የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የአባ ገዳዎች ህብረት አስታወቀ

የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የአባ ገዳዎች ህብረት አስታወቀ

የኢሬቻ በዓልን

(fanabc) — አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዘንድሮን የኢሬቻ በዓል ለማክበር አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የአባ ገዳዎች ህብረት አስታወቀ።

የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ከኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን በበዓሉ አከባበር ዙሪያ በትናትናው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም መስከረም 21 ቀን 2010 የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለማክበር አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ነው ያሉት።

የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል አከባበር የሚያስተባብሩ 300 ወጣቶች መመረጣቸውንም የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት አስታውቋል።

በበዓሉ ላይም የጦር መሳሪያ የታጠቀ ፖሊስ እንደማይገኝ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ማረጋገጡን የአባ ገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ እና የቱለማ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ተናግረዋል።

የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ስፍራ ላይም ሀገሪቱን የሚያስተዳድረውን ፓርቲ ጨምሮ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሰንደቅ ዓላማ እንዳይውለበለብ መወሰኑንም አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፥ ስፍራው የፖለቲካ መድረክ ከመምሰል በፀዳ መልኩ የኦሮሞ ባህልን በማንፀባረቅ የሚከበር ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስም ያለ ምንም ትጥቅ ከዳር በመሆን በዓሉን ለማክበር ከመጡት ጋር ተቀላቅለው ጥፋት ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ አካላትን የመከላከል ስራ ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል።

በበዓሉ ላይ የሚሳተፉ ሰዎችን የመፈተሽ ስራ የሚሰሩትም በአባ ገዳዎች የተመረጡት 300 ወጣቶች መሆናቸውንም ወይዘሮ ሎሚ ተናግረዋል።

በ2009 ዓ.ም በኢሬቻ በዓል ላይ ህይወታቸው ላለፉ ሰዎች በቆመው የመታሰቢያ ሀውልት ላይ ከተፃፈው ጽሁፍ ጋር ተያይዞ ቅሬታ በመቅረቡ ጽሁፉ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ መወሰኑንም አስታውቀዋል።