የባለሃብቱ ልጅ በጋምቤላ ተገደለ

የባለሃብቱ ልጅ በጋምቤላ ተገደለ

(Sendek News) ከጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ 400 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘው ዲማ ወረዳ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ዕለት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ ወጣት አማኑ ኢተፋ መኮንን ከጫካ ውስጥ በወጡ ማንነታቸው ለጊዜው ባልታወቁ ኃይሎች በአራት ጥይት ተደብድቦ መሞቱን ተገለጸ።

የሟች ወጣት አማኑ ኢተፋ ወላጅ አባት አቶ ኢተፋ መኮንን በትናንትናው ዕለት ለሰንደቅ እንደገለጹት፣ “አለምንም ምክንያት ሰኞ ጠዋት በጥይት ተመቶ ነው የተገደለው። ከእርሻ ቦታ ወደከተማ የቀን ሠራተኞችን ለማምጣት እየሄደ ሳለ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ከጫካ በመውጣት በጥይት ደብድበው ገድለውታል። ጉዳዩን ለጣቢያ አመልክቻለሁ። አሁን የልጄን አስከሬን ይዤ ወደ ነቀምት እየሄድኩ ነው” ብለዋል በተሰበረ ልብ።

“ቤተሰብ እስከመግደል የሚያደርስ ጠብ ወይም በሌላ ሁኔታ የሚጠራጠሩት ሰው አለ ወይ?” ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “ልጄ ከሰው ተግባቢ በአካባቢው የሚወደድ ነው። እኔም በግሌ ጠብ ውስጥ የገባሁበት ሁኔታ የለም። የምጠረጥረውም ሰው የለኝም። ለልጄ ሞት የምሰጠው ምክንያት የለኝም። ፍርዱ ከአምላክ ነው የምጠብቀው” ብለዋል።

በአካባቢው የነበሩ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዓይን እማኝ ለሰንደቅ ሲናገሩ፣ “ሟች ጥቃቱ ከደረሰበት በኋላ ከዋናው መንገድ ከመኪና ላይ ሸሽቶም ለማምለጥ ሞክሮ ነበር። አስክሬኑን ያገኘነው ጫካ ውስጥ ነው። የራስ ቅሉ አራት ቦታ በጥይት ተመቶ ፈርሶ ነበር። አባቱም በአቅራቢያ ባለመኖሩ አስክሬኑን በአዲስ አበባ ሚኒሊክ ሆስፒታል አስመርምረን አሁን እሱን አጅበን ወደ ወለጋ እየተጓዝን ነው” ብለዋል።

አቶ ኢተፋ መኮንን በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት ተሰማርተው እየሰሩ የሚገኙ ባለሃብት ናቸው።

በጋምቤላ ክልል በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ከጸጥታ ጋር በተገናኘ ያላቸውን ሥጋት በተለያዩ መድረኮች ሲያሰሙ እንደነበር ይታወቃል። በተለይ ለሱዳን ድንበር በጣም የተጠጉት የግብርና እርሻ ቦታዎች ከፍተኛ የፀጥታ ችግሮች እንዳሉባቸው በስፋት ይታመናል።

የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዑመድ ኡቶ ስለጉዳዩ አነጋግረናቸው በሰጡት ምላሽ፣ “ወጣቱ መገደሉን አውቃለሁ። ዝርዝር መረጃ ግን የለኝም ብለዋል።¾