ስለኤርትራና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አምባሳደር-አቶ አውዓሎም፡

ስለኤርትራና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አምባሳደር- አቶ አውዓሎም፡

(bbc)—-ኤርትራን ነፃነቷን ማግኘቷን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ዕውቅናን ለመስጠት የመጀመሪያው ሆነ። አቶ አውዓሎም ወልዱም በ1986 ዓ.ም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አሥመራ ላይ ተሾሙ። የመጨረሻ አምባሳደር ይሆናሉ ብሎ ግን የጠበቀ አልነበረም።

ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ ግን የሁለቱ ሃገራት ጦርነቱ በመቀስቀሱ የመጨረሻው አምባሳደር ሆነዋል። “ሁለቱ ሃገራት በነበራቸው ግንኙነት እንደ ሁለት ሃገራት ሳይሆን እንደ አንድ ሃገር ነበሩ” የሚሉት አቶ አውዓሎም የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ ፖለቲካና ሌሎች ጉዳዮች ጣልቃ ይገባ ነበር ይላሉ።

• ሬድዋን ሁሴን በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ

• ወደ አሥመራ ለመጓዝ ማወቅ የሚገባዎ 6 ነጥቦች

ቢቢሲ አማርኛ፡ ከጦርነቱ በፊት የነበረው የሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዴት ይታያል?

አቶ አውዓሎም፡ ኤርትራ እንደ ሃገር ሆና ብትቆምም የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው እንደ ሁለት ሃገራት አልነበረም። በተለይ የኤርትራ ኢኮኖሚያዊ ዕቅድ የተነደፈው ከኢትዮጵያ ብዙ ሃብትን በመውሰድ ነው። በቀላል አማርኛ ለመግለፅ ኢትዮጵያን እንደ የጓሮ አትክልት ስፍራ ነው የወሰዷት። ከዚያም በተጨማሪ በንግዱም ዘርፍ ሆነ በሌሎች ጉዳዮች የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት ያሳይ ነበር።

በተለይም በንግዱ ዘርፍ የኢትዮጵያ ሃብት የሆኑትን ልክ እንደ አንድ አምራችና ላኪ በመሆን ለምሳሌ የቡና ምርቶችን፣ ሰሊጥ፤ በኮንትሮባንድና የወርቅ ንግድ ይሳተፉ ነበር።

የውጭ ምንዛሬ የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋዊ ካስቀመጠው የልውውጥ መጠን ውጭ እነሱ በከፍተኛ ደረጃ በጥቁር ገበያ ዘርፍ ኤምባሲው እሱን ይሰራ ነበር።

ብዙ እልባት ያላገኙና ግልፅ ያሉ አካሄዶች ነበሩት። የጋራ የገንዘብ መገበያያ ፣ የወደብ አጠቃቀም የጠራ አካሄድ አልነበረውም።

ከዚህም በተጨማሪ በሁለቱ ሃገራት የሚገኙት የየሃገራቱ ህዝቦችን በተመለከተ በዝርዝር ተሂዶ የእነሱ መብትና የሥራ ስምሪት በሚገባ ተለይቶ የሄደበት ሁኔታ አልነበረም። የድንበር አከላለሉም በውዝፍ የቆየ ሥራ ነበር።

ብዙ ክፍተቶች ተፈጥረው ነው ግንኙነቱ የተመሰረተው፤ በጊዜው ልክ እንደ ሌሎች አገሮች እንደ ሁለት ሃገር ሆነው የሚሄዱበት ሁኔታ ከጅምሩ አልተሰመረም፤ አልተቀየሰም። ኢህአዴግም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ሥራ አልሰሩም።

ኢህአዴግ እንደ መንግሥት እኔም በነበርኩበት ወቅት በኤርትራ ጉዳይ ላይ ኃላፊነታችንን ተወጥተናል የሚል አቋም የለኝም። እነዚህ ሁሉ ክፍተቶች ለጦርነቱ እንደ ቆስቋሽና መነሻም ነበሩ።

• ኤርትራዊያን የሚሿቸው አምስት ለውጦች

ቢቢሲ አማርኛ፡ የኤምባሲው ሚና እንደ ሌሎች ገሮች ነበር? ወይስ ከኤርትራ ጋር በነበረው ግንኙነት ሚናው ይለያል?

አቶ አውዓሎም፡ ለየት ይላል ምክንያቱም የምፅዋና የአሰብን ወደቦች ብቸኛው ተጠቃሚ የኢትዮጵያ መንግሥት ስለነበር በሁለቱንም ወደቦችና ላሉት ሥራዎች በሙሉ እንደ በላይ ሃላፊ ሆኖ የውስጥና የውጭ ገቢውን የሚቆጣጠረው ኤምባሲው ነበር።

ከአሥመራ ውጭ በአሰብና በምፅዋ ኢትዮጵያ ቆንስላ ነበራት። ኢትዮጵያና ኤርትራ በጋራ ኖረው ሁለት አገር ስለሆኑ፤ በሁለቱም አካባቢ የሁለቱም ህዝቦች ነዋሪዎች አሉ። በዚህም ምክንያት ትንሽ ዘርዘር ያለና እስከ አሰብ ድረስ ሙሉ ዕውቅና ያላቸው በኢትዮጵያ በጀት የሚተዳደሩ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ባንክ፣ የጉምሩክ ሥራዎች፣ መሬት ላይ ነበሩ።

ከዚህም በተጨማሪ የድንበር ማካለል ጉዳይ፣ በጋራ ብር የመጠቀም ሁኔታ፣ ንግድን የመሳሰሉት ጉዳዮች በጋራ መወሰን ያለባቸው ናቸው። በሌሎች ሃገሮች ያሉትን ኤምባሲዎቻችንን ስናይ ምንም እንኳን በኢኮኖሚውም ሆነ በማህበራዊ ዘርፎች ሁለትዮሽ ግንኙነት ቢኖረንም እንደ ሁለት ሃገራት ነው ስምምነቶቹም ሆነ የንግድ ሽርክናዎች የሚመሰረቱት፤ ከኤርትራ ጋር ለየት ያለ ግንኙነት ነበረን።

ቢቢሲ አማርኛ፡ የሁለቱ ገራት ህዝቦችስ በሚጓጓዙበት ጊዜ የኤምባሲው ሚና ምን ነበር?

አቶ አውዓሎም፡ በአጎራባች አካባቢ ባሉ ለምሳሌ በአፋርና በትግራይ አካባቢዎች፤ ህዝቡ በአቅራቢያው ባሉት መስተዳድሮች የራሳቸውን አሰራር ፈጥሮ በነፃ እንዲንቀሳቀስ ተደርጓል። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማዳበር በድንበር አካባቢ የነበረው የቁጥጥር ሁኔታ ቀለል ያለና ነፃነት ያለው ነበር።

በተረፈ ግን በአውሮፕላን የሚጓጓዙት አየር ማረፊያዎቹ ላይ ሲደርሱ ቪዛ የሚያገኙበት መንገድ ተመቻችቶ ነበር። ሳይተገበር ጦርነቱ ተነሳ እንጂ በሂደትም የነፃ ቀጠና እንዲሆን ተወስኖ ነበር።

ቢቢሲ አማርኛ፡ የጦርነቱን መነሻ የመጀመሪያ ዓመታት እንዴት ያዩዋቸዋል?

አቶ አውዓሎም፡ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት እንደ ጫጉላ አይነት ነበር። በዝርዝር ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ የሄድንበት ሁኔታ አልነበረም። ለምሳሌ የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያን መንግሥት ሳያማክር ነው የራሱ መገበያያ ገንዘብ ናቅፋ ያሳተመው።

ይህንንም ሁኔታ ተከትሎ እንደማንኛውም ሃገር የመገበያያ ገንዘብ ሁለቱ ሃገራት በመረጡት እንገበያይ ማለቱ ጦርነቱን ቀስቅሶታል። የባድመ ጉዳይና የድንበር ማካለሉ ጉዳይ እንደ ችግርም አጀንዳም አልነበረም። ከጦርነቱ መቀስቀስ ጀርባ መነሻ ያሉት በሙሉ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ነበሩ። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን በመጨረሻ አይቶታል።

• ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የኢትዯጵያና የኤርትራ ሕዝቦች አንድ ናቸው አሉ

ቢቢሲ አማርኛ፡ ጦርነቱ ሲነሳ እርስዎ በወቅቱ የት ነበሩ? በአመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዕጣ ፈንታስ ምን ሆነ?

አቶ አውዓሎም፡ ጦርነቱ ከመጀመሩ ከቀናት በፊት አዲስ አበባ አንድ ስብሰባ ነበር። ድንበር ማካላል የሚባል አንድ የተዋቀረ ኮሚቴ ነበር። እኔም ከልዑካኖቹ ጋር አዲስ አበባ ነበርኩ። የኤርትራ ልዑካንም ሳይነግሩን ተመለሱ ከቀናት በኋላ ጦርነቱ ተነሳ።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ ይገኝ የነበረው አሥመራ ማሪናዮ የሚባል አካባቢ ሲሆን፤ የድሮ የባሕር ኃይል መስሪያ ቤት የነበረና የኤርትራ ህዝበ-ውሳኔውም የተካሄደው እዚሁ ነው። ያው ኤምባሲው ተዘጋ፤ ዋነኛ ንብረት የምንላቸውንም በመርከብ ጭነን ተመለስን።

ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት በሲኤምሲ አካባቢ ወደ 23 ሺ ካሬ ሜትር ለኤርትራ ኤምባሲ ግንባታ ሊያካሂዱ እቅድ ላይ የነበሩ ሲሆን፤ እኛም አሥመራ አየር ማሪፊያ አካባቢ 23 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቶን ካርታው ወጥቶ ሥራ ለመጀመር እቅድ ላይ ነበርን።

• የ “ጥርስ አልባው” ማዕቀብ መነሳት ፖለቲካ?

ቢቢሲ አማርኛ፡ አሁን ሁለቱ ሃገራት የሰላም ስምምነት ላይ ናቸው። ለወደፊትስ ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል? የኤምባሲዎቹስ ሚና ምን ሊሆን ይገባል?

አቶ አውዓሎም፡ ሰላምና ጦርነት በሌለበት ሁኔታ ተፋጠው የነበሩ ሃገራት ከጠላትነት ወጥተው፣ ከጦርነት ወጥተው ግንኙነት መጀመራቸው ግንኙነት መጀመራቸው መልካም ነው። ነገር ግን አሁንም ለጦርነቱ ምክንያት የነበሩ ጉዳዮች ተዳፍነው በጭራሽ ውይይት ሳይደረግባቸው ወደ ሰላም መምጣታቸው መጥፎ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ሁለቱም ሃገራት ሞቅ ሞቅ ያለ ሁኔታ ላይ ነው ያሉት ዘላቂነትን ለመፍጠር በጥልቀት የውይይትና ሥራ ያስፈልገዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከተቻለ የአሰብ ወደብ ባለቤትነት ጥያቄ ማቅረብ አለበት። የዛን ያህል ርቀት የኢትዮጵያ መንግሥት ይሄዳል የሚል ግምት የለኝም ነገር ግን የአሰብን ወደብ እንደ ጥያቄ ማንሳት አለበት።

የሰላም መዝሙሩ እንዳለ ሆኖ መሰረታዊ እልባት ካልተገኘለት ትርጉም ያለው ግንኙነት ይሆናል የሚል ዕምነት የለኝም።

እንደ ሁለት ሃገራት የኢኮኖሚ ሽርክና፣ወደብን እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ አቅጣጫ ቢያስቀምጡ ጋራ የፖለቲካና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች በጣም ከፍተኛ በሆነ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የአልጀርስ ስምምነት እንዳለ ሆኖ መሬት ላይ በአፋርም ሆነ በትግራይ ሁለቱ ከጦርነቱ በፊት በነበረው የየራሳቸውን መስተዳድር እንደነበረ ሆኖ ቢቀጥል ጥሩ ነው እላለሁ።