የትግራይ መንግስት ወቅታዊ የአቋም መግለጫ

የትግራይ መንግስት ወቅታዊ የአቋም መግለጫ

በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ፣ እንግልት፣ እስርና ግድያ እንዲያበቃ ሁሉም የድርሻውን ሚና ሊወጣ ይገባል። በቅድምያ የትግራይ ሰራዊት የእናቶች ዘመቻ በሚል በተሰየመው ኦፕሬሽን በደቡብ ትግራይ የሚኖረው ህዝባችን ከወራሪዎችና ተስፋፊ ሃይሎች ነፃ ለማውጣት በቅጥረኛ ታጣቂ የደመኛ ጠላቶቻችን ሃይሎች ላይ ከሓምሌ 5 2013 ዓ/ም ጀምሮ እየወሰደው ባለው ነጎድጓዳዊ ጥቃት እስከአሁን ለስመዘገበው አንፀባራቂ ድል የትግራይ መንግስት ለትግራይ ህዝብና ለወዳጆቻችን የእንኳን ደስ ያላችሁ ደስያለን መልእክት ሲያስተላልፍ ክብር ይሰማዋል። በሃገር ቤትና በተለያዩ የአለም ሃገራት የሚኖረው የትግራይ ህዝብ፣ አንድነቱን እንደብረት አጠንክሮ፣ የትግራይ ሰራዊትና ህዝባችን ከመረጡት ህጋዊ የትግራይ መንግስት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ ላለፉት ስምንት ወራቶች ወራሪዎችን ለመመከት ባደረገው ትንቅንቅ የማታማታ ደመኛ ጠላቶችን አይቀጤ ቅጣት ቀጥቶ አከርካሪያቸውን ሰብሮ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ የሚኖርበትን አከባቢ በማረጋጋት ሰላሙን በትግሉ አረጋግጦ አንፃራዊ እፎይታ አግኝቶ ንፁህ አየር በመተንፈስ ላይ ይገኛል።
 
ሆኖም አሁንም የሚበዛው የምዕራባዊ ዞንና አንዳንድ የደቡባዊ ትግራይ አከባቢዎች በደመኛ ጠላቶቻችን ቁጥጥር ውስጥ ስለሚገኙ በሁለቱም ዞኖች የሚኖረው የትግራይ ህዝብ ታሪክ ይቅር የማይለው ዘግናኝ ግፎችና በደሎች እየደረሱበት ነው። በመሆኑም በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁሬታ የተረዱትን ማለትም የትግራይ ህዝብና መንግስት ህልውናቸውንና ደህንነታቸውን በትግላቸው ለማረጋገጥ እያካሄዱት ያለውን ህጋዊ፣ ፍትሃዊና ተቀባይነት ያለው ህዝባዊ ጦርነት መጋመሱን እንጂ አለመጠናቀቁን በውል በመገንዘብ በተለይም የደመኛ ጠላቶቻችን ትንኮሳ በመቆጣጠር በቀጣይም ግብአተ መሬታቸውን ለማፋጠን ሁለንተናዊ ዝግጅታቸውን አጠናክረው ትግላቸውን ቀጥለዋል።
 
የፋሺሽት አብይ አህመድ ቡድንና የጥፋት አጋሮቹ ነፃ ባልወጡት የትግራይ ቦታዎች የሚኖረውን ህዝባችን ጨምሮ ባጠቃላይ የትግራይ ህዝብ እንደህዝብ በጥይት፣ በረሃብ በፆታዊ ጥቃትና ሃብትና ንብረቱን በማውደም ከምድረገፅ ለማጥፋት ቀርፀው ተግባራዊ ያደረጉትን እኩይ ፓኬጅ አሁንም አጠናክረው ቀጥለውበታል። ይህ ወራሪዎች የነደፉት የጥፋት ፓኬጅና ፕሮጀክቶች በተለያዩ የኢትዮጽያ አከባቢዎች በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ እያደረሱት ያለው ስነልቦናዊና አካላዊ ባርባራዊ በደል ዘግናኝ በሆነ አኳሃን እየፈፀሙት ይገኛሉ። ተጋሩ ጥረው ግረው ያፈሩትን ሃብት በጠራራ ፀሃይ በመዘረፍ ላይ ናቸው። እነዚህ የትግራይ ህዝብ ደመኛ ጠላቶች ህዝባችን ከጀግናው የትግራይ ሰራዊትና መንግስት ጎን ተሰልፎ ነፃ ባወጣቸው ከተሞችና ገጠሮች የሚኖረውን ንፁ ወገናችንም በበሽታ፣ እርዛትና ረሃብ እንዲያልቅ በየብስና በአውሮፕላን የእርዳታ እህል ወደ ትግራይ እንዳይገባ የህዝብ የትራንስፖርት መጓጓዟና አውሮፕላኖች ወደ ትግራይ እንዳይቀሳቀሱ አግዷል። የመብራት፣ የስልክ፣ የኢንቴርኔት፣ የባንክና ወዘተ አገልግሎቶችም እንዲቋረጡ አድርጓል። ይህ የወራሪዎቹና የትግራይ ህዝብ ደመኛ ጠላቶች እኩይ ሰይጣናዊ ተግባር ከዚህ በፊት በህዝባችን ላይ ሲያካሂዱት የነበረው ጀምላዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅጥያ መሆኑን የትግራይ ህዝብ ወዳጆች፣ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዉል እንደሚገነዘቡት የትግራይ ህዝብና መንግስት ሙሉ እምነት አላቸው።
 
የፋሺሽት አብይ አህመድ ቡድን የመሰረተ ልማት አውታሮች ከመዝጋት እንዲሁም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ከማቋረጥ ባሻገር ነፃ ባልወጡት የትግራይ አከባቢዎች እንዲሁም አዲስአባባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጽያ አከባቢዎች የሚኖሩትን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ከዚህ በፊት በአረመኔው ፋሺሽት አብይ አህመድና አጋሮቹ በማንነታቸው ብቻ ሲደርስባቸው የነበረው ግፍ በከፋ መልኩ በማጠናከር ብዙ መከራ፣ ሰቆቃ፣ እንግልት፣ መፈናቀል፣ እስርና ሞት እያደረሰባቸው ይገኛል። ከዚህ በፊት ሃገርንና ሀዝብን ያገለገሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጅ የቀድሞ የኢፌደሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት በተለያዩ የማጎርያ ስፍሮች አስሮ እያሰቃያቸው ይገኛል። እንደትላንት ሁሉ በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪል የትግራይ ተወላጆች ማለትም ነጋዴዎች፣ ባለሃብቶች፣ ሙሁራን፣ ተማሪዎች፣ በመንግስትና በግልና መስራቤቶች በአምራች ተቋማት የሚሰሩ ሰራተኞች፣ ላብ አደሮች እንዲሁም የተለያዩ የግል አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ባለቤቶች የሆኑ ከዚህ በተጨማሪም ኢመደበኛ በሆኑ የስራ መስኮች ተሰማርተው የእለት ጉርሻ ለማግኘት ደፋ ቀና የሚሉት ንፁሃን የትግራይ ተወላጆች ያለምንም ጥፋት እስከ አርባሰባት ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚለካ ሙቀት ባላቸው ቦታዎች
እነደማንኛውም ግኡዝ እቃ በኮንቴኔር ታሽገው በመሰቃየት ላይ ናቸው። ግማሾቹ ደብዛቸው ጠፍቶ የገቡበት አይታወቅም። ከእስርና እንግልቱ በተጨማሪ የትግራይ ተወላጆች ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩተን ሃብትና ንብረት በመዘረፍ ላይ ነው። አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ሳይቀር በፋሺሽት አብይ አህመድና ቡዱን ጀሌዎቹ ታሽገዋል። ይሀውም በቤተሰባቸው ዘንድ የስነልቦና ቀውስን አስከትሏል። አንዳንዶቹም የሚበሉትንና የሚጠጡትን አጥተዋል።
 
ነገር ግን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በአጠቃላይ የትግራይን ህዝብ ጉሮሮ ለመዝጋት የተሰማሩትን በተለየም በአሁኑ ወቅት ነፃ ባልወጡት የትግራይ ቦታዎች እንዲሁም አዲስአበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጽያ አከባቢዎች በሚኖር ህዝባችን ላይ ሰቆቃ፣ እንግልት፣ መፈናቀል፣ እስርና ግድያ እየፈፀሙ ያሉት የፋሺሽት አብይ አህመድ ቡድን የአመራር አባላት የአስፈፃሚና ፈፃሚ አካላት ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡና የእጃቸውን እንደሚያገኙ ወዳጅም ጠላትም ሊያውቅ ይገባል።
 
በአጭሩ ፋሺሽት አብይ አህመድና ሸሪኮቹ የትግራይን ህዝብ እንደህዝብ ከምድረገፅ ለማጥፋት ያልቧጠጡት አለት አልነበረም። በአሁኑ ወቅትም እነዚህ የጥፋት ሃይሎች የዘረጉት የጥፋት መረብና የከጀሉት የእልቂት ውድመት ለመተግበር በመሯሯጥ ላይ ናቸው። ስለዚህ አለም አቀፍ ማህበረሰብ፣ የሰብአዊ መብት ተቋማት እና የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በአጠቃላይ ባለድርሻ አካላት በትግራይ ህዝብ እየደረሰ ያለውን ጀምላዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ስፋትቱንና ጥልቀቱን በሚገባ እንደምትረዱት ይታመናል። በመሆኑም በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን መፈናቀል፣ ሰቆቃ፣ እንግልት፣ እስርና ግድያ እንዲያበቃ በተለይም የፋሺሽት አብይ አህመድ ቡድን መሰረታዊ የልማት አውታሮችን ቆርጦ የትግራይን ህዝብ ጉሮሮ በመዝጋት እየፈፀመ ያለውን ግፍ በማውገዝ የወራሪ ሃይሎች አመራሮችና ጋሻ አሻጋሪዎቻቸው በጦር ወንጀለኝነት ተከሰው ዓለም አቀፍ ፍርድቤት እንዲቀርቡ የማያዳግም፣ ተገቢ የሚዳሰስና የሚጨበጥ እርምጃ እንዲወሰድ የበኩላችሁን ሚና በሃላፊነት መንፈስ እንድትወጡ የትግራይ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።
 
በመጨረሻም በአሁኑ ወቅት ለግዜው በወራሪና ተስፋፊ ሃይሎች ስር ባሉት የትግራይ መሬቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ ጨምሮ በአራቱም የሃገሩቱ አቅጣጫዎች የምትኖር የትግራይ ህዝብ ትላንት አንድነትህን እንደአለት አጠንክረህ ወራሪዎችን እንደመከትክ ሁሉ ዛሬም እየደረሰብህ ባለው ዘግናኝ ግፍና መከራ ሳትበገር ወራሪ ሃይሎችንና ሴራዎቻቸውን በትግልህ በመበጣጠስ እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ በፅናት ታግለህ እንደምታሸንፋቸው የትግራይ ህዝብና መንግስት ቅንጣት ታክል አይጠራጠሩም። ነፃ በወጡት የትግራይ አከባቢዎችና በውጪ ሃገራት ያለሀው ህዝባችንም ከጠላት ጉያ ስር ሆኖ በመታገል ላይ ከሚገኘው ህዝባችን ጋር የትግል ክንድህን አቀናጅተህ እንደትላንት ሁሉ ዛሬም ትግልህን እንደምታፋፍም የትግራይ መንግስት ይተማመንብሃል።
ህልውናችንና ደህንነታችን በፈረጠመው ክንዳችን!
ትግራይ አሸንፋለች ምንግዜም ታሸንፋለች!
የትግራይ መንግስት ሓምሌ 7 2013 ዓ/ም
መቐለ ትግራይ