የኢሕአዴግ ምክር ቤት የፓርቲዎቹን ውህደት አፀደቀ::

የኢሕአዴግ ምክር ቤት የፓርቲዎቹን ውህደት አፀደቀ
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር /ኢሕአዴግ/ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የመራለትን የፓርቲውን ውህድ በሙሉ ድምጽ አፀደቀ፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ ምክር ቤቱ በውህደት ሂደቱ ወቅት የተወያየባቸውን ዋና ጉዳዮች ዘርዝረዋል።

የኢሕአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ውህደቱን በተመለከተ ያስቀመጣቸው ሦስት አቅጣጫዎች ውስጥ አንደኛው የውህደቱ ጥናት ሳይንሳዊ በሆነ ተጠናቅቆ ወደ ውይይት እንዲሄድ ነበር።

ሁለተኛ ውህደቱ ለኢሕአዴግ ምክር ቤት ሙሉ ውክልና እንዲሰጥ ሲሆን ሦሰተኛ የአጋር ድርጅቶች አመራሮች እስከ ውህደቱ ድረስ በኢሕአዴግ ምክር ቤት እንዲሳተፉ እና ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ውህዱ ፓርቲ እንዲቀላቀሉ የሚል ነው።

ዛሬ በተካሄደ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ምልዓተ ጉባዔ ተማልቶ ከመከረ በኋላ የውህደቱን አስፈላጊነት በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

የኢሕአዴግ ኦዲት እና ቁጥጥር ኮሚሽን ውህደቱ ላይ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ኢሕአዴግ አሁን ባለው ቁመና ሀገራዊ ለውጡን ለመምራት እና መሠረት ለማስያዝ አንዲሁም የሕዝቦችን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ ውህደቱ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል።

ውህደቱ ሕገ-ደንብ እና ሥርዓቱን የተከተለ ከመሆኑ አንፃርም ሲታይ በትክክል ሂደቱን የተከተለ መሆኑንም ጥናቱ አሳይቷል።

የአዲሱ የብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራም አራት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። አነዚህም ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ውጭ ጉዳይ ግንኙነት ናቸው። ውህደቱ እስካሁን በእነዚህ ዘርፎች እስካሁን የተመዘገቡ ድሎችን የሚያሰፋ ነው። በሌላ በኩል ሀገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚሄድ ነው ብለዋል።

ኢሕአዴግ ከዚህ በፊት ይቅርታ የጠየቀባቸውን ጥፋቶችንም ለማስተካከል የሚሠራ ነው። ለዛሬው እና ለወደፊቱ ትውልድም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ከማረጋገጥ አንፃር መሠረታዊ ይዘት ያለው እንደሆነም ነው አቶ ፍቃዱ ያስታወቁት።

አፅንኦት ተሰጥቷቸው የድምዳሜ ሀሳብ የተሰጣቸው ጉዳዮችም በፖለቲካ ፕሮግራሙ ኅብረ-ብሔራዊ እና ሕገ-መንግሥታዊ እና ዴሞክራሲያዊ የፌዴራል ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ እና የብሔር ብዘሃነት፣ ሀገራዊ አንድነት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የግለሰብ እና የቡድን መብት እኩል እውቅና ተሰጥቷቸዋል፤ እነዚህን መብቶች በማስታረቅ እና በማጣጣም ተግባራዊ መደረግ አለባቸው በሚል በፅኑ ታይተዋል።

ከሀገራዊ አንድነት እና ከብሔር ማንነት ጋር ተያይዘው ያሉትን ዋልታ-ረገጥ አመለካከቶች ለማስታረቅም ሁሉንም አብሮ መካከለኛውን መንገድ ይዞ መሄድ ለሀገራችን ብቸኛው መፍትሔ መሆኑ ታምኖበታል።

ግራ ዘመምም ሆነ ቀኝ ዘመም ከሆኑ የፖለቲካ አቋሞች መሃሉን በመያዝ፣ የኢትዮጵያን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ እና የሕዝቦቿን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ የመሄድ አስፈላጊነት ተሰምሮበታል።

ውህዱ ፓርቲ ከዚህ ቀደም ያሉትን በጎ ነገሮች ማስቀጠል እና ስህተቶችን ማረም እና ለዛሬ እና ለነገው ትውልድ የሚሆን ሁለንትናዊ ብልፅግና በማኅበራዊ፣ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ለማረጋገጥ ይታገላል።

በአጠቃላይ በዛሬው ውሎ ውህደቱ እና የአዲሱ ፓርቲ ፕሮግራም አጀንዳዎች በሙሉ ድምፅ ፀድቀዋል።

በነገው ውሎ በአዲሱ የብልፅግና ፓርቲ ረቀቅ ሕገ-ደንብ ላይ ላይ ውይይት ይደረጋል፤ የሚሻሻሉ ነገሮች ካሉ ተሻሽለው ሕገ-ደንቡ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ውይይቱ ዴሞክራሲያዊ እና ነፃ ሀሳቦች የተንፀባረቁበት እንደነበረም ነው አቶ ፈቃዱ የተናገሩት።

በዮናስ በድሉ


#etv በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተፈጠሩ ግጭቶች የህዝቦች የዘመናት የአብሮነት ታሪክ መገለጫ እንደማይሆኑ ተገለፀ፡፡

#etv ኢቲቪ 57 ምሽት 1 ሰዓት አማርኛ ዜና…ህዳር 11/2012 ዓ.ም