የአርሲ አዳማ መንገድ ተደርምሶ የትራፊክ ፍሰቱን ማስተጓጎሉ ተገለጸ

የአርሲ አዳማ መንገድ ተደርምሶ የትራፊክ ፍሰቱን ማስተጓጎሉ ተገለጸ

ግንቦት 06፣2009

በአርሲ ዞን ዴራ እና ኢተያ ከተሞች መካከል በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የተደረመሰው መንገድ የትራፊክ ፍሰቱን ማስተጓገሉ የአርሲ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

(EBC) -መንገዱ ከፍተኛ ትራፊክ ያለበትና ወደ አዳማ ለመጓዝ ብቸኛ መንገድ መሆኑ ችግሩን እንዳባባሰው የጽሕፈቱ ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ከድር ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡

ወደ አደማ ለመሄድ ተለዋጭ መንገድ ባለመኖሩ መኪናዎች ስጋት ባለው መንገድ ጎን ስለሚጓዙ መንገዱ መጨናነቁን ገልጸው ከፍተኛ ጎርፍ ባለበት ወቅት የትራፊክ ፍሰቱ ለሰዓታት እንደሚቋረጥም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን የተሰራው የጎርፍ መቀልበሻ ጎርፉን መቋቋም ባለመቻሉ መንገዱ መደርመሱንም  አቶ መሀመድ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የተደረመሰውን መንገድ በአስቸኳይ ለመጠገን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጿል፡፡

የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለኢቢሲ እንደገለፁት ላጋጠመው ችግር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የጥገና ቡድን ወደ ስፍራው ማምራቱን ተናግረዋል።

ችግሩንም ዘላቂ በመሆነ መንገድ ለመፍታት ተጨማሪ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡

በአብዱልአዚዝ ዩሱፍ