የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ግምገማ አዘል ሥልጠና ገብተዋል

የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ግምገማ አዘል ሥልጠና ገብተዋል

(Ethiopian Reporter) — የኢሕአዴግ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ከአንድ ወር በላይ የሚፈጅ ግምገማ አዘል ሥልጠና መግባታቸው ታወቀ፡፡ ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሚኒስትሮች ጀምሮ በከፍተኛ የመንግሥት የሥልጣን እርከን ላይ የሚገኙ ባለሥልጣናት ይህንን ግምገማ አዘል ሥልጠና እየተካፈሉ ነው፡፡

ከፍተኛ አመራሮቹ እንደዚህ ዓይነት ሰፊ ሥልጠና ከወሰዱ ከአራት ዓመታት በላይ መሆናቸውን የገለጹት ምንጮች፣ ይህ ሥልጠና ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ጠንካራና ጤናማ የሆነ አቋም እንዲኖረው የአመራሮቹን አቋም ለመገንባት ታልሞ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ለከፍተኛ አመራሮቹ ሥልጠናውን እየሰጡ ከሚገኙት መካከል የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ በረከት ስምኦን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን፣ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃንና ሌሎች የቀድሞው የኢሕአዴግ አመራሮች ይጠቀሳሉ፡፡

በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ እየተሰጠ ባለው ሥልጠና ላይ ተሳታፊዎቹ በግልጽ አስተያየት የሚሰጡበትና እርስ በርሳቸው ግምገማ የሚያደርጉበት መሆኑም ታውቋል፡፡ በመሆኑም የሥነ ምግባርና የአመለካከት ችግሮች ያሉባቸው ባለሥልጣናት እንደሚገመገሙ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ አመራሮቹ ብዙኃኑን ሕዝብ እንዴት ማገልገል እንዳለባቸውና የአመራር ብቃታቸው ሊጎለብትበት የሚችልበትን መንገድ እየሠለጠኑም ይገኛሉ፡፡ በሥልጠናው ፌዴራሊዝም፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግሥት የሚሉት ነጥቦች እየተዳሰሱ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና አምባሳደሮች እየተሳተፉበት ያለው ይህ ግምገማ አዘል ሥልጠና ሦስተኛ ዙር የሆነው ሲሆን፣ ከ1,500 በላይ ተሳታፊዎችንም ማካተቱ ተገልጿል፡፡ ይህ ሥልጠና ወደ አራተኛ ዙር ሊዘልቅ እንደሚችልም ለማወቅ ተችሏል፡፡

መካከለኛና ዝቅተኛ የኢሕአዴግ አመራሮችም በየክልሉ ተመሳሳይ ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ዘካርያስ ስንታየሁ