የሲዳማ ሕዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ ህገ መንግታዊና ነባራዊ ምክንያቶች እና የደረሰበት ደረጃ

የሲዳማ ሕዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ ህገ መንግታዊና ነባራዊ ምክንያቶች እና የደረሰበት ደረጃ

THE FINFINNE INTERCEPT

የሲዳማ ብሔር ራስን በራስ የማስተዳደር / በክልል የመደራጀት ጥያቄ/ በህጉ መሰረት ፈጣን ምላሽ በህገ መንግሥቱ በተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎች ሳይወሰዱ ገደቡ ሊያልቅ ሁለት ወራት ብቻ ቀርተውታል። የዞኑ አመራር የጥያቄውን ታሪካዊ ዳራና አስፈላጊነት በመተንተን የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መንግስትን እንደሚከተለው በፅሁፍ ጠይቋል።
መግቢያ
የሲዳማ ብሔር እንደሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሱ መልክዓ ምድራዊ አሰፋፈር፣ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት፣ የራሱ ባህልና፣ ማንነት ያለውና የህዝቦች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም እራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች እንዲከበሩ የታገለ ህዝብ ነው፡፡ በትግሉ ሂደት በሀገሪቱ ህገ መንግስታዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ሥር እንዲሰድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
በ1987 ዓ/ም በፀደቀው የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት እንደተደነገገው የአገራችን የመንግሥት አወቃቀር ፌዴራላዊ ሲሆን በተለይም ለአገራችን ህዝቦች ተስማሚ የሆነውን ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ለመገንባትና በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም ያለመ ሲሆን ሀገሪቷን ለፌዴሬሽኑ አባል የሆኑ ዘጠኝ ክልሎች በህገ-መንግሥቱ ተቋቁመዋል፡፡ በተጨማሪም በህገ መንግስቱ በአዲስ ክልል የመደራጀት መብት የተደነገገ እና መብቱን ተግባራዊ ለማድረግም መሰረታዊ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን የሚያሟላ ብሔር የራሱን ክልል የማቋቋም መብት ተደንግጓል፡፡ የሲዳማ ህዝብ የራሱ አስተዳደር እንድኖረዉ ለ130 ዓመታት የታገለ ስሆን በተለይም ህገ መንግሥቱ ሲፀድቅም ይሁን ከዚያ በኋላ የሲዳማ ህዝብ በራሱ ክልል የመደራጀት ጥያቄ በተደጋጋሚ በተደራጀና ባልተደራጀ መልኩ ሲያቀርብ ቢቆይም ጥያቄው ህገ መንግስታዊና የህዝቡ መሆኑ ቢታወቅም ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ በ2010 ዓ/ም በተመሳሳይ ሁኔታ ጥያቄው በህገ መንግስቱ መሰረት በህዝበ ውሳኔ እንዲያልቅ ለሚመለከተው አካል ሁሉ ህጉን ጠብቆ የቀረበ ቢሆንም እስከ ዛሬ ድረስ በአፈፃፀም ችግር ምክንያት ፈጣን ምላሽ አልተሰጠውም፡፡
በ1984 ዓ/ ም ፤ በ1994፤ በ1987 እንድሁም በ2004ዓ/ም በተለያየ መልኩ ስነስ የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎችን ማየት ይቻላል፡፡ በ1994 ዓ/ ም ከከተሞች አስተዳደር ሥርዓትና እንድሁም የሲዳማ ህዝብ የክልል ጥያቄ ጋር ተያይዞ ሰላማዊ ሰልፍ በወጣዉ ህዝብ ላይ የደረሰዉ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እስከዛሬ ድረስ በህዝቡ ዉስጥ ጠባሳ ጥሎ ይገኛል፡፡የሲዳማ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ህደቱን ጠብቆ የተጠየቀዉ በ1997ዓ/ ም ስሆን በወቅቱ ከነበረዉ አመራር ጋር ዉይይት ተደርጎ ጥያቄዉ የህዝብ ሆኖ ሳሌ የአመራር ጥያቄ ነዉ በማለትና ለጊዜዉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ይፈታ እንጅ በቀጣይ ይታያል በሚል በማታለያ አነጋገር እንድቆይ በይደር መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ስለዚህ ይህ ሰነድ የሲዳማ ብሔር ራስን በራስ የማስተዳደር / በክልል የመደራጀት ጥያቄ/ በህጉ መሰረት ፈጣን ምላሽ በህገ መንግሥቱ በተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎች ሳይወሰዱ ቀርቶ በመጓተቱና ጊዜ ገደቡ ሊያልቅ ሁለት ወራት ብቻ በመቅረቱ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ህዝቡ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው፡፡ በመሆኑም የሲዳማ ህዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ለበርካታ ዓመታት ያሳየውን ትግል፣ ጥያቄው ህጋዊና ተቋማዊ በሆነ መልኩ እንዲመለስ የተደረጉ ጥረቶችና ተግዳሮቶች እንዲሁም አሁን ያለበትን ነባራዊ አውድ የሚገመግምና የህዝቡን ፅኑ ፍላጎትና ጥያቀው ባይመለስለት ሊፈጠሩ የሚችሉ ስጋቶች ጭምር የያዘ ሰነድ ነው፡፡
የሲዳማ ሕዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ ህገ መንግታዊና ነባራዊ ምክንያቶች
1.1 የብሔሩ የሕዝብ ብዛት እንደመነሻ
የሲዳማ ጠቅላላ ሕዝብ በክልሉ በሕዝብ ቁጥር ዕድገት ምጣኔ በ2010 ዓ/ም ትንበያ መሠረት 4‚152‚460 ሲሆን የህዝቡ ቁጥር በትንበያ የተገለጸዉ ብቻ ሳይሆን የዉልደት መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑ ከዚህ እንደሚበልጥ ይጠበቃል ፡፡ በአገሪቱ የህዝብ ብዛት 5ኛ ደረጃ ይዞ የሚገኝ ነው፡፡ የሕዝብ ጥግግቱም 558 በካሬ ኪ.ሜትር ነው፡፡ የሕዝብ ብዛት ለአንድ አገርም ሆነ ክልል ጥንካሬ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ህዝብ በአንድ ዞንና በአንድ የከተማ አስተዳደር ብቻ የተዋቀረ ሲሆን መንግሥታዊ አገልግሎት ለመስጠትና ልማትን ለመደገፍ አዳጋች ነው፡፡ ከዚህም አንፃር የሲዳማ ሕዝብ በአንዳንድ አፍሪካ አህጉር ራሳቸውን ችለው አገር ከሆኑ አገሮች ብቻ ሳይሆን አገራችን ከምትከተለው ፌደራላዊ ሥርዓት ምክንያት ክልል የመሆን ዕድል ተጠቅመው ራሳቸውን እያስተዳደሩ ከሚገኙ ክልሎች የሕዝብ ቁጥር አንፃርም ሲታይ ይህ ሕዝብ ለሚጠይቀው ሕገ-መንግሥታዊ የክልል ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት በቂ ምክንያት ይሆናል፡፡
1.2 የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት እንደመነሻ
የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ ታሪክና ማንነት ተጨፍልቆ ብዙ አፈናና ረገጣ ሲደርስባቸው ቆይቶ ለዘመናት ያደረጉት ትግል ተሳክቶ አሀዳዊና ጨቋኙ ሥርዕት ከተገረሰሰ በኋላ ሳይመለስ የቆየው የህዝብ ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ታሪካዊ ሰነድ እንደሆነ የህዝብ ጭቆና የሚያሳስባቸው ሁሉ ያምናሉ፡፡ ሕገ-መንግስቱ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ እንደ ምሰሶ የወሰዳቸው መርሆዎችም በአንቀጽ 8 (1) የሕዝብ ስልጣን ባለቤቶች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች መሆናቸው፤ አንቀጽ 8(2) ሥር ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ሉዓላዊ ሥልጣናቸው መገለጫ የሆነው ህገ-መንግሥቱ ራሱ እንደሆነ እና በአንቀፅ 9(1) ሥር ደግሞ ህገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ህግ እንደሆነ የሚደነግግ መሆኑ ነው ፡፡
የኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገ-መንግስት በሕዝብ ሲነሳ የነበረዉን የረዥም ጊዜ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መሠረት የጣለ ሕገ-መንግስት ነዉ /አንቀፅ 39 እና 47/፡፡ ማንኛዉም የመንግስት አካል እነዚህንና ሌሎች የግልና የቡድን መብቶች የማስከበርና የማክበር ግደታ እንዳለበት አስቀምጧል /አንቀፅ 13 /፡፡
በሕገ-መንግስቱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብና ህዝብ የራስን መብት በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ ያለገደብ የተጠበቀ ነው፡፡ ይህ መብት በአይነቱ ልዩና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜ እንኳን የማይገደብ ፍፁማዊ መብት /absolute right/ እንደሆነ የኢፌዲሪ ህገ-መንግሥት አንቀፅ 39(1) እና 93(4) (ሐ) ሥር ተመልክቷል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአንድ ክልል ሥር ተካትቶ ያለ ብሔር ብሄረሰብ ህዝብ በማንኛውም ጊዜ የራሱን ክልል የማቋቋም መብት በኢፌዲሪ ህገ-መንግሥት አንቀፅ 46(2) ሥር በግልፅ ቋንቋ ያለገደብ የተፈቀደ ነው፡፡ ይህንን መብት ተግባራዊ ለማድረግም የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች አን
በተጨማሪም የፊቼ ጫንባላላ በዓል በውስጡ በርካታ ባህላዊ ትሩፋቶች ያሉት ሲሆን የሲዳማ ህዝብ የዘመን መለወጫ በዓል ከብሔሩም አልፎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቅርስና የዓለም ሕዝቦች ሁሉ የጋራ ቅርስ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በፊቼ ጫምባላላ በዓል ጊዜ፣ በጋራ ሥራ ሲሰራ፣ በለቅሶና በሌሎች ክስተቶች ወቅት የሚፈፀም የቄጣላ ሥርዓት የባህሉ አንዱ ክፍል ነዉ፡፡
በመሆኑም የሲዳማ ህዝብ በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖር፣ የራሱ ቋንቋና ባህል ያለው ህዝብ በመሆኑ አንድ ህዝብ ክልል ሆኖ ለመደራጀት በህገ-መንግሥቱ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ከሚገባው በላይ ያሟላ በመሆኑ ፈጣን ህገ-መንግስታዊ ምላሽ የሚሻው ነው፡፡
1.3 የሲዳማ ህዝብ ራስን በራስ ለማስተዳደር ያደረገው ትግል እንደ መነሻ
የሲዳማ ህዝብ ራስን በራስ ለማስተዳደርና የብሔር ጭቆናው እንዲቆም ትግል ማድረግ ከጀመረ በርካታ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁንና ግን በወቅቱ የነበረው የነፍጥ ሥርዓት የብሔር ብሔረሰቦችንና የህዝቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በነፍጥ ጨፍልቆ አገዛዙን በሃይል ለማስቀጠል የሞከረበት ወቅት ስለነበረ የሲዳማ ህዝብ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች የህዝቡን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቹ በመጣሳቸው ምክንያት በአርሶ አደሩ፣ በባላባቱና፣ በጭሰኛው መካከል የነበረውን የኢኮኖሚም ሆነ የማንነት ጭቆና በመቃወም ትግል አድርጓአል፡፡ የሲዳማ ተወላጅ ወጣቶች ተማሪዎችም በተማሪዎች ንቅናቄ በመሳተፍና የተማሪዎች ትግል መሪ ወይም ፕሬዝዳንት ሆኖ በመምራት (ለምሳሌ ይ/ዓለም 2ተኛ ደረጃ ት/ቤት አቶ አየለ ቦሮጀና ሌሎችም) ሕዝባዊ መንግስት ይቋቋም! የህዝቦች ሉዓላዊ ሥልጣን መብት ይጠበቅ! የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ይከበር! ወዘተ በማለት የፊውዳሉን ሥርዓት በመቃወም ሰፊ ትግል አድርገዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የሲዳማም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝቦች ብሔሮች ብሔረሰቦችና ተማሪዎች ጭምር ባደረጉት ትግል ንጉሣዊ ሥርዓቱ መገርሰሱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጅ አፋኙ የደርግ ሥርዓት የህዝብን የትግል ጥያቄ በመቀማት አፋኝና ፀረ ዲሞክራሲ ይዘት ያለውን ሥርዓት በመመሥረቱ የህዝብ ጥያቄ በመታፈኑ የሲዳማ ሕዝብም ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን የደርግ ሥርዓት በመቃወም ራሴን በራሴ ማስተዳደር አለብኝ በማለት ከ1970 ዓ/ም ጀምሮ ለኦሮሞ ሕዝቦች ነፃነት በባሌ አከባቢ ከሚታገሉት ታጋዮች ጋር በመደጋገፍ (ለምሳሌ ጄኔራል ዋቆ ጉቱ ጋር አቶ ወልደአማኑኤል ዱባሌ በሲዳማ ደጋማው ወረዳዎች ደርግን ለማምበርከክ የሲዳማን ታጋዮች በመያዝ በሀማራ፣በአሮረሳ፣ በጭሬ፣ በአርበጎና ፣ በሁላና በበንሣ ወረዳዎች እስከ ሱማሊያ ድንበር ድረስ ያለውን አከባቢ በመቆጣጠር የትጥቅ ትግል ያካሄዱና በቦርቻ ወረዳም ሕዝቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ጥያቄ በማንሳት ፀረ ደርግ ትግል በማካሄዱ በጨካኝ ደርግ ሜካናይዝድ በሆነ መሣሪያ የተጨፈጨፈበትም አንዱ የትግሉ ማሳያ ነው፡፡
በኢህአደግ መሪነት በኢትዮጵያና በሲዳማም ሕዝቦች የጋራ ትግል አፋኙ ደርግ ከተገረሰሰ በኋላ ኢህአደግ ሀገርቱን ተቆጣጥሮ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እንደተረጋገጠ በ1987 ዓ/ም ሕገ-መንግስት በፀደቀበት ወቅት በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ሲዋቀሩ የሲዳማ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ የሆነው የራሴ አስተዳደር ወይም በክልል የመደራጀት መብቴ ይከበርልኝ በማለት በተወካዮቹ በኩልና ሕዝቡ በራሱ በቄጣላ ፍላጎቱንና ስሜቱን በመግለፅ ታግሎአል፡፡ ይህም በክልሉ ብሎም በሀገር ደረጃ የሚታወቅ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም ሰፊ ጫናና ፀረ- ዲሞክራሲያዊ ድርጊት በሕዝቡና በመረዎቹ ላይ ደርሶበታል፡፡
በ1994 ዓ/ም ደግሞ ተመሳሳይ ጥያቄ ጠይቆ በሰላማዊና ፍፁም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ምላሹ እንዲሰጠው ዘንባባና አረንጓዴ ቅጠል ይዞ የወጣውን ሽማግሌም ሆነ ወጣቶች በጠራራ ፀሐይ በጅምላ ጨራሽ መሳሪያ (ፒኬም) ህይወታቸውን እንዲያጡ ተደርጎአል፡፡ ይህም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ሲሆን የክልል ጥያቄው ሲነሳና ምላሽ ሲያጣ ህዝቡ ቶሎ ብሎ ያንን ጥቁር ጠባሳ ዛሬም እያስታወሰ ከፍተኛ ሀዘን እየተሰማው ሥርዓቱ ላይም ከፍተኛ ጥላቻ እንዲያድርበት ዕያደረገ ያለ ጉዳይ ነው፡፡
በ1997 ዓ/ም ደግሞ የሕዝቡ በህገ – መንግስቱ መሠረት በህጋዊ መንገድ በክልል የመደራጀት ጥያቄን በምክር ቤቱ አማካኝነት ተወስኖ ጥያቄው በፅሁፍ ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም በአንድ በኩል ጥያቄው የህዝቡ ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ሳይሆን የአመራር ጥያቄ ነው በማለት በሌላ በኩል ለጊዜዉ ይቆይና ልማት ላይ አትኩሩ በሚል በፀረ – ዲሞክራሲያዊ መንገድና በጫና ታንቆ እንዲቀር የተደረገ መሆኑ ዛሬም ቢሆን በህዝቡ መካከል በትልቅ ቁጭት የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በኢህአዴግ ዘመን ጭምር የህዝቡ ህገ መንግሥታዊ ጥያቄን ላለመመለስ አፈና እየተደረገ የቆየ መሁን ማሳያ ነው፡፡
በ2004 ዓ/ም በተመሳሳይ ሁኔታ ከሀዋሳ ከተማና ከክልል አደረጃጀት ጋር ተያይዞ በህዝቡና በወጣቱ መካከል በስፋት ጥያቄ በመነሳቱ በአመራሩና ጥያቄ በሚያነሱ አካላት ላይ ፀረ – ዲሞክራሲያዊ እርምጃ ተወስዶአል፡፡ ይህም ሌላኛው የትግል ምዕራፍ ነው፡፡
ስለሆነም ፀረ-ሕገመንግስታዊ በሆነ አኳኋን በሚወሰዱት እርምጃዎች የሕዝቡ ጥያቄ በአፈና እንዲቀለበስ ሲደረግ የቆየ በመሆኑ በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታ እየወለደ፤ ምሁራን እየተሰደዱ፣ የማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ልማት ተሳትፎ እየቀነሰ፤ በሕዝቡ ውስጥ ጥያቄው እየጎላና እየገፋ በመምጣቱ በ2010 ዓ/ም በየደረጃው ያለው ሕዝብ ወጣቶች የሀገር ሽማግሌዎች ሴቶች ወዘተ ጥያቄያችን ይመለስ በማለት በየወረዳውና ከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም በ566 ቀበሌያት ጭምር ጥያቄያችን ሳይመለስ ማንኛውንም ዓይነት የልማት ስራ ለመስራት አትደግፉን በማለት ሕዝቡ ጫና በመፍጠሩና በየቀበሌውና በየወረዳው ም/ቤቶችና በየሕዝባዊ መድረኮቹም ጭምር በስፋት ተወያይቶ በመወሰኑ የዞኑ ም/ቤት በኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 47 ንዑስ አንቀፅ 3(ሐ) እና በክልሉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39/6(ሐ) መሠረት በሙሉ ድምፅ አፅድቆ ጥያቄው አፋጣኝና ሕገ-መንግስታዊ በሆነ አግባብ ምላሽ እንዲያገኝ ለሁለተኛ ዙር ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ህዝቡ ጥያቄዉ ምላሽ እንዲያገኝ ትግል እያደረገ ይገኛል፡፡
1.4 ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምክንያቶች እንደመነሻ
የሲዳማ ብሔር ክልል ሆኖ ባለመደራጀቱ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድሎችን በፍትሀዊነት እየተጠቀመ አይደለም፡፡ የሲዳማ ብሔር ፖለቲካዊ አቅም ማለትም፤ የመደራደር፣ የማስፈፀም አቅምና ለመደራጀት ምቹ ሁኔታን እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ክልሉን የሚመራዉ ፓርቲ (ደኢህዴን) በሚመለከት ብሔራዊ ድርጅቶች ተባብረው የፈጠሩት ግንባር ሲሆን ያሳካቸዉ ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው በ27 ዓመት ሂደት የተጠናከረ ክልላዊ መግባባት አልፈጠረም፡፡ ድርጅቱ በሁለት አስርት አመታት በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችና የፀጥታ ችግሮች ምክንያት በመባከን የሕብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላትና ለማንቀሳቀስ ሳይችል ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ይህ ሁኔታ በክልሉ ያሉ ሁሉንም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሙሉ የጎዳው ተግባር ሲሆን የሲዳማ ህዝብ ግን ይህንን በመቃወም ለበርካታ ጊዜ ትግል አድርጎ ሰሚ ያጣበት በመሆኑ በእጅጉ ያሳዘነው ጉዳይ ነው፡፡ ህዝቡ በፌደራል ሥርዓት ዉስጥ ሆኖ በራስ ህገመንግስት የሚተዳደርበትና አግባብነት ያላቸዉ ህጎች የሚያወጣበት ዕድል አላገኘም፤ጥያቄየም አልተመለሰልኝም በሚል በከፍተኛ የሥነልቦና ጉዳት ዉስጥ ወድቆአል፡፡
በእነዚህ ተግዳሮቶች መነሻነት የሲዳማ ህዝብ በሕገ መንግሥቱ የተሰጡትን የመልማት ዕድሎች አሟጦ ሳይጠቀም ቆይቷል፡፡ ከዚህ የተነሳ ዞኑ የመልማትና የተጠቃሚነት ዕድሉን አለመጠቀም ብቻ ሳይሆን ተጎጂም ነበረ፡፡ ከዞኑና ከተማ አስተዳደሩ ተጨባጭ ሁኔታ የመልማት ስትራቴጂ ቀይሶ ሕዝቡን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው መብት መሠረት ራስን በራስ የማስተዳደር የክልል ጥያቄ ማቅረቡ እጅግ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ሆኗል፡፡
የሲዳማ ህዝብ የመልማት ዕድል እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የሚከተሉ አገራት የእያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ የመልማት እኩል እድልና መብትን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን የሚቀየሰው የልማት አቅጣጫ ህዝቦቹ ከልማቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ የሚፈጥር መሆን ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ ህዝቡ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት ባለቤት ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ክምችት ያሉት ከመሆኑም በላይ አገሪቷ ለውጭ ምንዛሪ ኤክስፖርት ከምታደርገው ቡና አንፃር ከፍተኛ ምርት አቅራቢ ዞን ነው፡፡
በዞኑ ከነባሪ ከተሞች በተጨማሪ አዳዲስና ታዳጊ የማዘጋጃ ቤቶች እየተፈጠሩ የሚገኙ መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ እየተካሄደበት የሚገኝ ሲሆን ይህም ከውስጥ ገቢ ሰብስቦ ለመጠቀም ከፍተኛ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ በአጠቃላይ የዞኑን ገቢ የማመንጨት አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለገቢ አሰባሰብ አጋዥ የሚሆኑ ዝርዝር የማስፈፀሚያ ህጎች የማውጣት ሥልጣን በማጣቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሀብት ተመጣጣኝ ገቢ በመሰብሰብ እና ለሕዝብ ልማት ጥቅም ለማዋል አልቻለም፡፡
በሌላም በኩል በዞኑ ያለው ዕምቅ የተማረ የሰው ኃይል ስትራተጂካዊ በሆነና በተጠና መንገድ ወደ ሥራ በማሰማራት የዞኑን ህዝብ ተጠቃሚነት ከመጨመርም አልፎ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የሚረዱ አሰራሮችን ቀይሶ ተግባራዊ ከማድረግ ረገድ አሁን ያለው መዋቅር ትልቅ እንቅፋት ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ዞኑ ካለው የወረዳና የከተማ መዋቅር ስፋት አንፃር የኀ/ሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገ አገልግሎት አሰጣጥ ፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስና በቅርበት ለመከታተልና ለመደገፍ አልተቻለም፡፡ይህም ማለት ከ4.1 ሚሊዮን በላይ ህዝብና 36 የወረዳና የከተማ መዋቅሮችና 566 ቀበሌዎችን ይዞ በአንድ ዞን ተደራጅቶ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ አዳጋች ይሆናል፡፡ከላይ የተጠቀሰዉን ያህል የህዝብ ቁጥርና መዋቅሮች ይዞ በዞን አደረጃጀት የተደራጀ በሀገርም ሆነ በሌሎች አገሮች የለም፡፡
2. ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት የተወሰዱ ህገ-መንግታዊና ተቋማዊ ሂደቶችና ተግዳሮቶች
በአጠቃላይ የሲዳማ ህዝብ ከላይ የተጠቀሱ ህገ-መንግሥታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መነሻዎችንና ጥያቄው ለዘመናት ሲጠይቅና መስዋዕትነት ጭምር ሲከፍልበት የቆየ መሆኑን ምክንያት በማድረግ የብሔሩ ምክር ቤት ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ/ም ባካሄደው ጉባኤ ተቀብሎ በሙሉ ድምፅ በመወሰን ውሳኔውን በቀን 12/11/2010 ዓ/ም በተፃፈ ደብዳቤ ለክልሉ ም/ቤት አቅርቧል፡፡ በዚሁ መሰረት የክልሉ ም/ቤት 5ኛ ዙር 8ኛ መደበኛ ጉባኤው ጥቅምት 23 ቀን 2011 ዓ/ም ባደረገው ስብሰባ ጥያቄው ህገ-መንግስታዊ መሆኑን በሚገባ ካጤነው በኋላ ህዝበ-ውሳኔ እንዲደራጅ ለሚመለከተው አካል እንዲተላለፍ በኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት አንቀፅ 47/3(ሀ) እና በተሻሻለው የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39(6) (ለ) መሰረት አቅጣጫ ማስቀመጡን ተከትሎ ም/ቤቱ በቁጥር ክም/አ/9/7092/2011 በቀን 12/03/2011 ዓ/ም በተፃፈ ደብዳቤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዋጅ ቁጥር 532/1999 አንቀፅ 32(2) ሥር በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ህዝበ-ውሳኔ እንዲያደራጅ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ፅ/ቤት ማስተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡
ይሁንና የክልሉ ምክር ቤት ጥያቄውን ተቀብሎ ሪፍረንዴም እንዲካሄድ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ከመፃፍ የዘለለ ምንም እንቅስቃሴ ሳያደርግ መቆየቱ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ምክር ቤቱ ህዝበ ውሳኔ በማደራጀት ጉዳዩ በአፋጣኝ ዕልባት እንዲያገኝ የማድረግ ኃላፊነትና ተጠያቂነት /Constitutional Accountability/ በቀጥታ የሚመለከተው ከመሆኑ አንፃር አጠቃላይ የህዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ዕቅድ በማቀድ፣የህዝበ ውሳኔ አስፈፃሚ ኮሚቴ በማዋቀር፣ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ፣ ሥራውን በቅንጅትና በባለቤትነት መምራት የሚገባው ሆኖ ሳለ በሚጠበቀው መልኩ ፈጣን ምላሽ ባለመሰጠቱ ጠያቂው ህዝብ በቀን 14/06/2011 ዓ/ም ቅሬታውን ለመግለፅ በቁጥር እስከ ግማሽ ሚሊየን የሚገመት ህዝብ በራሱ ጊዜ አደባባይ በመውጣት፡- ህገ መንግሥት ይከበር! ለውጡን እንደግፋለን! ሪፍረንዴም የሚደረግበት ቀን በአፋጣኝ ለህዝብ ይፋ ይደረግ! ህዝበ ውሳኔም ይፋጠን! የሚሉና ሌሎችም የህዝቡን ስሜት የሚገልፁ መፈክሮችን ማሰማቱ የሚታወስ ነው፡፡
ህዝቡ ቅሬታውን በዚህ መልኩ ፍፁም በሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ከገለፀ በኋላም ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሎ ተገቢው ምላሽ የተነፈገው ህዝብና ወጣቱ ክፍል በራሱ ጊዜ ተነሳስቶ ለሁለተኛ ጊዜ በሲዳማ ዞንና የዞኑ መቀመጫ በሆነው ሀዋሳ ከተማ ውስጥ የሶስት ቀናት የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ ዳግም ቅሬታውን ማሰማቱ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡
በነዚህ በሁለት ዙር በተደረጉ የቅሬታ ማሰሚያ መንገዶች የተላለፉ የህዝብ መልዕክቶች /Opinion/ ምላሽ ወይም ሰሚ ማጣታቸው ያሳሰባቸው ከሲዳማ ዞን ከተለያዩ የከተማና ገጠር ቀበሌያት የተወጣጡ የሀገር ሽማግሎዎች በባህሉ መሰረት በእጃቸው ሳር ይዘው በታላቁ ጉዱማሌ / የባህል ቦታ/ በመውጣት ለህዝቡና ለወጣቱ እንዲሁም ለመንግሥት ጭምር መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ይህም መልዕክት፡- የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ህዝቡ በጋራ መክሮበት ያቀረበውና ሌላው ህገ-መንግሥትያዊ ሂደት ሁሉ ተጠናቅቆ በህጉ መሰረት ሪፍሬንዴም ብቻ ቀርቶ ያለው በመሆኑ በህጉ መሰረት ሪፍሬንዴም የሚደረግበትን ቀን ህዝቡና ወጣቱ በትዕግሥት መጠባበቅ የሚገባው መሆኑን፣ በዚህ በመጠበቁ ሂደትም የማንኛውም አብሮን የሚኖር ህዝብ ሰላም የሚያውክና የንብረት መብት የሚነካ ተግበር መፈፀም በባህሉ መሰረት የተወገዘ መሆኑን፣ ይልቁንም አብሮን ያለው ህዝብ ነገም ከእኛ ጋር የሚኖርና ህዝቡ የሚያገኘው መብት ተጋሪ በመሆኑ ጥያቄያችንን እስካላደናቀፈ ድረስ አቅፈን በፍቅር መያዝ እንዳለብን ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ መንግስትም በበኩሉ እራሱ ያወጣውን ህግ አክብሮ በህገ-መንግስቱ ተገድቦ በተሰጠው አንድ ዓመት ጊዜ ገደብ ውስጥ ጉዳዩን ለህዝበ ውሳኔ ማቅረብ እንደሚገባው ለዚህም ዞኑንና ክልሉን የሚያስተዳድሩ የመንግስት አካላት ኃላፊነታውን መወጣት እንዳለባቸው፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በህጉ ተገድቦ የተሰጠው ቀን በመንግሥት በኩል ሳይከበር ቢቀር ግን መንግሥት ያላከበረውን ህግ ዜጎች እንዲያከብሩ መጠበቅ ውጤት ስለማይኖረው ከወዲሁ ህጉን አክብሮ በሀገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ሀገ-መንግሥት መሰረት ለቀረበው ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ምላሽ በህጉ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ መመለስ እንደሚገባው የሚያሳስብ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ጉዳዩ ዕልባት እንዲያገኝ ለማድረግ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት መወሰድ ያለባቸው ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ጠብቆ ያጣው የሲዳማ ህዝብ በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች ቅሬታውን እየገለፀ የቀጠለ ከመሆኑም በላይ ከሀገር አልፎ በዓለም ደረጃ ታሪካዊ በሆነ መልኩ ቁጥሩ በግምት ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የሲዳማ ሴቶች በራሳቸው ጊዜ ተነሳስተው ለብቻቸው /ፉራ ጋዶ/ ወይም “ያካ”/ የሴቶች አመፅ/ በሰላማዊ ሰልፍ አንጸባርቀዋል፡፡ በዚህም በያካ ሥርዓት እናቶችና ወጣት ሴቶች ያነሱት፡- ሀገራዊ ለውጡ የእኔም ስለሆነ እደግፋለሁ! የህግ የበላይነት ይከበር! ህገ-መንግስቱ ሳይከበር ቀርቶ ልጄን ለሞት አልፎ እንዲሰጥ አልፈልግም! እኔ እናት ነኝ፣ እህት ነኝ፣ ሚስት ነኝ፣ ልጅ ነኝ፡፡ የአደረጃጀት ጥያቄው የእኔ ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ የሪፈሬንደም ቀን ይገለፅ! …ወዘተ የሚሉት ናቸው፡፡ ይህ “ያካ” የተሰኘው የሴቶች አመፅ በባህሉ መሰረት ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠውና ሴቶች በከፍተኛ ደረጃ ቅሬታ የፈጠረባቸውን ተግባር በመቃወም የሚያካሂዱት አመፅ ሲሆን የተቃወሙት ጉዳይ ሳይስተካከል ወደ ቤት የማይገቡበትና ትግላቸውን እስከመጨረሻው ድረስ የሚቀጥሉበት ባህላዊ ሥርዓት ነው፡፡ የሲዳማ ሴቶች ይህንን ሥርዓት ከረዥም ዓመታት በኋላ ተግባራዊ ያደረጉት በዚህ ታሪካዊ በሆነው የሲዳማ የክልል ጥያቄ ላይ ነው፡፡ ይህም የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ጥልቀቱና አንጋብጋቢነቱ ምን ያህል እንደሆነ ባህሉን ጠንቅቆ በሚያውቀው ዘንድ ግልፅ ነው፡፡
በመሆኑም የሲዳማ ልጆች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ጎልማሶችና ሽማግሌዎች በሙሉ ከዚህ በላይ በተገለፁ ሁኔታ ጥያቄውን በማቅረብ ህገ መንግስታዊ ምላሽ እየጠበቀ ያለ ከመሆነም በላይ ምላሹ ሲዘገይበትም ፍፁም ሰላማዊና ታሪካዊ በሆነ ሁኔታ ቅሬታውን እያቀረበ ትዕግስቱ እስከ ጫፍ ድረስ ያደረሰ መሆኑን የሚስጠነቅቅ በመሆኑ ለጉዳዩ ቶሎ ምላሽ ካልተሰጠ ሊከተል የሚችለው ቀውስ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ መንግስት በትኩረት ሊያየው የሚገባ ነው፡፡
3. የሲዳማ ህዝብ ፅኑ ፍላጎትና አሁን ያለበት ነባራዊ አውድ
ከላይ በሰነዱ እንደተመከለተው የሲዳማ ብሔር ጥያቄ ታሪካዊና ህዝባዊ መሠረት ያለው ሲሆን ከብሔሩ ም/ቤት ፀድቆ በሕገ መንግስቱ መሠረት ጉዳዩን ለማስፈፀም ሥልጣን ለተሰጠው አካል ቀርቦ እያለ በሚፈለገው ፍጥነት ባለመፈፀሙ ወይም ሪፈሬንደም የሚደረግበት ጊዜ ለህዝብ ይፋ መደረግ ከነበረበት ምክንያታዊ ጊዜ በላይ በመቆየቱ ከዚህ በላይ እንተገለፀው የሕዝቡን ስሜት የሚያንፀባርቁ በርካታ ህዝባዊ ኩነቶችና ሰላማዊ ሰልፎች እንዲሁም የስራ ማቆም አድማ ተካሂዷል፡፡
በተጨማሪም የሲዳማ ሕዝብ አጠቃላይ በሕዝብ አደረጃጀቶቹ ማለትም በወጣቶች እንቅስቃሴ (በኤጄቶዎች)፣ በሴቶች እንዲሁም በሀገር ሽማግሌዎች አደረጃጀት ጭምር በየጊዜው የሲዳማ ሕዝብ ፍላጎትና ትግል ላይ እየመከረና ሂደቶችን እየገመገመ በመላው የሲዳማ ሕዝብ ዘንድ የተቀጣጠለ የትግል አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደፊት እየገሰገሰ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከላይ በተጠቀሱ ሂደቶችና ክንዋኔዎች የተንፀባረቁ የሕዝብ ፍላጎቶችና ዓላማዎች እንደሚከተለው ተጠቃሎ ቀርቧል፡፡
ሀ/ የሲዳማ ብሔር የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ የሚደግፍ ስለመሆኑ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን መሠረታዊ በሚባል ደረጃ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካው፣ እና ዴሞክራሲያዊ ፍትህን በሀገር ደረጃ ለማስፈን እየተሠሩ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ለሀገር ግንባታ ያላቸው ሚና ወሳኝ መሆኑን እንደሚገነዘብና ለውጡን ለመደገፍ ያለው አቋም ፅኑ እንደሆነ አንፀባርቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሲዳማ ብሔር ለማንነቱና ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ብሔራዊ ጭቆናውን ከጥንስሱ ጀምሮ ሲታገል የቆየበት ከመሆኑም በላይ በተደጋጋሚ የንብረት፣ የአካልና የህይወት ዋጋ ጭምር የተከፈለበት ታርካዊ ይዘት ያለው ጥያቄ እንጅ የራሳቸው የግል አጀንዳ ያላቸው አንዳንዶች እንደሚሉት በሀገር ደረጃ ለዴሞክራሲና ለሀገር ግንባታ እየተደረገ ያለውን ለውጥ ወደ ኋላ የሚጎትት አለመሆኑ ብቻም ሳይሆን ለውጡን የራሱን የዘመናት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሚያደርግ እንደሆነ አድርጎ የሚቀበል መሆኑን በሰላማዊ ሰልፉና በባህላዊ ክንዋኔዎቹ አንፀባርቋል፡፡
ለ/ ሕገ – መንግስታዊና ፌዴራላዊ ስርዓቱ ላይ ያለውን ፅኑ እምነት
የሲዳማ ሕዝብ ያለፈው አሃዳዊ ሥርዓተ መንግሥት ጊዜ የነበረው ጨቋኝ ሥርዓት በሀገሪቱ ላለው ለባህል፣ ለቋንቋና ለሐይማኖት ብዝሃነት ዕውቅና ካለመስጠቱ የተነሳ የራሱን ነባር ብሐራዊ ማንነት በመደፍጠጥ ብሔራዊና መደባዊ ጭቆና ስር እንዲማቀቅ በማድረጉ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ጋር በመሆን በትጥቅ ትግል ስታገል የቆየና ለሀገራችን ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት የማይተካ አሻራ ያኖራ ህዝብ ነው፡፡
በመሆኑም የሲዳማ ብሔር በሕገ-መንግስቱ መሠረት ተግባራዊ የሚደረግ ሕብረ-ብሔራዊ ስርዓት እንዲስፋፋ ትግል እንደሚያደርግና የሀገር ግንባታ ሂደት ውጤታማነት ለራሱ መብት መከበር ዋስትና እንደሆኑ ፅኑ እምነቱን የገለፁበት ነው፡፡
ሐ/ የሲዳማ ብሔር ጥያቄ ሕገ-መንግስቱ በሚያስቀምጠው መሠረት በሕዝበ ውሳኔ ብቻ እንዲፈፀም የሚፈልግ ስለመሆኑ
የሲዳማ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ያካሄዳቸው ትግሎች አሁን ያለው የሕዝብ ፍላጎት ክልል በመሆን ከሚያገኘው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር የራሱን ማንነት፣ ቋንቋ ባህል ለማሳደግና በሀገር ደረጃ በአደረጃጀትም በስሙም መታወቅ /Visibility/ ነው፡፡
በመሆኑም ራሱን ችሎ በክልል ለመደራጀት ህገ መንግስታዊ ምላሽን እንዲሚፈልግና ጥያቄውም በሕዝበ ውሳኔና በሕዝበ ውሳኔ ብቻ እንደሚፈፀምለት፣ ከዚህ ውጭ ያሉ ሌሎች አካሄዶች ኢ-ሕገ መንግስታዊ ከመሆናቸውም በላይ የሲዳማ ህዝብ ለዘመናት ሲጠይቅና ሲታገልለት እንዲሁም በተደገጋሚ የደም ዋጋ ሲከፍልበት ለቆየው ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ የማይሰጡ በመሆናቸው በፍጹም እንዲማይቀበል ግልፅ ያደረገበትና የተስማማበት ጉዳይ ነው፡፡
መ/ ለሰላምና ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በሠላም አብሮ የመኖር ፍላጎት
የሲዳማ ህዝብ በሀገሪቱ ታርክ የህልውናው መሠረት የሆነውን ባህል፣ ቋንቋ እና ማንነት በግድ በአፈና እንዲተው ያደረገውን ጨቋኝና ነፍጠኛ ስርዓት ሲወገድ በነበረው ሁኔታ ጨቋኝ የነበሩ ባላባቶች ሌሎች አካባቢዎች ላይ ሲሳደዱና ከፍተኛ በደል ሲደርስባቸው የሲዳማ ህዝብ ግን በሆደ ሰፊነቱ በማቀፍ ከሌሎች አከባቢዎች በተለየ ሁኔታ እንዲይገደሉና እንዳይፈናቀሉ እንዲሁም ንብረታቸውን እንዳይበተን አድርጎ በባህላዊ አደረጃጀትና ባላው የአብሮነት እሰቶች ያቆየ ሕዝብ እንደነበረ የቅርብ ዘመን ታርክ ነው፡፡
በፌዴራልና በሕገ-መንግስታዊ ስርዓት መሠረታዊ ዕሴቶችና መብቶች የሆኑት ሁሉም ዜጋ በፈለገበት ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት፣ ንብረት የማፍራት፣ የደህንነት የነፃነት መብቶች እንዲከበሩ ፅኑ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ከላይ እንደተመለከተው የብሔሩ የመቻቻል፣ የመፈቃቀርና አብሮ የመኖር ልዩ እሴት ያለው ህዝብ ነው፡፡ ይህም ከሲዳማ ህዝብ ጋር በገጠርና በከተማ በሰላምና በፍቅር አብረው የሚኖሩ ከራሱ ብሔር ውጭ የሆኑ ህዝቦች የሚመሰክሩት ሀቅ ነው፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ የራሱን ሕገ-መንግስታዊ መብት ለማረጋገጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አብረውት በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎትና መብት ለመግፋት እንዳልሆነ በተለያዩ መድረኮችና ሕዝባዊ ኪንዋነዎች አንፀባርቋል፡፡
በተለይም የሲዳማ ኤጀቶዎችና ሽማግሌዎች በአስር ሽህዎች የሚቆጠሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ታላቁ ጉዱማሌ ተሰብስበው ባደረጉት ውይይት ላይ የተደረሰው ስምምነትና ባህላዊ መሃላ በውስጡ የሚገኙ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በብሔራቸው ምክንያት እንዳይነካ መሃላ የተገባበትና መኃላውም (ጎንዶሮም) የሲዳማ ሕዝብ ለሰላምና ለአብሮነት ያለውን አቋም የሚያሳይ ነው፡፡
ሠ/ የሲዳማ ሕዝብ አስቸጋር ጊዜ ጭምር ለመሪ ድርጅቱ ድጋፍ ያሳየ ሕዝብ ስለመሆኑ
በሲዳማ ሕዝብ የፖለቲካ ትግል ታሪክ በየጊዜው ሀገርን ያስተዳደሩ ጨቋኝ ሥርዓተ መንግስታት ለባህሉ፣ ለቋንቋውና ለማንነቱ እንዲሁም ፖለትካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶቹ ቦታ ያልነበራቸው በመሆኑ መደባዊ ጭቆና እንዲቀር ከታገሉ ሃይሎች ጋር መታገሉ ከላይ በሰፊው ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ብሔራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት በሀገሪቱ ሥር እንዲሰድ፣ ብሔራዊ ጭቆና እንዲቀር፣ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋቸውና ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳደሩ የሚያደርግ መሠረታዊ ዓላማ ያለው በመሆኑ ድርጅቱን ያለ ምንም ማመንታት ሲደግፍና በድርጅቱ ህዝባዊ መሠረትና በአንድነት ላይ በአሃዳውያን ድርጅቶች ዘንድ በተደረገ ጫና ምክንያት በ1997 ዓ/ም ምርጫ ወቅት ድርጅቱ ችግር ውስጥ ገብቶ በነበረበት ጊዜ ጭምር የሲዳማ ሕዝብ በዓላማ ላይ ያለውን ፁኑ ዕምነት በሚያጠናክር መልኩ ድምፁን ሰጥቶ ድጋፉን አሳይቷል፡፡ አሁንም ቢሆን የሲዳማ ሕዝብ መብቱን የሚያረጋግጥለት ከህገ መንግሥቱ በታች ሆኖ ይህ ድርጅት መሆኑን በጥልቀት እንደሚያምንና በዚህም ምክንያት ጥያቄው ካገኘ እስከመጨረሻው ድረስ ድርጅቱን ለመደገፍ ያለውን ፍላጎቱን በግልፅ አሳውቋል፡፡
4. የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ካልተመለሰ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶች
የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ያንድ ብሔር ጥያቄ ቢሆንም በክልሉ ብሎም በሀገር ደረጃ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ያለ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተለይም የሲዳማ ህዝብ ለዘመናት ሲጠይቅና ሲታገል የኖረበት ከእስራት ጀምሮ ብዙ የንብረት፣ የአካልና የህይወት መስዋዕትነት ሲከፍልበት የኖረበት ጉዳይ ሆኖ አሁን ወደ አለበት ደረጃ የደረሰ ነው፡፡ የሲዳማ ሕዝብ በደቡብ ክልል መንግስት ዉስጥ ሲደራጅ በወቅቱ ህዝቡ ተወያይቶበት ያልተቀበለዉና በጥቂት መሪዎች ተጽዕኖ ብቻ የተዋቀረ በመሆኑ ለረጅም ጊዜያት ህዝቡ የጠየቀዉን የሕዝብ ፍላጎት አንጻር ለክልል ጥያቄው ምላሽ ሊሰጥ የሚገባ ስለመሆኑ ግልፅ ነዉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ክልል የመሆን መብትና አተገባበሩ በሕገ-መንግስቱ መሠረት የብሔር ዉሳኔ እንጂ በየትኛዉም ሌሎች መስፈርቶች የሚወስን አይደለም፡፡ ከላይ እንደተመለከተዉ የክልሉ አወቃቀር ዘላለማዊ (የማይነካ) ሳይሆን በጊዜ ሂደት ሊቀያየርና ሊለዋወጥ የሚችል ነዉ፡፡ ህገ-መንግሥትን መሰረት በማድረግ ብሔር ብሔረሰቦች በራሳቸዉ ፍላጎት በአቅማቸዉ መሠረት መንግሥት ሆነው ራሳቸዉ እንዲያስተዳድሩ ዕድል መስጠት የግድ ይላል፡፡
የሲዳማ ብሔር ጥያቄ ሕገ-መንግስታዊ መብት የመጠቀም ጉዳይ ከመሆኑም በላይ የፈዴራል አባል በመሆን ኢትዮጵያዊ አንድነት የሚያጠናከር እና አሁን ካለው አገራዊ የመደመር ፍልስፍናችን አንፃር የብሔሩ መሠረታዊ ጥያቄ መመለሱ በአገርም ሆነ በክልል ከሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች ጋር የበለጠ መቀራረብንና መፈቃቀርን የሚያጠናክር ነወ፡፡ ይህ መብት ገብራዊ ካልተደረገ ሊያጋጥም የሚችል ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስጋት እንደሚከተለዉ ቀርባል፡፡
ሀ/ ለሕገ – መንግስታዊነትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ያለው ስጋት
በሀገራችን የተጀመረው የለውጥ ሂደት ሥር ሊሰድ የሚችለው በዋናነት በሕገ-መንግስቱ መሠረት መምራት ሲቻልና የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ተገቢ የሕዝብ አመኔታ ሲያገኙ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረ ፖሊትካዊ የመንግስት አመራር ስርዓት በሕግና በሕገ-መንግስት የማይመራ የዴሞክራሲ ተቋማት ም/ቤቶች፤ ምርጫ ቦርድ፣…ወዘተ ላይ እምነት ባለመኖሩ ምክንያት የተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህ በመሆኑ የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ማፈን (አፍኖ ማቆየት) በአንድ በኩል ሕገ-መንግስትን በግልፅ ከመናድ ባሻገር በም/ቤቶችና በፖለቲካ ድርጅቱ ላይ ያለው አመኔታ በእጅጉ የሚሸረሽር ነው፡፡ በተለይም ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ተቋማት በተለይም ምርጫ ቦርዱ ለቀጣይ ምርጫ እያደረገ ላለው ዝግጅት ተዓማንነት እንዲኖረውና ነፃነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ለዴሞክራሲያችን ወሳኝ በመሆኑ በሕጉ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ መዘገየቱና ፖለትካዊ ምላሽ መፈለጉ የተቋማት አመኔታ የሚሸረሽርና ሀገራዊ ለውጥን የመቀልበስ አቅም ያለው በመሆኑ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
ለ/ ለሰላምና ለፀጥታ ያለው ስጋት
ከላይ እንደተገለፀው የሲዳማ ህዝብ በትግል ስልቶች ላይ በሰላምና ፀጥታ ላይ ያለው የፀና አቋም ምን እንደሚመስል በግልጽ ያሳየ መሆኑ ከላይ ተደጋግሞ የታየ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ የመመለሱ ጉዳይ በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የሚባልበት ምክንያትም ትግሉ የሁሉም ህብረተሰቡ ክፍል ቢሆንም ዋናው የስበት ማዕከሉ መላው የወጣቱ እንቅስቃሴ ( youth movement) ሲሆን ይህ እንቅስቃሴ በጣም የተደራጀና የሲዳማ ህዝብ ፍላጎት ከወጣቱ ዘንድ የጠለቀ ይዘት ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን የሚታየው የማህበረዊ ገፆችና የተለያዩ አደረጃጀቶች ላይ የሚስተዋለው አዝማሚያ አካባቢው የመረጋጋትና የሰላም እጦት ልሸጋገር የሚችል መሆኑ አሳሳቢ ነው፡ በመሆኑም ይህ መዘዝ ሊያመጣ የሚችለው ፖለትካዊ ኪሳራ ግልፅ ነው፡፡
ኳይ መፈታት ያለበት ነው፡፡ አስተዳደራዊ መዋቅር ሂደቶች በዋናነት መንግስት ለሕብረተሰቡ የሚገቡ አገልግሎቶችንና የልማት ስራዎችን ማቀላጠፍ እንጅ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ በተጨማርም መዋቅራዊ አደረጃጀቱ ህዝቡ ተገቢ አገልግሎት እንዲያገኝ በተገቢው ሁኔታ በፍጥነት ካልተፈታ በልማትና በሕዝብ አገልግሎት ላይ ጫና ማሳደሩ አይቀርም፡፡ በተለይም የሲዳማ ሕዝብ አሁን ያለበት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያ ችግሮች በተለይም ስራ አጥነትና ድህነት በስፋት የሚታይበትና እንዲሁም የአደረጃጀት ጥያቄ በቶሎ በመፍታት በልማት የወጣቱን የስራ አጥነትና የድህነት ችግር መፈታት ካልተቻለ በሀገር ደረጃ የተቀበረ ቦንብ (time bomb) ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ጥያቄ የሁሉም የሕብረተሰቡ ክፍል በተለይም የወጣቱ ሊቀለበሰ የማይችል ፍላጎት በመሆኑ በአስቸኳይ በመመለስ መንግስት ልማቱን ሊሠራና ሊደግፍ ይገባል፡፡
መ/ ለመሪ ድርጅት- ኢህአደግ/ደኢህዴን/ ህዝቡ ያለው ድጋፍና አመኔታ ላይ ያለው ስጋት
የመሪ ድርጅቱ ከላይ እንደተመለከተው የሲዳማ ሕዝብ ከብሔራዊ ፍላጎቱ ጋር የሚጣጣም ስትራቴጂና ፖሊሲ ያለው በመሆኑ በችግር ጊዜ እንኳን ሲደግፍና ሲመርጥ የቆየ ሕዝብ ነው፡፡
በተጨማሪም የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ተከትሎ የተደረጉ በኢህአደግና/ደህዴን የማዕከላዊ ኮሚቴና በአስፈፃሚ ኮሚቴ እንድሁም በ10ኛዉ የደህዴን ጉባኤ ይሁንታ ያገኘ ጉዳይ በመሆኑ አሁን ባለበት ሁኔታ የሲዳማ ሕዝብ ውሳኔውና የድርጀት አቅጣጫ እንዲፈፀምለት በጥብቅ ይፈልጋል፡፡ ይህም በመሆኑ ዛሬም ቢሆን የሲዳማ ህዝብ መብቱን ሊያረጋግጥለት የሚችለው መሪ ድርጅቱ እንደሆነ ትልቅ እምነት ያለው መሆኑን በነበሩ የትግል ክንዋኔዎች አቋሙን አሳይቷል፡፡ በመሆኑም ይህ ሳይሳካ ሲቀር አጠቃላይ ሕዝቡ በድርጅቱ ላይ ያለው እምነት የሚሸረሸር መሆኑ ግልፅ አዝማሚያው ታይቷል፡፡
ማጠቃለያ
የሲዳማ ብሔር ለረዥም ዓመታት የራሱን ዕድል በራሱ ለመወሰን ቋንቋውንና ባህሉን፣ ማንነቱን ለማጎልበት እልሕ አስጨራሽ ትግል እያደረገ ቆይቷል፡፡ ጥያቄውም በህገ መንግሥቱ መሰረት በህዝበ ውሳኔ ብቻ እንዲፈፀምለት በክልሉ ም/ቤት ቀርቦ ለምርጫ ቦርድ ተመርቶ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ይሁንና ህገ-መንግሥቱ ባስቀመጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ ምላሽ የሚያገኝበት ምክንያታዊ ጊዜ ውስጥ እንቅስቃሴ ባለመደረጉ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ የፈጠረ ጉዳይ በመሆኑ በሰላማዊ ሰልፎችና በሥራ ማቆም አድማ በተደራጀ ሁኔታ እየታገለ ይገኛል፡፡ በትግል ሂደቱም በሰላምና ፀጥታ፣ ለአብሮነትና ለመቻቻል፤ ለመሪ ድርጅት ያለው እምነት፣ በህገ መንግስታዊና ፌዴራላዊ ሥርዓት ላይ ያለው ፅኑ እምነትና ጥያቄው በሪፈሬንደም ብቻ መፈፀም እንዳለበት በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ክንውኖች በይፋ ፍላጎቱን አሳውቋል፡፡ በመሆኑም በህገ መንግሥቱ መሰረት ባይፈፀም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሥጋቶችና አደጋዎች ግልፅ በመሆኑ ሊተኮረበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡