የተዳፈነዉ ብሶት: የአፋር መስተዳድር ባለሥልጣናት በህዝብ ላይ ያደርሱታል የሚባለዉን በደል በመቃወም ህዝቡ በተለይም ወጣቱ እንቅስቃሴ ከጀመረ ዓመታት አስቋጥሯል

የተዳፈነዉ ብሶት: የአፋር መስተዳድር ባለሥልጣናት በህዝብ ላይ ያደርሱታል የሚባለዉን በደል በመቃወም ህዝቡ በተለይም ወጣቱ እንቅስቃሴ ከጀመረ ዓመታት አስቋጥሯልበሥልጣን ላይ ያለዉ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) መሪዎች በተማሩ ኃይላት እንዲቀየሩ ወጣቶች በግልፅ መከራከር የጀመሩት የዛሬ ሰወስት ዓመት ግድም ነበር።


(dw)—ማቀጣጠያዉ የአንድ ሰዉ መታሰር ወይም መታፈን ነዉ።መሠረታዊዉ ምክንያት ግን፤ ታዛቢዎች እንደሚሉት ስር የሰደደዉ የፍትሕ፤ የነፃነት፤ የመልካም አስተዳደር እጦት ነዉ።ባለፉት ስድስት ወራት በማመልከቻ፤ በአቤቱታ እና በማስታወቂያ መልክ ብልጭ ድርግም ሲል የነበረዉ ተቃዉሞ አሁን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን፤ የመንግስት ሠራተኞች እና የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎችን ባደባባይ እያሰለፈ ነዉ። ሰልፉ፤ ማክሰኞ ሠመራ ላይ ነበር።ቅዳሜ አሳኢታ።የአፋሮች ተቃዉሞ።

ለመሐል ሐገሩ ፖለቲከኛ፤የተቃዋሚ ፓርቲ ይሁን የመንግሥት ባለሥልጣን፤ ለፖለቲካ ተንታኝ፤ ለጋዜጠኛ ወይም ለማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አርበኛ ድምፃቸዉ የሚስማ፤ ቢሰማም ትኩረት የማይስብ የሩቆች ብሶት ነዉ።የዳር አገሮች ጩኸት።የሚገቡት ቃል፤ የሚሰጡት ተስፋ እና ጅምር ምግባራቸዉ በአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ዘንድ ቢያንስ

እስካሁን ያስወደዳቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ  አሕመድ እንኳን ጠብ ለማብረድ ጅጅጋ፤ ወደብ ፍለጋ ጅቡቲ ሲሄዱ፤ ከኤርትራ ጋር መሪዎች ጋር ለመነጋገር ሲጠይቁ የአፋሮችን ብሶት፤ ቅሬታ እና ጥያቄ በይደር ትተዉ ግን የአፋሮችን ግዛት አቋርጠዉ ነዉ።

የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲን እንደሚሉት ወደቡ የጅቡቲ፤ የሶማሊላንድ ሆነ፤የኤርትራ ለኢትዮጵያ የሚጠቅመዉ፤ የሶማሌ እና የኦሮሞ እርቅ የሚፀናዉ አፋር ሲረጋጋ እና ሕዝቡ ሲፈቅድ መሆኑን ቀዳሚዎቹም ሆኑ ያሁኑቹ የኢትዮጵያ መሪዎች መዘንጋት የለባቸዉም።

መንበሩን ብራስልስ-ቤልጅግ ያደረገዉ የአፋር የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ሊቀመንበር ገአስ አሕመድ እንደሚሉት የአፋር ወጣቶችን ለአደባባይ ሰልፍ ያሳደመዉ የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስት የአፋርን ህዝብ መዘንጋቱ ጭምር ነዉ።

የአፋር መስተዳድር ባለሥልጣናት በህዝብ ላይ ያደርሱታል የሚባለዉን በደል በመቃወም ህዝቡ በተለይም ወጣቱ እንቅስቃሴ ከጀመረ ዓመታት አስቋጥሯል።በሥልጣን ላይ ያለዉ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) መሪዎች በተማሩ ኃይላት እንዲቀየሩ ወጣቶች በግልፅ መከራከር የጀመሩት የዛሬ ሰወስት ዓመት ግድም ነበር።
ይሁንና ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ታዛቢዎች እንደሚሉት ነባሮቹ የፓርቲዉ መሪዎች ከሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) ባገኙት ጠንካራ ድጋፍ የወጣቶቹን ንቅናቄ በቀላሉ አክሽፈዉ ሥልጣኑን እንደተቆጣጠሩ ቀጠሉ።በፖለቲካ ተንታኝ  ዩሱፍ ያሲን አገላለፅ «ሕወሐቶች ሐጂ ስዩምን አንግሰዉ ሄዱ።»

ሐጂ ስዩም አወል።ቀድሞ የመስተዳድሩ የፀጥታ ዘርፍ ሐኃላፊ ነበሩ።ከ2008 መጀመሪያ ጀምሮ ርዕሠ መስተዳድር ናቸዉ።እነ ሐጂ ስዩም የሚመሩት የአፋር መስተዳድር ችግር መሠረታዊ ምክንያት፤ አቶ ገአስ

አሕመድ እንደሚሉት ብዙ ነዉ።ዋናዎቹ ግን ሰወስት ናቸዉ።የአፋር መስተዳድር ባለፉት 24 ዓመታት በአንድ ፓርቲ መገዘቱ-አንዱ ምክንያት ነዉ።የፓርቲዉም ሆነ የክልሉ መሪዎች በሙስና የተዘፈቁ፤ ያልተማሩ እና ለሕወሐት ተገዢ መሆናቸዉ-ሰወስት።

ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በፊት የገዢዉን ፓርቲ (የአብዴፓ)ን መሪዎች በወጣቶች ለመለወጥ የተደረገዉ ሙከራ በርግጥ አልተሳካም።የወጣቶቹ ትግል ግን ተጠናከረ እንጂ አልቆመም አብዴፓ እራሱን የመለወጥ እድሉ ሲነፈገዉ ወጣቶቹ ፓርቲዉን ከነመሪዎቹ ይቃወሙ ገቡ።
የዛሬ ስድስት ወር ግድም የሰመራ ዩኒቨርስቲ የሰዉ ኃይል አደረጃጃት ኃላፊ ታፍነዉ ተወሰዱ መባሉ  ዉስጥ ዉስጡን ሲብላላ ዓመታት ያስቆጠረዉ ተቃዉሞ አደባባይ የሚወጣበት ሰበብ አገኘ።

ይላሉ ለሕወታቸዉ ሥለሚፈሩ ስማቸዉ መጠቀሱን ያልፈለጉ የሰመራ ዩኒቨርስቲ መምሕር።የመንግስት ሠራተኛነኝ ያሉን ሌላዉ የሰመራ ነዋሪ ደግሞ  አቶ ረሺድ ሳሌሕ የታፈኑት የአንድ ጄኔራል ትዕዛዝን አልቀበል በማለታቸዉ ነዉ ይላሉ።
በበራሪ ወረቀቶች፤ በማመልከቻ እና አቤቱታ ለቀረበዉ ጥያቄ የመስተዳድሩ ባለሥልጣናት የሰጡት መልስ፤ ጥያቄ አቅራቢዎችን ማሰር፤ ያልታሰሩትን ማስፈራራት ሆነ።ተቃዉሞዉም ከማመልከቻ ይልቅ ወደ አደባባይ ሰልፍ ናረ።ማክሰኞ የሰመራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፤የሰመራ እና የአካባቢዉ ከተሞች ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተዉ መስተዳድሩን በግልፅ አወገዙ።

አቶ ገአስ እንደሚሉት መስተዳዱሩን በመተቸታቸዉ አሁን እስር ቤት ከሚገኙት አንዱ የታሰሩት በፌስ ቡክ ፅሑፍ አሰራጭተሐል በሚል ምክንያት ነዉ።አጠቃላይ የመብት ረገጣዉ ደግሞ ሕዝቡን በመኖር እና አለመኖር መሐል አቃርጦ ይዞታል።

አቶ ዩሱፍ ያሲን ደግሞ በአፋር መስተዳድር ያለዉ ሁለንተናዊ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ነዉ።የሰመራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የመሩትን ሠልፈኛ ለመበትን ፀጥታ አስከባሪዎች ተኩስ ከፍተዉ እንደነበር የሰልፉ ተሳታፊዎች አስታዉቀዋል።በተኩሱ የተጎዳ ሰዉ ግን የለም።ለወትሮዉ የአመራር ለዉጥ ሲጠይቅ የነበረዉ ወጣት አሁን ጥያቄዉ ወደ ሥርዓት ለዉጥ ተሸጋግሯል።ወጣቱ እንዳለዉ።

የአደባባይ ሰልፉ በተለያዩ ከተሞች እንደቀጠለ ነዉ።የዓይን ምስክሮች እንዳሉት ባለፈዉ ቅዳሜ አሳኢታ ዉስጥ አደባባይ የወጣዉ የከተማይቱ ነዋሪ እና የኮሌጅ ተማሪዎችም የሥርዓት ለዉጥ እንዲደረግ በግልፅ ጠይቀዋል።የፖለቲካ ተንታኝ ዩሲፍ ያሲን እንደሚሉት በአፋር መስተዳድር

የሚታየዉ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜu እየተባባሳ እና ስር እየሰደደ ነዉ።
አሁን በስልጣን ላይ ያሉት መሪዎችም የችግሩ ፈጣሪ በመሆናቸዉ ትክክለኛ መፍትሔ መፈለጋቸዉን አቶ ዩሱፍ ይጠራጠራሉ።

የአፋር ሕዝብ ጥያቄ በሌሎች አካባቢዎች ከተነሱት ጥያቄዎች የተለየ አይደለም። ይሁንና የህዝቡ አኗኗር ከሌሎቹ አካባቢዎች ለየት ያለ ነዉ።መስተዳድሩ ከኦሮሞ፤ ከኢሳ-ሶማሌ፤ ከአማራ፤ ከትግራይ፤ ከኤርትራ እና ጅቡቲ ጋር የሚዋሰን ነዉ።መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡ ለኢትዮጵያ ሲበዛ ስልታዊ ነዉ።
በዚሕም ምክንያት የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲን እንደሚያምኑት፤የፌደራሉን መንግስት ሥልጣን ለመያዝ የሚሻኮቱ ኃይላት የመስተዳድሩን ፖለቲካዊ እዉነት ማወሳሰባቸዉ አይቀርም።

ዉስብስቡን ችግር ለመፍታት የመስተዳድሩ ባለሥልጣናት፤ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፤ ምሑራን እና የፌደራሉ መንግስትም ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ እንዲወስዱ ታዛቢዎች ይመክራሉ።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ