቀጠል የለበትም፣ በአምስት አመት ስልጣኑ ያልቃል የሚለውን ህገ መንግስት ስድስት አመት በማድረግ ተረጎምነው ሊሉ ነው ወይ ሲሉ የሚያነሱት አቶ ቀጀላ መንግስት ብስለት ከጎደላቸው መግለጫዎቹና ተግባራቱ እንዲታረም አሳስበዋል፡፡