የትግራይ ኃይሎች በጥብቅ ቅድመ ሁኔታዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጀውን የተኩስ አቁም እንደሚቀበሉ ተናንት አስታዉቀዋል።

የትግራይ ኃይሎች በጥብቅ ቅድመ ሁኔታዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጀውን የተኩስ አቁም እንደሚቀበሉ ተናንት አስታዉቀዋል።

የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ልዩ ኃይል ከትግራይ ለቀው በመውጣት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ወደነበሩበት ድንበር እና ወሰን እንዲመለሱ የቀረበው ቅድመ ሁኔታ የመጀመሪያው ነው። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ « ፈጸሟቸው» ላሏቸው ጥፋቶች ተጠያቂ እንዲሆኑ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትግራይ ክልል ለተፈጸመው ወንጀል በገለልተኛ አካል እንዲያጣራ ጠይቋል።
በክልሉ የሚከናወኑ የሰብአዊ ድጋፎች ያለክልከላ እንዲዳረሱ እና የክልሉ ተወላጆችም ከተፈናቀሉባቸው አካባቢዎች ተመልሰው እንዲቋቋሙ ቡድኑ ባወጣው መግለጫው አመልክቷል።
 
የተቋረጡ የኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮምዩንኬሽን፣ የባንክ፣ የአየር ጉዞ፣ የትምህርት እና የጤናን የመሳሰሉ አገልግሎቶች ይጀመሩ የሚሉት በቅድመ ሁኔታው የተካተቱ ናቸው። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እንዲከበር ጥያቄ ያቀረቡት የትግራይ አማፂያን የ2013 ዓ.ም የትግራይ ክልል በጀት እንዲለቀቅ ባስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ ሥር “የኢትዮጵያ መከላከያ፣ የፌድራል ፖሊስ እና የስለላ ተቋማት ትግራይ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም” የሚል ሐሳብ አካተዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አቅጸስላሴ የኢትዮጵያ መንግስት ኃይሎች ከወልቃይት አካባቢ ለቀው እንደማይጡ ቀደም ሲል በጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው »የወልቃይት ፣ ጠገዴ ፤ የጠለምት እና የራያ አካባቢዎች አማራነት የተረጋገጠ እና የተዘጋ ፋይል ነው» ማለታቸውን የክልሉ ብዙኃን መገናኛ ዘግቧል። የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሰኞ የተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ከወጣ በኋላ ክልሉን የተቆጣጠሩት የትግራይ ኃይሎች በቅድመ ሁኔታ እንቀበላለን ያሉት የተኩስ አቁም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን በይፋ የተሰጠው ምላሽ የለም። በትግራይ ኃይሎች የቀረበው ቅድመ ሁኔታ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በተናጥል ያወጀው የተኩስ አቁም በዘላቂነት እንዲተገበር ምን ያህል አስቻይ ነው፤ ሃሳባችሁን አጋሩን።