የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሐመድ ከእስር ቤት ለማምለጥ ሞክረዋል – ፖሊስ

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሐመድ ከእስር ቤት ለማምለጥ ሞክረዋል – ፖሊስ

አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2011 “የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሐመድ ከእስር ቤት መስኮት ሰብረው ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል” ሲል ፖሊስ ገለጸ።

አቶ አብዲ መሐመድ ከሐምሌ 26-30 ቀን 2010 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሳቢያ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።

አቶ አብዲ ዛሬ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀጠሮ ችሎት በቀረቡበት ወቅት መርማሪ ፖሊስ እንደገለጸው አቶ አብዲ መሐመድ ለደህንነታቸውና ለጤናቸው ሲባል የፖሊስ ቢሮ ውስጥ ታስረው ነበር።

ይሁንና አቶ አብዲ የታሰሩበትን ቢሮ መስታወት በመስበርና አንድ የጥበቃ አባልን ጉሮሮ በማነቅ ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል ብሏል።

አቶ አብዲ መሐመድ በበኩላቸው ድርጊቱ ሆን ብሎ ስሜን ለማጥፋትና እኔን ለመምታት የተደረገ ሴራ ነው ብለዋል።

ድርጊቱን ፈጽመዋል መባሉ ውሸት መሆኑንና በእርሳቸው ላይም ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ  ተናግረዋል።

ምቹ ባልሆነ እስር ቤት መታሰራቸውን፣ የአዕምሮ ህመምተኛ የሆነ ታሳሪ የታሰሩበትን ክፍል በር ገንጥሎ በመግባት ሁለት ቀን ጉዳት ሊያደርስባቸው እንደሞከረና ይህም በደህንነታቸው ላይ ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

በአንድ አጋጣሚም አንድ አስረኛ የሽንት ቤት በር ገንጥሎ እሳቸው ላይ በመጣል ጉዳት ሊያደርስ መሞከሩንም ተናግረዋል።

የታሰሩበት እስር ቤት የማይመችና በጤናቸው ላይም እክል እንደፈጠረባቸውም ነው አቶ አብዲ የተናገሩት።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ አቶ አብዲ መሐመድ ማንኛውም እስረኛ በሚቆይበት እስር ቤት እንደታሰሩ ገልጸው በእርሳቸው ላይ ምንም አይነት የተለየ ጫና እየተደረገ እንዳልሆነ አስታውቋል።

በተጨማሪም ፖሊስ ከእርሳቸው ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ለግጭቱ መቀስቀስ ተጠያቂ መሆናቸውንና በዚህም ተጸጽተው ይቅርታ መጠያቃቸውን ገልጿል።

ፖሊስ በአብዲ መሐመድ የክስ መዝገብ ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ ምርመራውን እያካሄደ ያለው ፖሊስ የምርመራውን ውጤት ለጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ይዞ እንዲቀርብ በማሳሰብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Source: ena


የሶማሌ ክልል የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ከእስር ቤት መስኮት ሰብረው ለማምለጥ ሙከራ ማድረጉን ፖሊስ ገለጸ።

እንደፖሊስ ማብራሪያ አቶ አብዲ የታሰሩበትን ቢሮ መስታወት በመስበርና አንድ የጥበቃ አባልን ጉሮሮ በማነቅ ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ አቶ አብዲ መሐመድ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን በመጥቀስ፥ ሆን ተብሎ ስሜን ለማጥፋትና እኔን ለመምታት የተደረገ ሴራ ነው ብለዋል። 
#FBC