የኢትዮጵያ መንግሥት የሚወቀስባቸው የስቅየት ድርጊቶች:- DW

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚወቀስባቸው የስቅየት ድርጊቶች:-DW

(DW) — ከአዲስ አበባው የፖሊስ ወንጀል ምርምራ ዋና መሥሪያ ቤት (ማዕከላዊ) እስከ ቃሊቲ እና ቂሊንጦ ማረሚያ ቤቶች ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስቅየት ደረሰብን ሲሉ ይደመጣል። በተለይ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተጠርጥረው የታሰሩ ኢትዮጵያውያን እንደሚሉት መርማሪ ፖሊሶች የሚፈልጉትን መረጃ ለማግኘት እስረኞችን ይደበድባሉ፤ያንገላታሉ፤ ያሰቃያሉም።

በስደት ግብጽ የሚኖረው የቀድሞው መምህር ቤኛ ገመዳ የአዲስ አበባውን ማዕከላዊ የወንጀል የምርመራ ቢሮ ሲያስታዉስ እንቅልፍ ይነሳዋል። በኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) አባልነት ተጠርጥሮ ከሚሰራበት የጋምቤላ ክልል ወደ ምርመራ ቢሮው እንደተወሰደ የሚናገረው ቤኛ በጎርጎሮሳዊው የዘመን አቆጣጠር ከ2011-2015 ዓ.ም. በተለያዩ እስር ቤቶች ቆይቷል። ቤኛ እንደሚለው በአዲስ አበባ ማዕከላዊ ወንጀል ምርምራ ዋና መሥሪያ ቤት (ማዕከላዊ) ሲደርስ መጀመሪያ የታሰረው ከጭለማ ቤት ነበር።

“ወዲያው ቀጥታ በኢትዮጵያ መንግሥት አጠራር 84 ተብሎ የሚጠራ ወይ ደግሞ ጨለማ ቤት ምንም መብራት የሌለበት ውስጥ ገባሁኝ እና አራት ወር ሙሉ ታሰርኩኝ። እዛ እስር ቤት ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ወደ ቢሯቸው እየጠሩኝ የተለያዩ ሰቆቃ ግፍ ያደረጉብኝ ነበር። ጀርባዬን በኤሌክትሪክ ቶርች እያደረጉ እያቃጠሉ፤ጥፍሬን በከስክስ ጫማ እየረገጡ፤እየነቀሉ በጥፍር መቁረጫ እየጎተቱ ፤ውሐ እያርከፈከፉብኝ፤በኤሌክትሪክ ሽቦ እየገረፉኝ እኔ የማላውቀውን ነገር እመን፤ይሔን አድርገሃል፤የምታውቀውን ተናገር እያሉ እየደበደቡ ምርመራ ከሌሊቱ 7 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት እያደረጉብኝ ወደ ጨለማ ቤት እየመለሱኝ ነበር።”

ታች አርማጭሆ ተወልዶ  ጎንደር ያደገው ወገኑ ማስረሻ (ስሙ የተቀየረ) የእስር ቤት ታሪኩን ለመናገር ሥጋት ይጫነዋል። “ብዙ ግፎችን አሳልፊያለሁ” የሚለው ወገኑ ከተደጋጋሚ የእስር ቤት ምልልስ በኋላ ተወልዶ ካደገበት ፤ቤተሰብም ከመሰረተበት ርቆ ለመኖር መገደዱን ይናገራል። “ሌባ ታደራጃለህ” የሚለውን ጨምሮ ፖለቲካዊ ክሶች በመርማሪዎች እንደቀረበበት የሚናገረው ወገኑ “ያለ ምንም ወንጀል ጎንደር ከተማ ውስጥ ሁለት አመት” እንደታሰረ ይናገራል።

“እኔ በገባሁባቸው ቀኖች ያልተመታሁበት ያልተደበደብኩበት ቀን የለም። አንዴ ራሴን እስክስት ለሶስት ለአራት ረጅም ሰዓት ከደበደቡኝ በኋላ እኔ ራሴን ስቼ ከጥቂት ሰዓት በኋላ ራሴን ያወኩኝ። ለመረጃ ተብሎ ነው ብቻዬን ያሰሩኝ በሰዓቱ። በጣም የሚገርመው ግን እኔ ጎንደር ከተማ ውስጥ እኔ ሰርቼ የማውቀው ወንጀል የለም። ሌባ ታደራጃለህ፤ከፖለቲካም ጋ ም ታደራጃለህ እንደዚህ ነው።ሽፍታ የሚባል አለ በሰዓቱ አርበኞች ግንባር እንደሚባሉት እንደዚህ እነሱ ጋ ግንኙነት አለህ ተብሎ በቃ

አጋልጥ ተናገር {እባላለሁ} እኔ ምንም የማውቀው ነገር ስለሌለ የምገልጸውም ምንም ነገር የለም። ዱላው ብቻ ነው ትርፌ”

በኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር አባልነት ተጠርጥረው ሰባት አመታትን በእስር እንዳሳለፉ የሚናገሩት የአዲስ አበባ ነዋሪ  እንደ ወገኑ ሁሉ የደኅንነት ሥጋት ይሰማቸዋል። በእስር ቤት “ብዙ ድብደባ እና መጎሳቆል” ገጥሞኛል የሚሉት ግለሰብ ማንነታቸውን መናገር አይፈልጉም። ከስምንት አመታት በፊት ከሌሎች 13 ሰዎች ጋር ታስሬ ነበር የሚሉት ሰው “ኦሮሞን ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ለመነጠል” ጥረት አድርጋችኋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በእስር ቤት የተመለከቷቸው፤ በምርመራ ወቅትም ደረሱብኝ የሚሏቸው በደሎች አሏቸው።

“ሰዎችን በማሰር የሰው ብልት ላይ ሐይላንድ እና ጀሪካን ውሐ ሞልቶ ማንጠልጠል፤ሰዎችን አንጠልጥሎ በመብራት የማስፈራራት በኤሌክትሪክ የመምታት፤በኤሌክትሪክ ንዝረት የማስፈራራት ይኸም ካልበቃ ደግሞ እስከ መገደል ድረስ የሚሔድ ማስፈራሪያ ድረስ ነው እንግዲህ ወንጀል ምርመራ የሚካሔደው። እኔ እንግዲህ ድብደባም ተፈፅሞብኛል። በኤሌክትሪክም ተመትቻለሁ። ቃለ-መጠይቅ መስጠት አለብህ እንደዚህ አይነት ነገር እኔ ነኝ ያደረኩት ብለህ ቃል መስጠት አለብህ በሚል ብዙ ድብደባ ተፈፅሞብኛል። በአካሌ ላይም ብዙ ጠባሳዎች እንትን ብለውብኛል።”

ጉዳዮ የሚመለከታቸዉ የኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣናት ለቀረቡት ወቀሳዎች ምላሽ እንዲሰጡን ያደረግንው ሙከራ አልሰመረም። የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ባለሥልጣናት ጥሪዎቻችንን አይመልሱም። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቃል-አቀባይ የሰጡንን ቀጠሮ አላከበሩም።

በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሚሰነዘሩት ወቀሳዎች ግን ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንግዳ አይደሉም። ሒውማን ራይትስ ዎች ከአራት አመታት በፊት ባወጣው ሐተታ “የማዕከላዊ መርማሪዎች የተጠርጣሪዎችን የእምነት ክሕደት ቃል ለመቀበል እና ሌሎች መረጃዎች ለማሰባሰብ እስከ ስቅየት (ቶርቸር) የሚደርሱ አስገዳጅ ሥልቶች ይጠቀማሉ” ሲል ወቅሶ ነበር። ሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ባለፈው ሰኔ ባወጣው ሌላ ዘገባ ሕገ-መንግሥቱ እና በሕግ የተከለከሉት ታሳሪዎችን የማሰቃየት እና የማንገላታት ድርጊቶች በጸጥታ ኃይሎች ይፈጸማሉ ብሎ ነበር።

“የማረሚያ ቤቶች እና የቅድመ-ክስ ሒደት ማቆያ ማዕከላት ይዞታ በአስከፊ ደረጃ ላይ የሚገኝ እና በአንዳንድ ሁኔታዎችም ለሕይወት አስጊ እንደሆነ” የሚገልጠው ደግሞ ያለፈው ዓመት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሰብዓዊ መብት ዘገባ ነው። ዘገባው ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ወደ 20,000 ገደማ ተቃዋሚዎችን ባሰረችበት ዓመት “በማዕከላዊ፤ በይፋ የሚታወቁና የማይታወቁ እስር ቤቶች፤ በፖሊስ ጣቢያዎች እና በቅሊንጦ ፌዴራል ማረሚያ ቤት ውስጥ ታሳሪዎች በግፍ እንደተያዙ” ገልጧል።

ከሌሎች 20 ተጠርጣሪዎች ጋር በአወዛጋቢው የጸረ-ሽብር አዋጅ ክስ ተመስርቶበት እንደነበር የሚናገረው ቤኛ ገመዳ ከማዕከላዊ እስከ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ድርስ በእስር ላይ ቆይቷል። እርሱ እንደሚለው በማዕከላዊ የደረሰበትን ለፍርድ ቤት ቢናገርም መፍትሔ ግን አላገኘም።

“አራዳ የሚባል ፍርድ ቤት አለ። በየ28ቱ ቀን በጸረ-ሽብር ሕግ {ተከሰን} እያቀረቡን ነበር። እዛ ውስጥ እየተገረፍን ነው፤እየተደበደብን ነው፤ታመን ሕክምና አናገኝም ጭለማ ቤት ውስጥ ስለምንታሰር አይናችን እየጠፋ ነው። ብርሐን እያየን አይደለም ተጎድተናል። ብለን ስንጮህ  ፍርድ ቤቱ ምንም ጆሮ አይሰጠንም። አራት ወር ሙሉ ፍርድ ቤት ከቀረብኩ በኋላ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አዛወሩኝ። ፌዴራል ልደታ ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት  ተከሳሽ ሆኜ ነው የቀረብኩኝ። ከ20 ተከሳሾች ውስጥ ፍርድ ቤት ሶስት ሰዎች ነፃ አወጣን ። እኔ ሶስት አመት ከሁለት ወር ከታሰርኩኝ በኋላ ፍርድ ቤት በነፃ አሰናበተኝ።”

ወገኑ እንደሚለው እርሱ ጎንደር እስር ቤት ሲገባ ትዳሩ ተበትኗል። የተፈረደበትን የሁለት አመት እስራት አጠናቆ ሲወጣ ልጁን እንኳ ማሳደግ አልቻለም። “ያሳለፍኩንትን ሳስታውስ ብንን ያደርገኛል” የሚለው ቤኛ የደረሰበትም ይሁን የታዘበው “ዜጋ ላይ ሳይሆን ጠላት ላይም አይደረግም” ሲል ይናገራል። ርቆ የተጓዘው ቤኛ “እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም እንዴ?” ሲል ይጠይቃል። ለጥያቄው ግን የሚከሳቸው ምላሽ ሊሰጡ አልፈቀዱም።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ