የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት:መከባበር፣ በእኩልነት አብሮ መኖር፣

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት:መከባበር፣ በእኩልነት አብሮ መኖር፣

“የህዝቦች አብሮነትና እኩልነት በመፈክር ብቻ ሊመጣ አይችልም፡፡ መከባበር፣ በእኩልነት አብሮ መኖር፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን ግድ ይላል፡፡አንዱ ጠግቦ እየበላ፣ ሌላዉ እየተራበ፣ አንዱ አግኝቶ ሌላዉ እንዲያጣ፣ አንዱ በልጽጎ ሌላዉ ደህይቶ የምንኖርባት ሀገር እንዲኖር አንፈልግም፡፡ የምንታገለዉም ለእኩልነት፣ ለአንድነት እና ለህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ነዉ፡፡

የአማራ ሕዝብ የኛ ሕዝብ ነዉ፡፡ የትግራይ ህዝብ የኛ ህዝብ ነዉ፡፡ የሲዳማ ፣ የሶማሌ፣ የአኙዋክ፣ የጉራጌ፣ የአፋር፣ የቤንሻንጉል … ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ሁሉ የኛ ህዝቦች ናቸዉ፡፡ አንድ ነን፡፡ ምንም ልዩነት የለንም! እኛ የምንፈልገዉ ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰላም፣ እኩልነትና አንድነት እንዲኖር፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ነዉ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያን የሚያሳድገዉ ይሄ ነዉ፡፡ ሀገራችንን የሚለዉጠዉ ይሄ ነዉ! የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምኞት፣ ትግልና ልፋት ለዚህ ብቻ ነዉ፡፡…” Obbo Lammaa Magarsaa

 የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት

Oromia communication office

የኢትዮጵያ አንድነት እና የህዝቦች አብሮነት
======
መስከረም 15/2010 ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ከኦሮሚያ ክልል ሁሉም ዞኖች የተዉጣጡ አባ ገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት የሰላም ኮንፈረንስ በፊንፊኔ የኦሮሞ ባህል ማዕከል ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ አንድነት እና የህዝቦች አብሮነትን በተመለከተ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕረዝዳንት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ለኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ያደረጉትን ንግግር ወደ አማርኛ ተርጉሜ አቅርቤላችኋለዉ፡፡ መልካም ንባብ!

…በአሁኑ ወቅት በኦሮሞ ህዝብ ዉስጥ እየተፈጠረ ያለዉ የአንድነት እና የመተባባር መንፈስ የሀገራችን ኢትዮጵያን አንድነት ያጠናክራል፡፡ ከጥልቅ ተሃድሶዉ መጀመር ወዲህ የክልሉ መንግስት ወደ ህዝብ መመለስ፣ የህዝቡን ችግር አድምጦ መፍትሄ መስጠት፣ ህዝቡ የሚፈልገዉን መስራት መጀመሩ ጠቀሜታዉ ለኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን ለሀገራችንም ጭምር እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ እዉነት ለመናገር በአሁኑ ወቅት ህዝባችን የሚፈልገዉን ከመስራት ዉጪ ምንም ሌላ አማራጭ የለንም፡፡

የኦሮሞ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ለሁላችንም ግልጽ መልዕክት እያስተላፈልን ነዉ፡፡ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር አመራር ላይ ያለን ሰዎች የህዝቡን ቃል እና ፍላጎት ቸል ብለን ለመሄድ የምንሞክር ከሆነ አንድም ቀን ማደር እንደማንችል ህዝባችን በግልጽ እየነገረን ነዉ፡፡የህዝባችንን ጥያቄ መመለስ ፣የህዝቡን ፍላጎት ከማርካት ዉጪ ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝ ማየት አይቻልም፡፡ መንገዱን ካጋመስን በኋላም ወደ ኋላ ማየት የለም፡፡ ስለዚህ የኛ ልፋት የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት ነዉ፡፡

ይህን ሁሉ የምንሰራዉ ለምንድን ነዉ? ለሀገራችን ኢትዮጵያ ዕድገት ነዉ፡፡ ለኦሮሞ ህዝብ ዕድገት ብቻ አይደለም፡፡ እኛ አጥብበን በመንደር ታጥረን የምናስብ ሰዎች አይደለንም፡፡ ለመላዉ የሀገራችን ህዝቦች ብልጽግናና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የምናስብ ሰዎች ነን፡፡የሀገራችንን ዕድገት ለማፋጠን የኛ ሚና ወሳኝ እንደሆነ በአግባቡ እንገነዘባለን፡፡

ከጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ ወዲህ ከመሬት፣ ማዕድን፣ ኮንትሮባንድ እና ከመሳሰሉት ጉዳዮች ጋር ተያይዘዉ በሚስተዋሉ የኪራይ ሰብሳነት ተግባራት ላይ እርምጃ መዉሰድ ጀምረናል፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነት ተሰማርተዉ ያለ አግባብ ሲዘርፉ የነበሩ ግለሰቦች በክልሉ መንግስት የስራ ሃላፊዎች እና በክልሉ ህዝብ ላይ የተቀነባበረ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፍተዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉት የክልሉ መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስቆም ትናንሽ እርምጃዎችን መዉሰድ ስለጀመረ ነዉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስቆም ገና ወደ ወሳኙ ምዕራፍ አልገባንም፡፡ ከመሬት፣ ማዕድን፣ ኮንትሮባንድ እና በመሳሰሉት ጉዳዮች እርምጃ መዉሰድ በመጀመራችን የክልሉን አመራር እንደ ጠባብ ብሄርተኛ ፣ የሀገራችንን ብሄር ብሄረሰቦች እንደ ጠላት የሚያይ፣ በአጎራባች ክልል የሚኖሩ ወንድሞቻንን ለማጥፋት የተነሳን ጠብ አጫሪ አስመስለዉ እኛን ለማቅረብ ላይ ታች እያሉ ይገኛሉ፡፡ የኦሮሞ ህዝብም በሀገራችን ህዝቦች ዘንድ በጥርጣሬ አይን እንዲታይና እንዲጠላ፣ ለዚህች ሀገር አንድነት የማይጨነቅ አስመስለዉ ፕሮፓጋንዳ እየነዙ ነዉ፡፡

እኛ እንደዚህ አይነት ህልም ፈጽሞ የለንም፡፡ እየለፋን ያለነዉ፣ እየሰራን ያለነዉ ስራ ሁሉ ለሀገራችን ኢትዮጵያ አንድነት እና ብልጽግና ነዉ፡፡ሕዝቦችን ለመለያየት፣ የህዝቦች አብሮነትን ለማሰናከል ፈጽሞ አስበን አናዉቅም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር በአብሮነት መኖር ዛሬ የሚጀምር ህዝብ አይደለም፡፡ለአያሌ አመታት በአብሮነት መኖር ምን እንደሆነ ለዓለም ያሳየ ህዝብ ነዉ፡፡አብሮነት ዛሬ የምንጀምረዉ ተሞክሮ የማያዉቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ከማንም ጋር መኖር የሚዉቅ ህዝብ ነዉ፡፡ ወንድም ህዝቦችን የራሳችን አድርገን፣ ያለንን ተካፍለን፣ ተጎራርሰን መኖር የምናዉቅ፤ የሀገር አንድነትን በጽኑ የምንፈልግ መሆናችንን በተግባር ያሳየን ህዝብ ነን፡፡ የአብሮነትን ጉዳይ ዛሬ ማንም ተነስቶ እንደ አዲስ ነገር የሚነግረን አይደለም፡፡

በዚህች ሀገር ለዘመናት የቆየዉን የህዝቦች አብሮነትና አንድነት እንዲናጋ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ የክልሉ መንግስት በፍጹም አይፈልጉትም፡፡ እኛ የምንለፋዉ ለኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች አንድነት ነዉ፡፡ አንድነት ብቻ ሳይሆን እኩልነት እንዲሰፍን፣ ለስም አብሮ መኖር ሳይሆን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ነዉ፡፡

የህዝቦች አብሮነትና እኩልነት በመፈክር ብቻ ሊመጣ አይችልም፡፡ መከባበር፣ በእኩልነት አብሮ መኖር፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን ግድ ይላል፡፡አንዱ ጠግቦ እየበላ፣ ሌላዉ እየተራበ፣ አንዱ አግኝቶ ሌላዉ እንዲያጣ፣ አንዱ በልጽጎ ሌላዉ ደህይቶ የምንኖርባት ሀገር እንዲኖር አንፈልግም፡፡ የምንታገለዉም ለእኩልነት፣ ለአንድነት እና ለህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ነዉ፡፡

የአማራ ሕዝብ የኛ ሕዝብ ነዉ፡፡ የትግራይ ህዝብ የኛ ህዝብ ነዉ፡፡ የሲዳማ ፣ የሶማሌ፣ የአኙዋክ፣ የጉራጌ፣ የአፋር፣ የቤንሻንጉል … ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ሁሉ የኛ ህዝቦች ናቸዉ፡፡ አንድ ነን፡፡ ምንም ልዩነት የለንም! እኛ የምንፈልገዉ ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰላም፣ እኩልነትና አንድነት እንዲኖር፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ነዉ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያን የሚያሳድገዉ ይሄ ነዉ፡፡ ሀገራችንን የሚለዉጠዉ ይሄ ነዉ! የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምኞት፣ ትግልና ልፋት ለዚህ ብቻ ነዉ፡፡.

Via: Oromummaa Wtuoga