የእሬቻ በዓል: በኦሮሞ ባህል ውስጥ ከሚገኙ የእምነት ሥርዓቶች አንዱ በሆነው እሬቻ ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶች ተሠርተዋል፡፡

የእሬቻ በዓል
18 September 2019
በጋዜጣዉ ሪፓርተር
እያንዳንዱ ኀብረተሰብ ፈጣሪ አምላኩን የሚለምንበትና የሚያመሠግንበት የራሱ የሆነ የእምነት ሥርዓት አለው። ከእነዚህ ሥርዓቶች አንዱ የእሬቻ በዓል ሲሆን፣ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድም በየዓመቱ መስከረም በደማቅ ሁኔታ ይከበራል፡፡ የዘንድሮው የእሬቻ በዓል ደግሞ በአዲስ አበባም ጭምር መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በተለያዩ ዝግጀቶች እንደሚከበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡

በኦሮሞ ባህል ውስጥ ከሚገኙ የእምነት ሥርዓቶች አንዱ በሆነው እሬቻ ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶች ተሠርተዋል፡፡ ክብረ በዓሉ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚደረግ ሲሆን፣ ከእነዚህ በቱለማ ኦሮሞ የሚከበረው ይገኝበታል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሒዩማኒቲስ፣ የቋንቋ ጥናት፣ የጆርናሊዝምና ኮሙዩኒኬሽን ኮሌጅ፣ የአማርኛ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል ድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር በቱለማ ኦሮሞ ስለ ባህላዊ የፍቅር ግንኙነቶችና ኤችአይቪ/ኤድስ የሚነገሩና የሚከወኑ የሥነ ቃል ዓይነቶችና ትንተና ላይ በበጅጋ ተካ ቡኔ በ2008 ዓ.ም. የተሠራ ጥናት እንደሚያስረዳው፣ እሬቻ ማለት ምሥጋና ለአምላክ ለማቅረብ የሚከናወን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው። የሚከናወነው የምልጃና የምሥጋና ተግባር በቦታና በጊዜ የተወሰነ ነው። የእሬቻ በዓል በተለያዩ ቦታዎች ሊከናወን የሚችል ቢሆንም፣ ታላላቅ የሚባሉት ግን በሁለት ቦታዎች የሚከናወኑት ናቸው። እነዚህም የተራራ ላይ እሬቻ እና የመልካ (ወንዝ) ላይ የሚደረግ እሬቻ ናቸው። ይህን እምነት የሚከተሉ፣ በአንድ በተመረጠ ቦታና በተወሰነ ወቅት በአንድ ላይ ተሰብስበው ፈጣሪያቸውን ከሚለምኑበትና ምሥጋናቸውን ከሚያቀርቡበት ሥርዓት አንዱ የእሬቻ ክብረ በዓል ነው።

እሬቻ ማለት እርጥብ ሳርና አበባ በመያዝ ለእሬቻ በተመረጠ ቦታ ላይ በማስቀመጥ ለፈጣሪ ምሥጋና ማቅረብ እና ፈጣሪን መለመን ሲሆን፣ የእምነቱ ሥርዓት እግዚአብሔርን ማምለክ (Waaqeffannaa) እንደሚባል በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

በእምነቱ መሠረት እሬቻ የሚካሄድባቸው ቦታዎች ከመልካ (ወንዞች ወይም ሐይቆች) ውስጥ በተመረጠው መልካ እንዲሁም ከተራሮችም ውስጥ በተመረጠው ተራራ ነው፡፡ በተገኘው ወንዝና ተራራ የእሬቻ ሥርዓቶች አይከናወኑም፡፡

በወንዞች (ሐይቆች) በዓሉ የሚከበረው ክረምት ከወጣ በኋላ በመስከረም ወር ሲሆን፣ በተራራ የሚከበረው ደግሞ በመጋቢት ወር ነው። በዚሁ መሠረት የቱለማ ኦሮሞ በተመሳሳይ ወቅት በየአካባቢው እሬቻ የሚያደርግበት የየራሱ ቦታዎች ያሉት ቢሆንም፣ ሁሉም በጋራ የሚያከብሩት ነው፡፡

ከሐይቅ የቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲን፣ ከተራራ ጋራ ጩቃላን (ዝቋላን) ናቸው። ማኅበረሰቡ እነዚህን ቦታዎች የመረጠበት የራሱ ታሪካዊ ምክንያት አለው። የእሬቻ መከበሪያ ጊዜያት የመልካው ክረምት ወራት አልፈው መስከረም ወር ውስጥ፣ የተራራው ደረቅ ወራት አልፈው በመጋቢት ወር ውስጥ ነው፡፡ በመልካ የእሬቻ ሥነ ሥርዓት ላይ በርካታ የሥነ ቃል ዓይነቶች ይነገራሉ፡፡ ሽማግሌዎች በምረቃ፣ ወጣቶች በዘፈንና በጭፈራ ክብረ በዓሉን ሲያደምቁ ይታያሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሚከበረውን የእሬቻ በዓል አስመልክቶ ከአባገዳዎች፣ ከቄሮዎችና ከፎሌ ከተውጣጡት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡


Irreecha Birraa nagaan baane; Irreecha Arfaasaas nagaan akka jala baanu, Waaqni jabaan nu eeginna!

Via: Dábessá Gemelal