ሜድሮክ ፒያሳ አካባቢ ያጠረውን ጨምሮ ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችን አጥር የማፍረስ ስራ ተጀመረ

ሜድሮክ ፒያሳ አካባቢ ያጠረውን ጨምሮ ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችን አጥር የማፍረስ ስራ ተጀመረ

(FBC ) —አዲስ አበባ ፣ ህዳር 12 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሜድሮክ ፒያሳ አካባቢ አጥሮ ያስቀመጠውን ቦታ ጨምሮ በመዲናዋ ለዓመታት ያለስራ ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችን አጥር የማፍረስ ስራ ጀመረ።

ሜድሮክ ለገበያ ማዕከል በሚል ከ20 አመታት በላይ አጥሮ ያስቀመጠውና ፒያሳ የሚገኘው ቦታ የከተማ አስተዳደሩ የደንብ ማስከበር ሰራተኞች፣ አመራሮች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በዛሬው እለት መፍረስ ጀምሯል።

አስተዳደሩ ከሜድሮክ በተጨማሪም በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች በልማት ስም መሬት ከወሰዱ በኋላ ልማት ሳይካሄድባቸው፥ ሳያለሙ ለበርካታ ዓመታት ታጥረው የተቀመጡ መሬቶች ላይ ያሉ አጥሮችን እንደሚያፈርስ ገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት ለረጅም ጊዜ ታጥረው ባልለሙ ቦታዎች ላይ ንብረቶቻቸውን ያስቀመጡ አካላት ንብረታቸውን እንዲያነሱ ከሳምንት በፊት መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል።

ይሁን እንጅ እነዚህ አካላት ንብረቶቻቸውን ማንሳት ባለመጀመራቸው ምክንያት አስተዳደሩ ወደ እርምጃ ገብቷል።

አስተዳደሩ የህዝብን ሃብት ለተገቢው ልማትና ለነዋሪዎች ተጠቃሚነት እንዲውል በጀመረው ተግባር ህገ ወጥነትን እንደማይታገስና፥ ህግ የማስከበር ሃላፊነቱን እንደሚወጣም አስታውቋል።