የኢትዮጵያ ህዝቦች ቀጣይ የትግል አቅጣጫ ምን መሆን አለበት?

ይህንን ምርጥ መንገድ አመላካች ትንተና ወንድማችን ዶር Birhanemeskel Abebe Segni አቅርቦታል። ዶርን አመሰግናለሁ

የኢትዮጵያ ህዝቦች ቀጣይ የትግል አቅጣጫ ምን መሆን አለበት?

1፣ መግቢያ፣

ዘረኞቹ እና ሸፍጠኞቹ አሃዳዊያን፣ በእኔ ላይ ከከፍቱት ተከታታይ ስም የማጥፋት ዘመቻ አልፋው፣ 1) ኦሮሙማን (ኦሮሞነትን) ገለናል፣ 2) የኦሮሞን ህዝብ የነፃነት እና የእኩልነት ትግል በትነናል፣ 3) ኦሮሞን እርስ በርሱ አባልተን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመስዋዕት በግ አድርገናል(በሌላ አገላለፅ አንዱን ኦሮሞ እንደ ዱላ ተጠቅመን ሌላውን ኦሮሞ መተናል)፣4) የኦሮሞን ህዝብ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት እና በአከባቢ ከፋፍለን አባልተናል፣ 5) የኦሮሞ ብሄርተኞችን በአሃዳዊያኑ ከተሞሉት የኢትዮጵያ ተቋማት መንጥረናል ፣ 6) በኦሮሞ ህዝብ ግንባር ቀደም መሪነት የመጧውን ለውጥ ቀልብሰና፣ ወዘተ እያሉ ጮጴ እየረገጡ እና እየፈነደቁ ይገኛሉ። አሃዳዊያኑ በህልማቸው በርካታ የኦሮሞ እኩልነት ትግል መሪዎችን ገለው፣ ቀብረው፣ ታስካራቸውን እያወጡ ይገኛሉ።

ይህ የአሃዳዊያኑ ፉከራ እና ቀረርቶ፣ ባዶ የቁራ ጩኸት ሳይሆን፣ ከውስጥ እና ከውጭ ተናበው የሚሰሩ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ተቋማትን ከተቆጣጠሩ ዘረኛ እና አግላይ ኃይሎች እየመጣ መሆኑ፣ ለሁሉም የእኩል የሆነች (all inclusive) ኢትዮጵያን የመፍጠር ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በላይ የዘለቀው የሰፊው የኢትዮጵያ ጭቁን ህዝብ ትግል ገና ከግቡ ያለመድረሱን እና አዲስ የትግል ምዕራፍ መከፈቱን አመልካች ነው።

ይህ እውነታ እንደ ኦሮሞ ያሉ የኦትዮጵያ ጭቁን ህዝቦች ትግል ያለበትን ደረጃ እና የወደፊት የትግል አቅጣጫን እንደ ገና እንድናጤን ግድ ይለናል። ይህ ደግሞ አገራዊ እና ህዝባዊ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ትግል የተሰው ሰመዓታት ደም እና መጭው ትውልድ ከእኛ በግልም ሆነ እንደ ህዝብ የሚጠብቁት የትውልዶች አደራ ነው።

የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እንደ ህዝብ የቡድን መብታቸውን ሳያስከበሩ፣ ከዚህ ህዝብ አብራክ የወጡት እና ወደ ፊትም የሚወጡት ግለሰቦች(ሙሁራንም ቢሆኑ)፣ እኳን በነፃነት የመኖር፣ የማሰብ መብታቸው እንኳን፣ለአሃዳዊያኑ ብቻ አገር እንድትሆን በተፈጠረችው አሮጌዋ ኢትዮጵያ እንደማይከበሩ የአሃዳዊያኑ የሰሞኑ ተከታታይ ዘረኛ እና አግላይ ጥቃቶች ምስክሮች ናቸው።

በተለይም ደግሞ፣ የሰሜን የፖላቲካ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያን የመንግስት የፖለቲካ ስልጣን ይዘው፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦችን(የኦሮሞ ህዝብን ጨምሮ) 1ኛ) የሰው ኃይሉን በፊውዳሉ ዘመን ጭሰኛ፣ አሁን ደግሞ ባለንብረት ሳይሆን ተቀጣሪ ሰራተኛ አድርገው የሚበዘብዙበት፣ 2ኛ) የደቡቡን ህዝብ መሬት፣ “መሬት የመንግስት ነው(መንግስት እነርሱ ስለሆኑ) ” በሚል ሸፍጥ ፖላቲካውን ተቆጣጠረው የጭቁኑን ህዝባችንን መሬት በመቆጣጠር፣ ህዝባችንን መሬት አልባ ያደረጉበት፣ 3ኛ) የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ መዋቅሮችን በመያዝ የደቡቡን ህዝብ የተፈጥሮ ሃብቱን የሚዘርፉበት እና የደቡቡን ህዝብ አገር አልባ ያደረጉበት፣ 4ኛ) አሃዳዊያኑ ገዥ፣ የደቡቡ ህዝብ አገር አልባ እና ተገዥ የሆነበት፣ የኢትዮጵያ ፖላቲካ ኢኮኖሚ ስረዓት ሙሉ በሙሉ ፍርሶ፣ ኢትዮጵያ ለሁሉም ህዝቦቿ የእኩልነት፣ የፍትህ እና የርዕትህ አገር ባልሆችበት ሁኔታ፣ የአሃዳዊያኑን የተቀናጀ እና የተደራጀ ዘመቻን በቸልታ ማለፍ ለዳግም ባርነት ራስን መዳረግ ነው።

ስለዚህ ይህ ስር ነቀል ለውጥ የሚሻ የአሃዳዊያኑ አደጋ እንደ ተራራ አንጋጦ በፊታችን በቆመበት ሁኔታ፣ ሰሞኑን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የመንግስትን ዕድሜ ለማራዘም ያሉ ህገ መንግስታዊ ክፍተቶችን ለማፈላለግ እና ስለምርጫ ጊዜ መወሰን ላይ የሚደረጉት ሰጣ ገባዎች የኢትዮጵያን መሠረታዊ ስረዓታዊ ችግሮችን የዘነጉ እና የኢትዮጵያን ስረዓታዊ ችግሮች የበለጠ ያወሳስቡት ይሆናል እንጂ አንዳችም የሚፈቱት የኢትዮጵያ ህዝብ ችግሮች አይኖሩም።

አሁን ለፖላቲካ ታክቲክ ወይም ባለማወቅ ቀለል ተደርገው የሚታዩት አሃዳዊያኑ እየፈጠሩ ያሉት የኢትዮጵያ ችግሮች፣ የህገ መንግስት መከበር እና የምርጫ ጉዳይ ብቻ ቢሆኑ ኖሮ፣ በአፄው፣ በደርግ እና በህወሃት ዘመን ነፃ አውጭ ግንባሮችን አደራጅተን ከምንተላለቅ፣ ጥሩ ጥሩ ጠበቆችን አፍርተን እና አከራክረን፣ በህጋዊ መንገድ ብቻ በፈታናቸው እና ባለፍናቸው ነበር።

የኢትዮጵያ ችግሮች በዘረኝነት፣ በመድሎ እና በአግላይነት ላይ የተመሰረቱ የፖላቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ተቋማትን እና እነዚህን ዘረኛ ተቋማትን የወለደውን ስረዓታዊ አስተሳሰቦች እና የኃይል አሰላለፎች አፍርሶ፣ አዲስ እና ሁሉን አካታች (all inclusive) ሀገረ መንግስታዊ ስረዓት የመመሥረት እንጂ፣ ዘረኛውን እና አግላይ ስረዓቱን በምርጫ እና በህገ መንግስት ጠጠሮች ደግፎ ለማስቀጠል መሞከር አይደለም።

የዘረኛው እና የአግላዩ ስረዓት ሰለባ የሆነው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በተለይም ደግሞ የአሁኑን ለውጥ በማምጣት ከፍተኛ ዋጋ የከፈለው የኦሮሞ ህዝብ፣ ከ1966ቱ አብዮት እና ከ1983ቱ ለውጥ ውድቀት መማር ያለበት አንድ ትልቅ ቁምነገር ቢኖር፣ ይህን ዘረኛ እና አግላይ ስረዓት አፍርሶ፣ በአዲስ ስረዓት መተካት እንጂ፣ ያረጀውን፣ በአግላይ እና በጠባብ መሠረት ላይ የቆመውን ፈራሽ ሥረዓት መጠጋገን የትም እንደማያደርሰን መገንዘብ ነው።

ይህ ለውጥ የዛሬ ሁለት ዓመት ሲመጣ፣ ኢትዮጵያን በዲሞክራሳዊ ሽግግር ሂደት፣ የሁሉም ህዝቦቿ የእኩል እና የፍትህ አገር የማድረጉ ተስፋ በህዝብ ዘንድ በፍጥነት እየተበተነ ፣ ህዝባዊ ትግሉ በተደራጁ ቡድኖች መካከል የስልጣን ሽሚያ እየመሰለ፣ በአሃዳዊያኑ ፉከራ እና ጩኸት መተካቱ፣ በትግሉ ላለቀው ህዝብ እና ትግሉን ለሚመሩት የመጨረሻ የማስጠንቀቂያ ደውል ነው። ዘረኛ እና አግላይ አሃዳዊያን፣ ለውጡ ባማጣው ክፍተት ተጠቅመው፣ ለእኩልነት እና ለፍትህ ከመስራት ይልቅ፣ የአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ተቋማትን re-activate በማድረግ፣ የተደራጀ እና የተቀናጀ ብሄር ተኮር ዘረኝነት እና መድሎ የሚፈፅሙበት መሰሪ ስረዓቶች በኢትዮጵያ ውስጥ እንደገና በከፋ ሁኔታ እየገነቡ መሆኑ፣ የህዝባዊ ትግሉን አቅጣጫ እና አጠቃላይ ይዘት እንደገና እንድናጤን ግድ ይለናል።

በህወሃት/ኢህደግ ዘመን የኢህዴግ መንግስት ተብሎ ለሚታወቀው ጉዑዝ አካል፣ የህወሃት ተቋማት እንደ deep state(ስውር መንግስት) ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበረ ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያ፣ ዘረኛ እና አግላይ አሃዳዊያን፣ የኢትዮጵያ ከተሞችን፣ የመንግስት ተቋማትን፣ የኢኮኖሚ ተቋማትን፣ የሚዲያ ተቋማትን፣ የባህል እና ማህበራዊ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በመያዝ፣ አዲስ ስውር መንግስት( deep state) ሆነው እየተደራጁ ያሉበት አገር ሆናለች። ይህ የኢትዮጵያ ፈተናዎችን አብስቷል፣ አወሳስቧል።

2፣ የኢትዮጵያ ትላልቅ ፈተናዎች፣

ኢትዮጵያ አሁን በአምስት ትላልቅ ፈተናዎች ውስጥ ተጠምዳለች።

አንደኛ፣ በህወሃት ዘመን የተፈጠሩ ችግሮች እና የህዝብ ጥያቄዎች በለውጡ ሂደት ስላልተፈቱ እና ምላሽ ስላልአገኙ፣ እያመረቀዙ እና የህዝብን ሮሮ እያባባሱት ይገኛሉ።

ሁለተኛ፣ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተፈጠሩት ችግሮች በደርግ እና በህወሃት ዘመን በትክክል ስላልተፈቱ፣ የአሃዳዊያኑ ከለውጡ በኋላ በተፈጠረላቸው አዲስ አጋጣሚ እንደገና አቆጥቁጦው እና አዲስ ኃይል ሆነው ኢትዮጵያን አንቀው ይዘዋል። የኢትዮጵያ ህዝብም ትግል በመጣበት ፍጥነት ከህወሃት ወደ ዘረኛ እና አግላዮቹ አሃዳዊያን ዞሯል።

ሶስተኛ፣ ለዚህ ለውጥ መምጣት ምክንያት የሆነውን፣ የኢትዮጵያ ህዝብን የፍትህ፣ የእኩልነት እና የርዕትህ ጥያቄዎችን የሚመልስ አዲስ ስረዓት እንኳን ሊወለድ፣ ባለመፀነሱ፣ ህዝብ ግራ ተጋብቶ ተስፋ አልባ እንዲሆን አድርጓል። የፖላቲካ ትርክቱም አዲስ ስረዓት በመፍጠር ላይ ሳይሆን፣ በህወሃት ዘመን በነበረው እና በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን በነበሩት ሁለት አሮጌ ስረዓቶች መካከል አንዱን ምረጡ የተባለ ይመስላል።

አራተኛ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ግራ መጋባት እና ጎራ መደበላለቅ የተገነዘቡ የቅርብ እና የሩቅ አገሮች በኢትዮጵያ የየራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ፣ ኢትዮጵያን የአጀንዳቸው ማራመጃ ቤተ ሙከራ ለማድረግ እየሰሩ ይገኛሉ። አውሮፖዎች በባርሊን ኮንፍራንስ ጀርመን አገር ላይ ተሰብስበው አፍርካን ሲካፋፋሉ፣ በአደዋ ጦርነት ከቅኝ ግዛት የተረፈችው ኢትዮጵያ አሁን አፍርካን 1ኛ) በፀጥታ ቀጠና፣ 2ኛ) በኢኮኖሚ ቀጠና እና 3ኛ) በሃይማኖት ቀጠና ከፋፍሎ ለመቀራመት እየተደረገ ከለው አደጋ የምታመልጥ አትመስል። ለኢትዮጵያ ህዝብ ህልውና፣ ከዱሮው መቀራመት፣ የአሁኑ የከፋ መሆንን ግን መሳት የለብንም።

አምስተኛ፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ በሽታው ኢትዮጵያን አጠቃ፣ አላጠቃ፣ ኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ በአለም ዙሪያ የሚፈጥረው የፖላቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ቀውስ ሰለባ መሆኗ ሳይታለም የተፈታ ነው።

እጅግ የሚገርመው ግን፣ እነዚህን ግዙፍ አደጋዎች የተጫኑባት ኢትዮጵያ፣ ከውስጥ የፖላቲካ እቃቃ ጨወታ ወጥታ አንድም ትርጉም ያለው ምክክርም ሆነ አቅጣጫ ጠቋሚ ስራ ያለመስሯቷ ነው።

ለምሳሌ፣ አንደኛ እና ሁለተኛ የኢትዮጵያ ፈተናዎችን እንኳን ብንመለከት፣ በለውጡ ሂደት በህወሃት ዘመን የተፈጠሩት ችግሮች ሳይፈቱ፣ የአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ችግሮች እንዳሉ፣ በአሃዳዎያኑ ዘረኝነት እና አግላይነት ታጅበው፣ የኢትዮጵያን አሮጌ ተቋማት ስለተቆጣጠሩ፣ እጅግ በሚያሳስብ ሁኔታ ለውጥ ፈላጊው ህዝብ ከለውጡ ሸሽቶ፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለውጡ ከመጣበት ከህወሃት ጋር እንዲያብር እና ከአሃዳዊያኑ ለሚመጣበት እጅግ ዘረኛ ዘመቻ ራሱን ለመከላከል ህወሃትን እንደ አዲስ አጋር ኃይል እንዲያይ የሚያደርግ አዲስ ፖላቲካዊ ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህን የጎራ መደበላለቅ የፈጠሩ ብዙ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፣ የለውጥ ኃይሉ ማህበራዊ መሰረቱን ይዞ ሳይደራጅ በመበታተኑ እና ወደ ኋላ እንጂ ወደ ፊት ማየት የማይችለው ዘረኛ እና አግላይ አሃዳዊ ቡድን ከለውጡ በኋላ የኢትዮጵያን ተቋማት ሙሉ በሙሉ በመያዛቸው ነው። ሁለተኛ፣ ዘረኛው እና አግላዩ ቡድን የኢትዮጵያ ህዝብ ነገ የተሻለች አገር አንዲፈጥር ሳይሆን፣ ህዝብ በህወሃት ዘመን እንኳን አገኛው የሚላቸውን የባህል እና የቋንቋ መብቶች እንዲቀለበሱ በማድረግ፣ በአፄው ዘመን የነበረችውን Assimilationist ኢትዮጵያ ዳግም ለመፍጠር የሚሰራ ፀረ አንድነት እና ፀረ እኩልነት ኃይል መሆኑ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ይህ ሁኔታ ደግሞ፣ ለውጡን ቀልብሶ፣ ኢትዮጵያን ለስር ነቀል አብዮት ወይም የእርስ በርስ ጦርነት የሚዳርግ፣ ከለውጡ በኋላ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ፣ የኢትዮጵያን ፖላቲካ ማዕከላዊ ስፍራ የያዘው ዘረኛው እና ገፉው አሃዳዊ ቡድን መሆኑን፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከወዲሁ ማወቅ አለበት።

ሶስተኛውን አደጋ በተመለከተ፣ በህወሃት እና በአፄው ዘመን የተፈጠሩትን ሰረዓቶች የሚተካ አዲስ ስረዓት ባለመቀረፁ እና እንደ ጭንቁር የሚባሉት ዘረኛ አሃዳዊያን የአሮጌዎን ኢትዮጵያ የፖላቲካ መዕከል ስለያዙ፣ እኩልነት የሚፈልገው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በተለይም ለበርካታ ዓመታት በነፃ አውጭ ፖላቲካ ውስጥ ሲዳክር የኖረው፣ የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የሱማሌ፣ የሲዳማ፣ የአፋር፣ የጋምቤላ እና ወዘተ ህዝቦች፣ በኢትዮጵያ የማሃል ፖለቲካ ቤት አልባ ስለተደረጉ፣ ወደ ዳር ፖለቲካ ተመልሰው የየራሳቸውን ነፃ አገር ማቋቋም ወደ ሚለው አማራጭ በድብቅ የሚመከር የፖለቲከኞች ውይይት ሳይሆን በህዝብ ልብ እየተመዘነ ያለ አዲስ የፖለቲካ አማራጭ ሆኖ እየቀረበ ይገኛል። ኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ(all inclusive) የእኩልነት፣ የፍትህ እና የርዕትህ አገር እናደርጋለን፣ የህዝብ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ መዕቀፍ ይፈታሉ፣ ብለን ብዙ ዋጋ ለከፈልን፣ ይህ ለውጥ በአሃዳዊያኑ ከተቀለበሰ፣ ትልቅ አገራዊ ክስረት ነው።

አራተኛውን ፈተናም ካየን የውሸት ፉከራውና ቀረርቶውን ወደ ጎን ትተን፣ የቅርብ እና የሩቅ አገሮች የየራሳቸውን ብሄራዊ አጀንዳ በኢትዮጵያ እንዳያስፈፅሙ፣ የሚከለክል አገራዊ አንድነትም ሆነ ተቋማዊ ጥንካሬ በኢትዮጵያ ተዳክሟል። ሰሚ እና ሰሪ የለም እንጂ፣ማጠናከር ግን ይቻላል።

ቀጥለን አሃዳዊያኑ በፍጥነት የህወሃትን እግር ተክተው እንዴት የኢትዮጵያ ተቋማትን እንደተቆጣጠሩ እና እንዴት ለለውጡ ትልቅ ደንቃራ እንደሆኑ ዘርዘር አርገን እንመለከታለን ። በመጀመሪያ ግን ለውጡን ለአሃዳዊያኑ መፈንጫ ያደረጉ የለውጡን ድክመቶች እናያለን።

3፣ የለውጡ ውስጣዊ (intrinsic) እና መዋቅራዊ (structural) ድክመቶች፣

ለውጡ አዝሎት የመጣው ውስጣዊ እና መዋቅራዊ ችግሮች አሉ። እነዚህን ድክመቶች አምኖ ከመቀበል ብንጀምር ውይይታችንን እውነተኛ ያደርገዋል። ያን ሳናደርግ የለውጡን ችግሮች ሁሉ ውጫዊ (external) ብቻ አድርገን፣ በአሃዳዊያኑ ላይ ብቻ ከነጣጠርን፣ እውነተኛ መፍትሄ አናገኝም። ስለዚህ ከለውጡ ድክመቶች መጀመር ለውጡን ለማስቀጠል እና ትግሉን አጠናክሮ ለመቀጠል እጅግ አስፈላጊ ነው።

ከሁሉ በፊት ግን አንድ ለሁሉም ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ አለ። የ1966ቱ አብዮትም ሆነ የ1983 ለውጥ የታገለው እና ሙሉ ለሙሉ ሳይነቅለው የቀረው የአሃዳዊያኑን ዘረኛ እና አግላይ አገዛዝ ነበር።

የ2018ቱ ለውጥ በተቃራኒው፣ ትኩረት ያደረገው ህወሃት ላይ ብቻ በመሆኑ፣ የ1966ቱን አብዮት (በደርግ የተቀማው ለውጥ) እና የ1983ቱ(ህወሃት መራሹ ለውጥ) የወደቁበትን መሰረታዊ( inbuilt and intrinsic) ችግሮች ሳያጤን የመጣ ለውጥ ነው። እነዚህ እጥረቶች ደግሞ የአሁኑ ለውጥ፣ ከሁለቱ ለውጦች አጭር ህይወት የሚኖር (short lived ) እና ምንም ፍሬ ሳያፈራ ሊያልፍ የሚችል (inconsequential) የመሆን ዕድሉን ከፍተኛ ያደርገዋል።

የታሰበውን ያህል ባይሆንም፣ የ1966ቱ ደርግ መራሽ አብዮትም ሆነ የ1983ቱ ህወሃት መራሽ ለውጥ የሚጥሉትን ስረዓት እና በምን እንደሚተኩት ያውቁ ነበር። የ1966ቱ አብዮት የአፄውን ጭሰኛ ስረዓት አፍርሶ በሶሻልስት ስረዓት እንደሚተካ፣ አብዮቱን ለመሩት ሁሉ ግልፅ ነበር። የ1983ቱ ለውጥ መሪዎችም የደርግን አሃዳዉ የክፍለ ሃገር መዋቅር አፍርሰው፣ በፌዴሬሽን(በተግባር ስራ ላይ ባያውሉትም) ልተኩት እንደወሰኑ አስቀድመው ያውቁ ነበር። የሚያዚያ 2018ቱ ለውጥ በተቃራኒው ግን ህወሃትን ከስልጣን ከማውረድ ባሻገር፣ በምን ስረዓት እንደሚተካው በግልፅ ያስቀመጠው አላማ አልነበረውም። ለውጡም አገራዊ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን ለምርጫ ፖላቲካ ስረዓት ማመቻቻ እንዲመስል ያደረገው ይኸው በትግሉ ወቅት ስረዓታዊ ለውጥ የማምጣቱ አላማ በግልፅ ያለመቀመጡ ነው። (በምርጫ ፖላቲካ ላይ እመለሳለሁ። )

ለምሳሌ፣ የ1966ቱ አብዮት በመሬት ላራሹ ፣ በከተማ ትርፍ ቤት እና በሶሻልስት ሪዖት(አይዶሎጂ) አውጆ መለስተኛ ጠቀሜታ ለህዝቡ አምጥቷል። የ1983ቱ ለውጥም የብሄር ብሄረሰቦችን ጥያቄዎች ለመመለ ክልሎችን በመፈጠር፣ ለውጡን ያመጠውን ህዝብ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እንዲታገስ አድርጓል። የ2018ቱ ለውጥ ግን ለውጡን ላመጣው ህዝብ አንድም ማስታገሻ እንኳን ሳይሰጥ የለውጡ ደጋፊዎችን እያጣ እና የህዝብ ድጋፍም እያንጠባጠበ ይገኛል። ይህ በቶሎ ካልታረመ፣ ኢትዮጵያ መሸከም ወደ ማትችለው፣ ከአሁኑ ለውጥ ወደ ሌላ፣ ምናልባትም ሰላማዊ ወደ ያልሆነ ሌላ ለውጥ ልታመራ እንደምትችል አደገኛ አዝማሚያዎች አሉ።

ሌላው የ2018ቱ ለውጥ ከ1966ቱ እና ከ1983ቱ ለውጦች ያልተማረው፣ ህዝባዊ ለውጥ በተደራጀ እና በተማከለ አመራር ከልተመራ(structured ካልሆነ) ፍሬ አንደማያመጣ መታወቅ ነበረበት። በሁለት የተደራጁ ኃይሎች የተመራው የ1966ቱን አብዮት(በወታደሩ) እና የ1983ቱን ህወሃት መምራታቸው ለውጡ ላስመዘገባቸው የተወሰኑ ስኬቶች ምክንያት መሆኑን በሚገባ መጤን እና ልምድ መወሰድ ነበረበት።

የ2018ቱ ለውጥ በትርክት ደረጃ፣ በደርግ እና በህወሃት ያልተመለሱ፣ 1) የቋንቋ፣ 2) የመሬት ባለቤትነት፣ 3) ራስን በራስ የማስተዳደር፣ 4) ቀደምት ስረዓቶች የፈጠሩትን የብሄር ድንበርን ተከትለው የተፈጠሩ የጎንዮሽ መበላለጦች (horizontal economic, political and social inequalities) ማስተካከል፣ 5) የኢትዮጵያ ሃገረ መንግስት የቆመበትን ዘረኛ እና አግላይ አሃዳዊ መዋቅር አፍርሶ ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር ነበር።

ነገር ግን በዋነኛነት በኦሮሞ ህዝብ መሪነት የመጣው የ2018ቱ ለውጥ ከላይ የዘረዘርኳቸውን ትርክቶች ማታገያ አድርጎ ህዝብን ለለውጥ ማነሳሳት ቢችልም፣ ከላይ የተመለከቱ እና ሌሎች ቁልፍ እጥረቶች ለዛሬው የለውጡ መቀጨጭ ምክንያት ሆኗል። እነርሱም፣ 1ኛ) ለውጡ የሚመራው ድርጅት አልነበረውም፣ 2ኛ) አክቲቨስቶች እንጂ የተማከለ አመራር አልነበረውም፣ 3ኛ) ጥያቄዎች ማንሳት እንጂ፣ የህዝብ ጥያቄዎችን በኢትዮጵያ የሚመልስ የመንግስት ለውጥ( regime change) ማድረግ ብቻ ሳይሆን የስረዓት ለውጥ (system change) ማምጣት መሆኑን በግልፅ አላስቀመጠም፣ 4ኛ) በህዝባዊ ብሶት እና ህወሃትን ከስልጣን ካባረርን የባሰ አይመጣም በሚል publicist እሳቤ ጉድለቶቹን ሳይሞላ የመጣ ለውጥ ነው።

እነዚህ የለውጡ መዋቅራዊ እና ውስጣዊ ክፍተቶች፣ አሃዳዊያኑ እና ሌሎች ለውጡን ለመቀልበስ የሚፈልጉ ቡድኖች በጎደለ እንዲሞሉ አድርጓል። ዛሬ ለተፈጠሩ ችግሮችም ሆኑ አገራዊ አደጋዎች፣ እነዚህ የለውጡ እጥረቶች ቁልፍ መሆናቸውን አምነን በመቀበል፣ ቀጣይ እርምት በማድረግ፣ ለመፍትሄው መታገል አለብን።

እዚህ ጋ መነሳት ያለበት ሌላው ነጥብ፣ ለውጡ የተንጠለጠለባቸው ኢህዴግ ውስጥ ያሉ ጥቂት ተራማጅ መሪዎችም ( progressive forces )፣ በፍጥነት ህዋሃት ራሱ ማስተካከል አቅቶት፣ጥሎት በሄደው የበሰበሰ የኢህዴግ አረንቋ ውስጥ መዘፈቃቸው ፣ እንዲሁም ሞግዚታቸው ህወሃት ዞር ስትል፣ በኦህዴድ እና በብአድን መካከል በአሃዳዊያኑ አጫፋርነት የተፈጠረው የስልጣን ሽሚያ እና ፍትጊያ፣ ለለውጡ የአሃዳዊያኑ መቀለጃ መሆን ትልቅ ድርሻ ተጫውቷል። የኢህዴግ ውስጣዊ ችግሮች ሳያንሱ፣ አድፍጠው ቀን ይጠብቁ የነበሩት በዘረኛ እና ሸፍጠኛ አሃዳዊያን እንደ ጥንብ አንሳ ከያሉበት ሁሉ ተሰብስበው በመልካቸው እና በአምሳላቸው በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን በተገነቡት አሃዳዊ፣ አግላይ፣ ዘረኛ እና assimilationist ኢትዮጵያ ተቋማት ( establishments) ላይ ሰፈሩ። አሃዳዊያኑ በኢትዮጵያ ተቋማት ውስጥ ያሉትን፣ በየትኛው መመዘኛ ለውጡን ያመጣውን የሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ ስነ ልቦናም ሆነ የጭቆና ሰቆቃ የማይጋሩትን፣ አማርኛ ተናጋሪዎችን ቅኝት እና ትርክት ብቻ ቀይረው እና ኦሮሞውን ተረኛ እና ዘረኛ እያሉ፣ የለመዱትን “የእምዬ ኢትዮጵያን ካሴት” ከተው፣ በጩኸት ተቀባይ ሚዲያዎቻቸው አጃቢነት፣ ሁሉንም የኢትዮጵያን ተቋማት እየተቆጣጠሩ ይገኛሉ።

የለውጡ ደጋፊዎች፣ መሪዎች እና ለውጥ ፈላጊዎች፣ ለውጡን በቀጣይነት ለመደገፍ እና ቀጣይ የትግል አቅጣጫዎችን ለመንደፍ፣ re-group፣ re-organize፣ እና re-charge አድርገው፣ ለውጡን ለማስቀጠል፣ እነዚህን የለውጡን ውስጣዊ ድክመቶች ( intrinsic and inbuilt weaknesses) እና መዋቅራዊ ድክመቶችን (structural wraknesses) አውቆ፣ማረም ያስፈልጋል ብቻ ሳይሆን ለውጡ ሙሉ ለሙሉ እንዳይቀለበስ እና ትግሉን፣ አሃዳዊያኑ እየተመኙ እንዳሉት ከዜሮ እንዳንጀምር፣ የግድ ይላል።

4፣ ለውጡ አሁን ያለበት የገመድ ጉተታ፣

ለውጡ አሁን ያለበትን ቦታ እና የኃይል አሰላለፉን ለመግለፅ ሶስት የእንግሊዘኛ ቃላትን ብጠቀም የበለጠ ገላጭ ነው ብዬ አስባለሁ።

እነርሱም፣ Inertia <===> Stability<====>change ናቸው። እነዚህ ቃላት፣ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሳሳቡ ያሉትን ሶስት ኃይሎች ያመለክታሉ።

1ኛ/ የለውጡ ወደ ኋላ ጎታች(Inertia) ቡድን፣

ይህ ቡድን፣ በኢትዮጵያ የፖላቲካ ኃይል አስላለፍ፣ ወደ ኋላ ጎታች ኃይሎችን ይወክላል። እነዚህ ኃይሎች ውስጥ የለውጡ ዋነኛ ጠላት የሆነው፣ ለውጡ ወደ ፊት ሳይሆን ወደ አፄ ኃይለስላሴ ዘመኗ ኢትዮጵያ እንድትመለስ የሚፈልገው ዘረኛ እና ሸፍጠኛ አሃዳዊ ቡድን ነው። ይህ ቡድን፣ በኢትዮጵያዊያን እኩልነት ፈፅሞ የማያምን፣ እጅግ አግላይ እና ዘረኛ ቡድን ነው። እነርሱ የሚፈልጉት የአንድ ቋንቋ፣ የአንድ ኃይማኖት፣ የአንድ ባህል ኢትዮጵያ ካልተፈጠረች፣ ኢትዮጵያ ብትፈራርስም፣ ህዝቦቿ ተባልቶው ብጨራረሱም፣ ለእነርሱ ሰርግ እና ምላሻቸው ነው። ይህ ቡድን የኢትዮጵያን ጭንብል ለብሶ የሚጓዝ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት እና እኩልነት ጠላት ነው። በኢትዮጵያ የተፈጠሩ የብሄር ፖላቲካን ( ህወሃት፣ ኦነግ፣ ሸኣቢያ፣ ኦብነግ ወዘተ) የወለደው እና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሱ ፍትሃዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዳያገኙ እያደረገ ያለው፣ ይህ ዘረኛ እና አግላይ ቡድን ነው። አሁን በኦሮሞ እና በተቀሩት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ላይ ዘረኛ እና አግላይ ፕሮፖጋንዳ በህዝብ ውስጥ እየዘራ የሚገኘው ይህ ቡድን ነው።

2ኛ) አረጋጊ እና አዘናጊ (የ”stability”) ቡድን፣

ይህ ቡድን አሃዳዊያኑ ከኋላ የሚዘውራቸው፣ የኢትዮጵያ መንግስት ተቋማትን የያዙ ምንም ሙያዊ ብቃት ያሌላቸው አደርባዮች እና ከለውጡ በኋላ በአፈ ጮሌነት የለውጡን ባቡር የተሳፈሩ ጩሉሌዎች ፣ ለውጥ ፈላጊዎች ሳይሆኑ የጥቅም አባራሪዎች፣ career builders፣ የስልጣን ፈላጊዎች እና የሆድ አደሮች ጥርቅም ቡድን ናቸው። የዚህ ቡድን አባላት እነርሱ እስከተጠቀሙ ድረስ፣ ነገሮች ባሉበት እንዲቀጥሉ ብቻ የሚፈልጉ ናቸው። በኢትዮጵያ እኩልነት እና ፍትህ እንዲሰፍን ቢፈልጉም፣ አይታገሉለትም። Status quo ( ባለህበት ሂድ) የሚመቻቸው የቀደሙት ስረዓቶች ተጠቃሚዎች እና በአብዛኛው ከከተማ upper and middle class የተወጣጡ ናቸው። በአስተሳሰብ ለአሃዳዊያኑ ይቀርባሉ። የአሃዳዊያኑ የልጅ ልጆችም ይበዙበታል። የኢትዮጵያ የፖላቲካ ችግሮች መዕከል ከሆኑት የኦሮሚያ፣ የሱማሌ፣ የደቡብ፣ የጋምቤላ፣ የአፋር፣ የትግራይ እና የጭቁኑ የአማራ ክልል ህዝቦች ወዘተ ስነልቦና እና ህመም ሩቅ ናቸው። ከአዲስ አበባ ዙሪያ ከተፈናቀለው የኦሮሞ ገበሬ እሮሮ ይልቅ ስለሶሪያ ስደተኞች ቢያወሩ ይቀላቸዋል። እነዚህ በኢትዮጵያ የቁርጥ እና የፈተና ቀን የሉም። በድሎት እና በደጉ ቀን ግን የነዚህን ያህል አጨብጫቢ እና አዘናጊ የለም። ላይ ላዩን የለውጡ ሚዛን አስጠባቂ ቢመስሉም፣ ከውስጥ ሆነው ለለውጡ ከድንጋይ በላይ የከበዱት እነዚህ ናቸው።

3ኛ/ የለውጥ (change) ቡድን፣

ይህ ለውጥ ፈላጊውን፣ ሰፊውን የኢትዮጵያን ህዝብ የሚወክል ቡድን ነው። ይህ የአሁኑንም፣ የ1966ቱንም ሆነ የ1983ቱን ለውጥ በኢትዮጵያ ያመጣ፣ ነገር ግን በተደራጁ ኃይሎች ለውጡ ተጠልፎበት፣ በኢትዮጵያ እኩልነት ላይ የተመሰረተ ስረዓት እንዲገነባ ማድረግ ያቃተው እና አሁንም በለውጥ መንፈስ ውስጥ ያለ፣ ሰፊውን የኢትዮጵያን ህዝብ የሚወክል ቡድን ነው። ይህ ቡድን ጭቁኑን የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግሬ፣ የሶማሌ፣ የሲዳማ፣ የአፋር፣ ወዘተ ያሉ ህዝቦችን ይወክላል። ያለፉት ስረዓቶች ጭቆና ሙሁራን እና ተቋማት አልባ ያደረጉት ህዝብ ነው። በጭቆናው እና በሰቆቃው ብዛት የነቃ ህዝብ ቢሆንም፣ የተደራጀ ግን አይደለም። የሚወክሉት ተቋማት የሉትም። የኢትዮጵያ ተቋማት የሚባሉት ሙሉ በሙሉ የአሃዳዊያኑ ጥቅም አስከባሪዎች እንጂ ለዚህ ጭቁን ህዝብ የቆሙ አይደሉም። ዘረኛቹ እና ሸፍጠኞቹም ራሳቸውን አማርኛ ተናጋሪ ተቋማት ውስጥ ደብቀው፣ ይህን ሰፊ ህዝብ የሚዳፈሩት እና የሚሳደቡት ይህ ህዝብ ስላልተደራጀ እና ተቋማት አልባ ስለሆነ ነው። የዚህ ለውጥም አንዱ እና ዋነኛ ግብ በአሃዳዊያኑ የተያዙትን እነዚህን የኢትዮጵያ ተቋማት የጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ተቋማት ማድረግ ነው። ይህን ለውጥ ፈላጊ ሰፊ ህዝብ አደራጅቶ የመራ፣ ኢትዮጵያን የሁሉም ህዝቧቿ የእኩል ለማድረግ የወሰነ መሪ፣ ኢትዮጵያን ወደ ገናናነት እና እድገት ይመራል። የለውጡ ኃይሎቹ ጉልበትም ሆነ የኢትዮጵያ ተስፋ ያለው እዚህ ቡድን ውስጥ ነው። እንደ ሙሴ ከአሃዳዊያኑ ቤት ሙታን ድግስ እና ማደግደግ፣ ከዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መከራን መቀበል ተስፋ እና ፍፃሜ አለው። ምክንያቱ፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህ እና ለርዕትህ(fairness) የሚታገል ህዝብ ሁሌ አሸናፉ ነው። ለለውጥ አመራሩም ሆነ ለሰፊው ለውጥ ፈላጊ ህዝብ የወንድ በር እና ድል ያለው እዚህ ነው። ከንኳኩት ወዲያው ይከፈታል።የኢትዮጵያም ሰላም፣ ተድላ እና ሃሴት ያለው በአሃዳዊያኑ የሞት ሰፈር ሳይሆን በዚህ ነው ። ለውጡም ይህን እውነታ ተጨባጭ ሃቅ ለማድረግ ነው።

ስለዚህ፣ ለውጡ ከወዴት ነው የወደቀው ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፣ የነዚህ ሶስት ኃይሎችን የኃይል አሰላለፍ መመልከት የግድ ይላል።

5፣ የአሃዳዊያኑ ለውጡን የመቀልበስ ስትራቴጂ

ለውጡን ለመቀልበስ፣አሃዳዊያኑ አምስት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ያነጣጠሩ ስትራቴጂዎችን እየተከተሉ ይገኛሉ።

እነርሱም ፣

1ኛ/ ኦሮሞን እርስ በርሱ በማጋደል ኦሮሞን የኢትዮጵያ ፖላቲካ ችግር ማንፃ የመስዋዕት በግ ማድረግ።

ይህ የአሃዳዊያኑ ስትራቴጂ ዘርፈ ብዙ ሲሆን ዋና ዓላማው ኦሮሞን በኦሮሞ አገዳድሎ፣ አሃዳዊያኑ ወደ ስልጣን የሚመጡበትን መንገድ ማመቻቸት ነው። ይህ በኦሮሞ ደም የስልጣን መንገዳቸውን የማንፃት መንገድ 1) በኦሮሞ ባለስልጣናት መካከል የስልጣን እና የገንዘብ ፉኩኩር ፈጥሮ በማባላት እና በመለያየት ተራ በተራ ሁሉንም አንድ በአንድ ማጥፋት፣ 2) የኦሮሞን ህዝብ በፖላቲካ፣ በሃይማኖት እና በአከባቢ ከፋፍሎ የአዛኝ ቅቤ አንጓች በመሆን የኦሮሞን ህዝብ አንድነት መበተን እና ማባላት፣ 3) በኦሮሞ የፖላቲካ ድርጅቶች መካከል በምርጫ ፖላቲካ አሳቦ አሃዳዊያኑ ባላቸው የሚዲያ እና ሌሎች ተቋማት ተጠቅሞ ጠላትነት በመፍጠር ድርጅቶቹን እርስ በርሳቸው ማባላት እና ማዳከም ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ይህን የኣሃዳዊያኑን ስትራቴጂ ለማክሸፍ 1) የኦሮሞ ባለስልጣነት፣ 2) የኦሮሞ ህዝብ እና 3ኛ) የኦሮሞ የፖላቲካ ድርጅቶች ከሞቱም የሚሞቱት፣ ከኖሩም የሚኖሩት፣ ለኦሮሞ ህዝብ ህልውና(survival) እንጂ ለአሃዳዊያኑ የስልጣን መንገድ ማንፃ የመስዋዕት በግ የሚሆን እንደም ኦሮሞ እንዳይኖር ግልፅ የፖሊሲ አቋም በአስቸኳይ መወሰድ አለባቸው። የኦሮሞ ህዝብ አብሮ የሚሞትለት የአገር ባለቤትነት ጥያቄ (cause) እንጂ፣ የሚገዳደልበት ስልጣን ወይም የግል ጥቅም የለውም። የኦሮሞ ህዝብ አገሩን ከአሃዳዊያኑ ዘረኞች ነጥቆ፣ የአገሩ ባለቤት ከሆነ ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበቃ ስፍራ አለ። ስለዚህ፣ የኦሮሞ የፖላቲካ ቡድኖች ካድሬ ቀጥረው ከመሰዳደብ ፣ ሙሁራን መልምለው ሃሳብ እና ለኦሮሞ ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም ፖሊሲ ወደ ማመንጨት መሸጋገር አለባቸው። በኦሮሞ መሪዎች ነዝላልነት፣ አሃዳዊያኑ በዚህ ዘረኝነታቸው እና ኦሮሞ ጠልነተቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በኦሮሚያ ጄኖሳይድ ይሆናል። ይህ በፍፁም መፈቀድ የለበትም።

2ኛ/ ሁለተኛው የአሃዳዊያኑ ስትራቴጂ ኦሮሞን ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ነጥሎ ለብቻ ማጥቃት፣

ይህ ስትራቴጂ የተቀዳው ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ነው። በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአሜርካ ትኩረት በሶቬት ህብረት ላይ ማነጣጠር ነበር። ዓላማውም ትልቋ ሶቬት ህብረት ከተመታች ሁሉም ተከታዮቿ ይመታሉ የሚል ነው። የሆነውም እንደዛው ነው።

አሁንም አሃዳዊያኑ በኢትዮጵያ የማንነት ፖላቲካ ጥያቄ አቀንቃኞችን ለመምታት፣ የትልቁን የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከመታን ፣ የትግሬውን፣ የሱማሌውን፣ የአፋሩን፣ የሲዳማውን፣ የወላይታውን፣ የጋምቤላው እና የሌሎች ብሄር ብሄረሰብ የእኩልነት ትግሎች በቀላሉ ነጣጥለን እንመታለን የሚል ስትራቴጂ ነው።

ይህን የአሃዳዊያኑን የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችን የእኩልነት ጥያቄዎችን ነጣጥሎ የመምታት ስትራቴጂ፣ የኦሮሞ ህዝብ ሁሉንም በኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት የሚያምኑ ኃይሎች ጋር ትግሉን አቀናጂቶ እና አደራጅቶ፣ የአሃዳዊያኑን ስትራቴጂ ማፍረስ አለበት።

3ኛ/ ሶስተኛው የኣሃዳዊያኑ ስትራቴጂ ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ እና የኦሮሞ ብሄርተኛ(ዘረኛ) ብሎ ኦሮሞን መከፋፈል ነው።

ይህን ስትራቴጂ አሃዳዊያኑ ለብዙ ዘመን ተጠቅመውበታል። ለምሳሌ፣ በትግሉ ወቅት የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ በኢትዮጵያ መዕቀፍ ይፈታል ብለን ስንታገል የነበርነውን ኦሮሞዎች፣ ሸፍጠኞቹ አሃዳዊያኑ በዓላማችን አምነው ሳይሆን ምናልባት ኦሮሞን ይከፋፍላል፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን ያዳክማል፣ ወዘተ ብለው እኛን ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ እያሉ ታቲካሊ ይደግፉን ነበር። ትግላችን ሰምሮ፣ የእና ዶ/ር አብይ እና የአቶ ለማ ቡድን ጥረት ታክሎበት፣ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ወደ ኢትዮጵያ መሃል ፖላቲካ ከመጣ በኋላ ግን፣ በአንድ ጀንበር እኛ ሁላችን (ኦህዲዶችን ጨምሮ) ፣ በሸፍጠኞቹ እና በዘረኞቹ አሃዳዊያን ትርክት ራሳችንን ኦነግ ሆነን አገኘነው። አሃዳዊያኑ አሁንም ይችን የተበላች እቁብ ደጋግመው ይጠቀማሉ። ለአሃዳዊያኑ ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር የቆመ ሁሉ ኦነግ ነው። ስለዚህ ሁሉም ኦሮሞ ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር፣ በአንድነት በመቆም “ኦነግ” ሆኖ የአሃዳዊያኑን የኦሮሞ ህዝብን የመከፋፈሉን ሴራ ማክሸፍ አለበት። ለኦሮሞ ህዝብ ኃይሉ፣ አንድነቱ ብቻ ነው።

4ኛ/ ኦሮሞ ለኢትዮጵያ መጤ(Immigrant) እንጂ ባለ አገር አይደልም።

በአሃዳዊያኑ ፀረ ኦሮሞ ዘረኛ እና አግላይ ትርክት ኦሮሞ ለኢትዮጵያ መጤ እና ከአራት መቶ አመት በፊት በኢትዮጵያ የተከሰተ ስደተኛ ህዝብ ነው። አሃዳዎያኑ ከ80 በላይ ከሚሆኑ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ውስጥ ለኢትዮጵያ መጤ እና ወራሪ ህዝብ ብለው የሚጠሩት ከኦሮሞ ህዝብ ውጭ አንድም ህዝብ የለም። ከኦሮሞ ህዝብ በስተቀር፣ በአሃዳዊያኑ ዘረኞች ትርክት፣ አማራው፣ ትግሬው፣ አገዋዎው፣ ሲዳማው፣ ሱማሌው፣ አፋሩ፣ ጋምቤላው፣ ወላይታው፣ ጉራጌውን፣ ወዘተ ጨምሮ አንድም በኢትዮጵያ ካሉ ብሄር፣ ብሄረሰቦች ውስጥ ለኢትዮጵያ እንግዳ፣ መጤ፣ እና በራሱ አገር እንደ ስደተኛ የሚታይ ህዝብ የለም። አሃዳዊያኑ፣ ኦሮሞው፣ ከውሃ ውስጥ የፈለቀ፣ ወይም ከማዳገስጋር የመጣ፣ ስደተኛ እና አገር አልባ ህዝብ ነው የሚል ትርክት ያራምዳሉ። የኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚደረገው የመሬት ወረራ ምንጩም፣ ከወራሪው ኦሮሞ፣ መሬታችንን መልሰን እንውሰድ በሚል ጄኖሳይዳል አጀንዳ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ነው። ኦሮሞ ዘረኛ እና ተረኛ ነው የሚለው ትርክታቸው ምንጩ ይኸው ነው። ይህ የአሃዳዊያኑ ትርክት እና ተቋማቶቻቸው በፅኑ የሚያምኑበት እጅግ ዘረኛ አስተሳሰብ መፍረስ ብቻ ሳይሆን በህግ መከልከል አለበት። የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ባለአገር እንጂ ተረኛ ያለመሆኑን ለማረጋገጥ፣ የአሃዳዊያኑን ዘረኛ እና አግላይ ስረዓተ መንግስት አፍርሶ፣ በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ እና ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የእኩል የሆነች አገር ለመፍጠር ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል አለበት።

5ኛ/ አሃዳዊያኑ ጋ እረኝነት በሚገቡ ኦሮሞዎች፣ ኦሮሞን ማሰደብ፣

ይህ ስትራቴጂ ቅጥረኛ ተዋጊዎች እንደመቅጠር ነው። በዚህ ስልት አሃዳዊያኑ የኦሮሞ ስም ያላቸውን ወይም ኦሮሞ ነን የሚሉ ግለሰቦችን ቀጥረው፣ ቀለብ እሰፈሩ ኦሮሞን ያሰድባሉ። አሃዳዊያኑ ሚዲያ እየሰጧቸው እና መድረክ እያመቻቹላቸው ያጨበጭቡላቸዋል። ድርጅት ብጤ ተላላኪዎችንም ህወሃት ኦህዲድን እንደፈጠረ ልፈጥሩ ይችላሉ። ይህን ርካሽ ተግባራቸውን ለማክሸፍ የኦሮሞ ህዝብ ተደራጅቶ የራሱን መያዝ ብቻ በቂ ነው።

ቀጥለን ወደ ምርጫ ፖላቲካ እንመለሳለን።

6፣ የኢትዮጵያ የምርጫ ፖለቲካ፣

በኢትዮጵያ ታርክ፣ ምርጫ ህዝብ ማደንዘዣ እና status quo(ያለውን ስረዓት) ማስቀጠያ እንጂ ለአገር ችግር መድሃኒት ሆኖ አያውቁም። አሁንም ኢትዮጵያ በምርጫ ፖላቲካ የሚፈታ ችግርም ሆነ ምርጫ ለማካሄድ የተሟላ objective እና subjective conditions የላትም።

በኢትዮጵያ ታርክ ህገ መንግስት እና ምርጫ ለገዥዎች ህዝብ መደለያ መሳሪያነት ወይም በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ ተቀዋሚዎች የምርጫ ወቅት ጠብቀው ህዝብ ማታገያ መሳሪያ አድርገው ከሚጠቀሙበት መለስተኛ ጫጫታ ውጭ፣ ምርጫ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ሃገረ መንግስታዊ ችግሮች ላይ ሌላ ተጨማሪ ችግሮችን ከመፍጠር ውጭ ለአገር እና ለህዝብ ችግሮች መፍትሄ ሆኖ አያውቅም።

ለምሳሌ፣ በየዘመኑ የነበሩትን የኢትዮጵያ የምርጫ ፖላቲካ ቁማሮች አንድ በአንድ እንመልከት፣

የአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ሁለት ህገ መንግስቶች እና በነዚያ ህገ መንግስቶች ስር የተደረጉት በርካታ ምርጫዎች፣ የጭሰኛውን ስረዓት በሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በመጫን፣ የመሬት ከበርቴውን መብት እና ጥቅሞች ከማስከበር ውጭ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንዳች ፋይዳ አልነበራቸውም።

በዚሁ መሰረት፣ ከ50 ዓመታት በላይ የቆየው የአፄው ስረዓት ተገረስሶ መሬት ላራሹ የታወጀው በምርጫ እና በህገ መንግስታዊ ሂደት ሳይሆን ገንፍሎ በወጣው የ1966ቱ አብዮት ነው።

የአፄ ኃይለስላሴ መንግስትን የተካው የደርግ ህገ መንግስትም እንደዚሁ የራሱን ህገ መንግስት ቀርፆ፣ የኢሠፓ ሰዎች የሚመራረጡበት የህዝብ መደለያ ምርጫ አድርጓል። ነገር ግን ደርግ የወደቀው በትጥቅ ትግል እንጂ፣ በምርጫ እና በህገ መንግስታዊ ሂደት አልነበረም።

ደርግን የተካው ህወሃት መራሹ መንግስትም የራሱን ህገ መንግስት ቀርፆ የመደለያ ምርጫዎችን ቢያደርግም፣ በስልጣን ላይ የቆየው በጉልበት እንጂ በምርጫ እና በህገ መንግስታዊ ሂደት አልነበረም።

ህወሃት መራሹም መንግስትም ልክ እንደ አፄው እና ደርግ መንግስት ከስልጣን የውረደው በምርጫ እና ህገ መነግስታዊ ሂደት ሳይሆን፣ በኦሮሞ ህዝብ ግንባር ቀደም መሪነት የኢትዮጵያ ህዝብ ከ2014 እስከ 2018 በደረገው ተከታታይ ደም አፋሳሽ ሰላማዊ የህዝብ ትግል ነው።

ትልቁ ጥያቄ፣ አሁንስ ኢትዮጵያ ከዚህ ከአንድ ክፍለ ዘመን የዘለለ ዓዙሪት ለመውጣ ደርሳለች ወይ ነው? አጭሩ መልስ አሁንም፣ “ኢትዮጵያ ለመርጫም ሆነ ለህገ መንግስታዊነት የተጣለ መሠረት የላትም።” ባሌለ መሠረት ላይ ደግሞ ቤት አይሰራም። ኢትዮጵያ ገና የእኩልነት፣ የፍትህ እና የርዕትህ አገር አይደለችም። ለመሆንም መሠረቱን አልጣለችም።

7፣ የምርጫ ፖለቲካ ውስጥ ለመግባት መሟላት የሚገባቸው Objective and Subjective Conditions

ቀጣዩ ትልቅ ጥያቄም ” እንዴት ምርጫ እናድርግ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ለሁሉም እኩል የሆነ አገረ መንግስታዊ መሰረት እንጣል ነው?”

በሌላ አገላለፅ፣

1ኛ) በኢትዮጵያ የተለያዩ የፖላቲካ አመለካከት ያላቸው የፖላቲካ ቡዱኖች ተፈራርቀውበት እንደ አገር የሚያስተዳድሩበት፣ ሁሉም ራሱን በውስጡ የሚያይበት፣ ለሁሉም እኩል የሆኑ የመንግስት ተቋማት እንዴት እንፍጠር?አሁን ያሉት የኢትዮጵያ መንግስት ተቋማት አማርኛ ብቻ የሚናገሩ ከአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ የተወረሱ እና በደርግ እና በህወሃት( ከክልል መስተዳድሮች በስተቀር) ያልተነኩ አሃዳዊ እና assimilationist ተቋማት ስለሆኑ፣ እንዴት እንቀይራቸው? እነዚህ ዘረኛ እና አግላይ ተቋማት ከአማርኛ ተናጋሪ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ተቋምም እንዲሆኑ ከምርጫው በፊት ፈርሰው፣ የስራ ቋንቋቸው ተስተካክሎ፣ እንደገና እንዴት ይዋቀሩ? በአጭሩ፣ ይህ ሳይደረግ ምርጫ ከተደረገ አማርኛ ተናጋሪዎች የሚመራረጡበት እንጂ አማርኛ መናገር የማይችለው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሳተፍበት ምርጫ በኢትዮጵያ ማካሄድ አይችልም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ለምርጫ የሚሆን ተቋማዊ ሁኔታ የላትም።

2ኛ) በተራ ቁጥር አንድ ስር የሚደረገው የተቋማት ለውጥ ለማካሄድ፣ ከምርጫው በፊት ችግሩ አገራዊ እውቅና አግኝቶ፣ በኢትዮጵያ እንደ አዲስ የሚዋቀር ሀገረ መንግስታዊ ተቋማት፣ ተቋማቱ የሚጠቀሙበት ቋንቋዎች እና ስብጥር ላይ ስምምነት ሲደረግ ብቻ ነው። ከምርጫው በፊት፣ ኢትዮጵያ አሁን ከምትከተለው ኢትዮጵያን የአንድ ቋንቋ(nation state) አገር የማድረግ አጀንዳ ሙሉ በሙሉ ተወጥታ፣ ኢትዮጵያ የብዙ ቋንቋዎች አገር( State nations or multinational state) መሆኗ ላይ በግልፅ የፖላቲካ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት። አሁን ያ ስምምነት የለም። ኢትዮጵያ በተግባር የአማርኛ ብቻ ተናጋሪዎች አገር ነች። ይህ መለወጥ አለበት። ይህም ለውጥ በምርጫ አይመጣም።

3ኛ) ኢትዮጵያ የእኩልነት ( equality) ፣ የፍትህ (justice ) እና የርዕትህ (equity) አገር ለማድረግ ከውሳኔ መደረስ አለበት። አሁን ባለበት ሁኔታ ፣ እነዚህን የኢትዮጵያን ተቋማት ይዞ ያለው እና በፍጥነት እያንሰራራ ያለው ዘረኛ እና አግላይ አሃዳዊ ቡድን በኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦች ቋንቋ፣ ታርክ፣ ባህል፣ ማንነት እና እኩልነት አያምንም። ዘረኛው እና አግላዩ ቡድን የ1966ቱ አብዮት፣ የ1983ቱ እና የ2018ቱ ለውጦች ከሽፈዋል ብሎ ስለሚያምን፣ ቡድኑ፣ የለውጥ ኃይሎች በሚመሩት የአገር ግንባታ ፕሮጄክት ተነቅሎ ካልፈረሰ፣ ወይም ሌላ ዙር ስርነቀል አብዮት ወይም በጦርነት ከልተሸነፈ በስተቀር፣ በኢትዮጵያ እኩልነት ፣ ፍትህ እና ሪዕትህ (equity) በፍፁም እንዲመጣ አይፈልግም። ከቻለ፣ አይፈቅድም። ከምርጫ እና ህገ መንግስታዊነት በፊት፣ ኢትዮጵያን የሁሉም የኢትዮጵያዊያን የእኩል አገር ለማድረግ ይህ አገርቷን አንቆ የያዘው ኃይል መሸነፍ አለበት።

8፣ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ህዝብ የትግል አቅጣጫ ምን መሆን አለበት?

የኢትዮጵያ የለውጥ ኃይሎች(መንግስት ውስጥ ያሉትም ሆኑ በውጭ ያሉት) የታገሉት እና ብዙ ሽህ የህዝብ ልጆች የተቀጠፉት፣ ስር ነቀል ሥረዓታዊ ለውጥ በኢትዮጵያ በማምጣት፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ የእኩልነት፣ የፍትህ እና የርዕትህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንጂ ፣ ግለሰቦችነ ወይም ቡድኖችን ወደ ስልጣን ለማምጣት እንዳልሆነ ይታወቃል። ስለዚህ የለውጥ ሃይሎቹ የነበረውን እና ያለውን ስረዓት በሚያስቀጥሉ (status quo ማስቀጠያ) ተልካሻ የተለመዱ ጉልቻ መቀያየሪያ የምርጫ ቁማሮች ከመጫወት፣ በፍጥነት ወጥተው፣ ስርነቀል ለውጥ በኢትዮጵያ ለማምጣት እንደ ገና ራሳቸውን አሰባስበው ፣ አደራጅተው እና ዘላቂ ህዝባዊ እና አገራዊ ራዕይ ሰንቀው ወደ ፊት መጓዝ መጀመር አላባቸው።

የኢትዮጵያ የለውጥ ኃይሎች፣ ኢትዮጵያ መሸከም የማትችለውን ነገ የሚመጣውን ስር ነቀል አብዮት ወይም የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቀረት፣ ከተራ የምርጫ ሰጣ ገባ ወጥተው፣ ቢያንስ ሰማንያ ከመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ተቋማት ያገለለው አግላይ ስረዓት ፈርሶ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የፍትህ፣ የእኩልነት እና የርዕትህ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ፣ ሰላማዊ እና ሥር ነቀል ስረዓታዊ ለውጥ ወደ ማድረግ መሄድ አማራጭ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ግድ ከሚላቸው አካላት ሁሉ የሚጠበቅ አገራዊ ግዴታ ነው።

ስለዚህ ከዚህ በኋላ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ዘረኛውን እና አግላዩን አሃዳዊ ቡድን አሸንፎ፣ ኢትዮጵያን የእኩልነት፣ የፍትህ እና ርዕትህ አገር እንድትሆን ማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ እነዚህን፣ ፀረ አንድነት እና ፀረ እኩልነት ኃይሎች ለማሸነፍ ሶስት አማራጮች አሉት። እነርሱም፣

1ኛ/ በለውጥ ኃይሎች በሚመራ ሁሉን አቀፍ እና አገራዊ ስምምነት ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ የአገር ግንባታ(nation building) ሂደት ውስጥ አገርቷን በማስገባት፣ አሃዳዊ፣ ዘረኛ እና አግላይ የሆኑትን የኢትዮጵያን ተቋማት፣ አፍርሶ እንደገና በእኩልነት ፣ በፍትህ እና በርዕትህ መሠረቶች ላይ መገንባት። ለነዚህ ተቋማት ህገ መንግስታዊ ጥበቃ መስጠት። ከዚያ በኋላ ምርጫ ማካሄድ።

2ኛ/ የዘርኞቹ እና አግላዮቹ ኃይል አይሎ፣ የለውጥ ኃይሉ ኢትዮጵያን የእኩልነት ፣ የፍትህ እና የርዕትህ አገር ማድረግ ካልቻለ፣ በስርነቀል ህዝባዊ አብዮት የዘረኛውን እና የአግላዩን ቡድን መሠረቶች ሙሉ በሙሉ ለመናድ ቀጣይ የትግል ስልቶች መሰነቅ እና ስርነቀል ለውጥ ማድረግ ።

3ኛ) ሶስተኛው አማራጭ ወደ ነፃ አውጭው ዘመን ትግል መመለስ ነው። ነገር ግን፣ በኢትዮጵያ ያሉት የለውጥ ኃይሎች ከተባበሩ (መተባበርም አለባቸው)፣ አልቃሽ እና ዘፋኝ እያደራጀ፣ በጩኸት አገር እያመሰ ላለው ጥርስ አልባ ዘረኛ እና አግላይ ቡድን ተብሎ፣ ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ዳግም ትገባለች የሚል ግምት የለኝም።

9፣ ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ የለውጥ ኃይሎች እና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፣ ለቡድኖች ወይም ግለሰቦች ስልጣን መሿከት ከሚመስል ተራ የምርጫ ሰጣ ገባ ወጥተው፣ 1ኛ/ ኃይላቸውን አሰባስበው፣ 2ኛ/ በአዲስ መልክ ራሳቸውን አደራጅተው፣ እና 3ኛ) ስር ነቀል ስረዓታዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የሚያመጣ ህዝባዊ ራዕይ ሰንቀው፣ በኢትዮጵያ የተነሱ የህዝብ የእኩልነት ( equality) ፣ የፍትህ (justice ) እና የርዕትህ (equity) ጥያቄዎች በስር ነቀል ለውጥ ለመመለስ ወደ ቀጣዩ የትግል ምዕራፍ መሸጋገር አለባቸው። የኢትዮጵያ ዘላቂ ፈውስ፣ አገራዊ እና ህዝባዊ ስር ነቀል ስረዓተ መንግስታዊ ለውጥ በማምጣት ውስጥ እንጂ፣ በምርጫ ውስጥ የለም። የህዝባችን ለቅሶ እና ሰቆቃም፣ ነገ ሳይሆን ዛሬ መቆ አለበት። በኢትዮጵያ ህዝብ የተባበረ ክንድ የመጣው ለውጥ በዘረኛ እና ሽፍጠኛ አሃዳዊያን አይቀለበስም። ትግሉ ይቀጥላል። ለእኩልነት፣ ለፍትህ፣ እና ለርዕትህ የሚታል ህዝብ ሁሌም፣ የትም፣ አሸናፊ ነው። እንደምናሸንፍም አንጠራጠርም።

ማሳሰቢያ፣
በዚህ ፁሁፍ ስር በዘረኞቹ እና በሸፍጠኞቹ አሃዳዊያን የተደራጁ አልቃሽ እና ዘፋኝ የጩኸት ቡድኖች( አንዳንዶች #ዲጂታል_ነፍጠኞች ይሏቸዋል) በሚተፏቸው ዘረኛ መርዞች እና ቃላቶች ህልናችሁ እንዳይበከል ጥንቃቄ አድርጉ።

Via: Dábessá Gemelal


ሜሮን ሞገስ – ኢትዮጵያዊቷ የCNN ዜና አዘጋጅ – አርትስ ወግ (Meron Moges Garby) but they did not put Garby why???may be she is an oromo?