የታሸጉ ቆዳ ፋብሪካዎች እንዲከፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዘዙ

የታሸጉ ቆዳ ፋብሪካዎች እንዲከፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዘዙ


በስድስት ወራት ውስጥ ካላስተካከሉ ዕርምጃው ይፀናባቸዋል ተብሏል
(Ethiopianreporter) -በሚያደርሱት የአካባቢ ብክለት ምክንያት ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታሸጉት ስድስት የቆዳ ፋብሪካዎች፣ ከረቡዕ ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተከፍተው መደበኛ ሥራቸውን እንዲጀምሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ማዘዛቸው ተሰማ፡፡

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አማካይት በተወሰደው ዕርምጃ መሠረት፣ ኤሊኮ አዋሽ ቆዳ ፋብሪካን ጨምሮ፣ ባቱ ቆዳ ፋብሪካ፣ ድሬ፣ አዲስ አበባ፣ ዋልያ፣ እንዲሁም ጫማ የሚያመርተው የቻይናው ሉዊንግ የተባሉት ቆዳ ፋብሪካዎች ታሽገው ሰንብተዋል፡፡ አስተዳደሩ ዕርምጃውን ከመውሰዱ በፊት ለዓመታት የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓታቸውን እንዲያስተካክሉ ሲጠይቅና ሲያስጠነቅቅ መቆየቱን አስታውቋል፡፡ የቆዳ ፋብሪካዎች የፍሳሽ አወጋገዳቸውን አጣርተው የሚለቁበት ሥርዓት እንዲገነቡ የተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እየተራዘመ፣ ከአምስት ዓመታት በላይ መቆየታቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡

ይሁንና ጥቅምት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በተወሰደ ድንገተኛ ዕርምጃ ስድስቱ ቆዳ ፋብሪካዎች ያለማስጠንቀቂያ እንዲታሸጉና ሥራ እንዲያቆሙ መደረጋቸው ታውቋል፡፡ ፋብሪካዎቹ ሰፊ የዕፎይታ ጊዜ እንደተሰጣቸው ባይክዱም፣ በድንገት ያውም ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ታሽገው እንዲቆዩ በመደረጋቸው ምክንያት የደረሰባቸውን ጉዳት ለመንግሥት ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ለመንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ የፋብሪካዎቹ መዘጋት 3,000 ሠራተኞቻቸውን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ከማስገደዱም በላይ፣ ያለ ሥራ ለተቀመጡበት ጊዜ በወር ከ7.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማድረግ እንደሚገደዱ ማስታወቃቸው ተሰምቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፋብሪካዎቹ በመዘጋታቸው ሳቢያ በምርት ሒደት ላይ የነበሩ 28.7 ሚሊዮን የሚያወጡ ጥሬ ቆዳና ሌጦን ጨምሮ፣ ያለቀላቸው የቆዳና ሌጦ ምርቶች ለብልሽት መጋለጣቸው እንደሚያሠጋው ማኅበሩ ማስታወቁን ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል፡፡

ስድስቱ የቆዳ ፋብሪካዎች እያንዳንዳቸው ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡት 6,000 የበግና የፍየል ሌጦ፣ እንዲሁም 800 የከብት ቆዳ በአማካይ እያመረቱ የሚገኙ መሆናቸውን በመግለጽ ዕርምጃው እንዲጤን የጠየቀው ማኅበሩ፣ የአካባቢ ብክለት እንደሚያሳስበው አስታውቆ በስድስት ወራት ውስጥ ሁሉም ፋብሪካዎች የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ሥርዓታቸውን እንደሚገነቡ፣ ለዚህም ግዴታ መግባታቸውን ለመንግሥት እንዳስታወቀ ታውቋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ጊዜ ውስጥ ተገቢውን ደረጃ የጠበቀ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት ባልገነቡት ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ ማኅበሩ እንደሚደግፍ በመግለጽ፣ ለአሁኑ የተዘጉት ፋብሪካዎች እንዲከፈቱ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡

ይህ ጥያቄ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል የቀረበላቸው አቶ ኃይለ ማርያም፣ ማኅበሩ ፋብሪካዎቹን በመወከል በገቡት ግዴታ መሠረት እንደሚያከናውኑ መተማመኛ በመስጠቱ የተዘጉት ፋብሪካዎች እንዲከፈቱ ማዘዛቸው ታውቋል፡፡ ማኅበሩ እያንዳንዱን ሒደት ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና ከሌሎችም ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ እንዲዋቀርና ሥራውን እንዲከታተል ጠይቋል፡፡

የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከ20 ጊዜ በላይ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ጽፎ ምላሽ ማጣቱን በመግለጽ በፋብሪካዎቹ አድራጎት ተስፋ መቁረጡን ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የቆዳ ፋብሪካዎቹ የሚለቁት ፍሳሽ ቆሻሻ ከአካባቢ ብክለት ባሻገር በነዋሪዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲያሳድር መቆየቱ፣ በተለይም በሕፃናት ጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በማስመልከት ነዋሪዎች ቅሬታ ሲያቀርቡ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡


ለጋምቤላ እርሻዎች የተሰጠው ብድር የልማት ባንክን መመለስ ያልቻሉ ብድሮች ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር አድርሷል ተባለ

በመንግሥት ድጋፍ የግል አልሚዎች በጋምቤላ ክልል ለጀመሯቸው ሰፋፊ እርሻዎች የተለቀቀው ብር የኢትዮጵያ ልማት ባንክን የማይመለስና መመለሳቸው አጠራጣሪ የሆኑ ብድሮች መጠን፣ 8.6 ቢሊዮን ብር እንዲደርስ ምክንያት ሆነዋል ተባለ፡፡

ይኼንን ያሉት የአገሪቱ የገንዘብ ተቋማትን የሚቆጣጠረው ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ናቸው፡፡

የተበላሸ ብድር መጠን ከአጠቃላይ ብድራቸው 15 በመቶ መብለጥ እንደማይኖርበት ባንኮቹን የሚቆጣጠረው ብሔራዊ ባንክ በሕግ ቢያስቀምጥም፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሸ ብድር (የማይመለስ ወይም መመለሱ አጠራጣሪ የሆነ ብድር) መጠን ከአጠቃላይ የባንኩ የብድር ክምችት በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 25 በመቶ ደርሷል፡፡

ይኼንኑ እውነታ በመንተራስ የፓርላማው የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ ባንክን የ2010 ዓ.ም. ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸምና የዓመቱን ዕቅድ ሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በገመገመበት ወቅት፣ ብሔራዊ ባንክ የልማት ባንክን የተበላሹ ብድሮች ጉዳይ ለመከታተልና ባንኩን ለመደገፍ ያስቀመጠውን ሥልት በተመለከተ ማብራርያ እንዲሰጡ ተጠይቋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ባዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙት የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ በሰጡት ምላሽ፣ የልማት ባንክን የተበላሹ ብድሮች አስመልክቶ ያስቀመጠው የመፍትሔ አቅጣጫ መተግበሩን ከመከታተል ውጪ የተለየ ማድረግ የሚችሉት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ልማት ባንክ የተጠቀሰውን ያህል መመለስ ያልቻለና መመለሱ አጠራጣሪ የሆነ ብድር ክምችት ውስጥ ሊገባ የቻለው፣ የመንግሥት የፖሊሲ ባንክ እንደ መሆኑ መጠን ለማኑፋክቸሪንግና ለሰፋፊ እርሻዎች የልማት ዘርፍ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ የማበደር ኃላፊነቱን ለመወጣት ሲሞክር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሰጠው ብድር ተመላሽነቱ በሕጉ መሠረት አጠራጣሪ መሆኑ ቢገለጽም፣ ብድሩን የወሰዱት ተቋማት የዕፎይታ ጊዜያቻውን ጨርሰው ወደ ክፍያ አለመግባታቸው ወይም መዘግየታቸው እንጂ፣ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙና የማምረት እንቅስቃሴ  ውስጥ እየገቡ ያሉ በመሆናቸው የመክፈያ ጊዜውን በማሻሻል ብድሩ ሊመለስ የሚችል፣ ለብድሩ የዋለው ሀብትም የባከነ ሳይሆን መሬት ላይ ያለና ተጨማሪ ድጋፍና ክትትል ከተደረገበት ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

የልማት ባንኩን አጠቃላይ የማይመለስና መመለሱ አጠራጣሪ የሆነ ብድር ከአጠቃላይ 38 ቢሊዮን ብር 25 በመቶ ወይም 8.6 ቢሊዮን ብር እንዲደርስ ያደረገው፣ በጋምቤላ ለተጀመሩ ሰፋፊ እርሻዎች ልማት የተሰጠው ብድር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ልማት ባንክ የመንግሥትን ፖሊሲ ለማስፈጸም የተቋቋመ በመሆኑ በብድር የሚቀርበው ገንዘብ ይኼንኑ ዓላማ ለመደገፍ በመሆኑ ወትሮውንም ተመሳሳይ ችግሮች እንደሚገጥሙት የገለጹት አቶ ተክለወልድ፣ ለሰፋፊ እርሻዎቹ የተለቀቀው ብድር የሚታወቀውን ችግር እንዳባባሰው ጠቁመዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ከዓመት በፊት ተቋቁሞ የነበረው አጥኚ ቡድንም በጋምቤላ የተጀመሩ ሰፋፊ እርሻዎችን ብድርና እርሻዎቹ ያሉበትን ሁኔታ እንዳጣራ አስታውሰዋል፡፡ ለእርሻዎቹ ልማት የተወሰደው ብድር ተበልቷል ወይም ሥራ ላይ ውሎ ባለመመለሱ የባንክን የማይመለሱ ብድሮች መጠን እንዳገዘፈ ተናግረዋል፡፡

ልማት ባንክ በጋምቤላ ክልል ለሚገኙ ሰፋፊ  እርሻዎች (Commercial Farms) 4.9 ቢሊዮን ብር ብድር እንዳቀረበ ከዓመት በፊት ዘግበን ነበር፡፡ ለዚህ ዘገባ መረጃ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ያስጠኑት የጥናት ውጤት ሲሆን፣ በሰፋፊ እርሻዎች አልሚነት ብድሩን ያገኙት በርካቶቹ ያገኙትን ብድር ሥራ አለማዋላቸውን አረጋግጧል፡፡

በእርሻዎቹ አካባቢ ለመጋዘን ግንባታ በማለት የተለቀቁ ብድሮችን አብዛኞቹ አልሚዎች ለተባለው ተግባር አለመጠቀማቸውን አጥኚው ቡድን በሥፍራው በመገኘት በቆርቆሮና በሳር የተሠሩ መጋዘኖችን በማስረጃነት አቅርቧል፡፡

ለእርሻ ማስረጃነት ግዥ የተለቀቀውን ብድር አጠቃቀም ለማዳረስ ለተደረገው ጥረት ተገዙ የተባሉ ማሽነሪዎች በእርሻ ቦታዎች አለመገኘታቸውን፣ በአንድ የእርሻ መሬት ላይ ተደራራቢ አልሚዎች ብድር ማግኘታቸውንና አብዛኞቹም ወደ ትክክለኛ የእርሻ ልማት ከዓመታት በኋላም ቢሆን ያልገቡ መሆናቸውን በማረጋገጥ ሪፖርት አቅርቦ ነበር፡፡

ይኼንንም የጥናት ውጤት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ ኢሳያስ ባህረን ከኃላፊነታቸው ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡ በምትካቸው በብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ተቋማት ቁጥጥር ዘርፍ ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን ምክትል ገዥ አቶ ጌታሁን ናና መሾማቸው አይዘነጋም፡፡

‹‹መንግሥት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አዳዲስ አመራሮችን የሾመው የባንኩን የማይመለሱና የተበላሹ ብድሮች፣ እንዲሁም ለአጠቃላይ አሠራሮች መፍትሔ እንዲያበጁ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡